የዘር ቅንጣት የሚያክል እስስት ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ተመራማሪዎች በምድራችን ላይ ትንሽ ነው የተባለ እስስት በማዳጋስካር ማግኘታቸውን ተናገሩ።
እስስቱ ከማነሱ የተነሳ የዘር ቅንጣት ያክላል ተብሏል።
የማዳጋስካር እና ጀርመን ተመራማሪዎች በተጨማሪም ሁለት ትንንሽ እንሽላሊቶች ማግኘታቸውን ይፋ አድርገዋል።
ወንዱ እስስት፣ ብረኬዢያ ናና የሚባል ሲሆን አካሉ 13.5 ሚሊሜትር እንደሆነ ተገልጿል።
በሙኒክ እንደሚገኘው ባቫሪያን የእንስሳት ሙዚየም ከሆነ ይህ እስስት በዓለም ላይ ከታወቁት 11 ሺህ 500 ተሳቢ እንስሳት መካከል በጣም ትንሹ ነው።
ይህ በዓለማችን ላይ ትንሽ ነው የተባለው እስስት፣ ከጭራው ጫፍ እስከ አፍንጫው ድረስ ርዝመቱ 22 ሚሜትር ርዝመት አለው።
ሴቷ ግን ከወንዱ በጥቂት ሚሊ ሜትሮች ረዘም ትላለች ያሉት ተመራማሪዎች 29 ሚሜትር እንደምትረዝም አሳውቀዋል።
ተመራማሪዎቹ ሌላ ዝርያ ይገኛል በሚል ተስፋ ጥረታቸውን ቀጥለዋል።
አዲሱ እስስት የተገኘው በሰሜን ማዳጋስካር ሞንታኔ በሚባል ጫካ ውስጥ ሲሆን የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል ተብሏል።
በሃምቡርግ በሚገኘው የተፈጥሮ ታሪክ ማዕከል ውስጥ ተመራማሪ የሆኑት ኦሊቨር ሃውልቲሼክ ይህ የፍሬ ያክል ትንሽ የሆነ እስስት በደን ጭፍጨፋ ምክንያት ለመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል።
ነገር ግን አካባቢው በቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥበቃ እየተደረገለት ሲሆን ይህም ዝርያው ሊተርፍ ይችላል የሚል ተስፋ አሳድሯል።
ተመራማሪዎች ይህንን የእስስት ዝርያ ምስጥ አድኖ እንደሚበላ እና በምሽት በሳሮች መካከል እንደሚደበቅ ደርሰውበታል።
ተመራማሪዎች ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ይህ የእስስት ዝርያ በዓለም አቀፉ የተፈጥሮ ጥበቃ ሕብረት ዘንድ ድጋፍ ለማድረግ እንዲቻል እጅግ በጣም ለአደጋ የተጋለጡ ዝርያዎች ዝርዝር ውስጥ እንዲመዘገብ ጠይቀዋል።












