በኬንያ የማደጎ ህፃናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት የፈፀመው አሜሪካዊ በእስር ተቀጣ

ግሪጎሪ ዶው

የፎቶው ባለመብት, YouTube

በኬንያ የሚገኙ ማደጎ ህፃናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት የፈፀመው አሜሪካዊ የ15 አመት እስር ተፈረደበት።

የክርስቲያን ሚሲዮናዊ (መልዕክተኛ) ነኝ የሚለው ግለሰብ ህፃናት ሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት በመፈፀም ጥፋተኛ ሆኖ ያገኘው የአሜሪካ ፍርድ ቤት ነው።

የ61 አመቱ ግሪጎሪ ዶው ከባለቤቱ ጋር አቋቁሞ የነበረው የህፃናት ማሳደጊያ ከጎሮጎሳውያኑ 2008- 2017 ድረስ አገልግሎት ሲሰጥ ነበር ተብሏል።

"ግሪጎሪ በመፅሃፉ ላይ የተጠቀሰው የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡት ተኩላዎች መካከል አንዱ ነው" በማለት የፌደራል ቢሮ ምርመራ (ኤፍቢአይ) ሚካኤል ድሪስኮል ተናግረዋል።

ባለፈው አመት ግሪጎሪ የተከሰሰበትን አራት ወንጀሎች ጥፋተኝነቱን አምኗል።

በምዕራብ ኬንያ በሚገኝ ቦታ የተቋቋመው የህፃናት ማሳደጊያው ፔንስይልቫኒያ በሚገኝ ቤተ ክርስቲያንም በከፊል የገንዘብ ድጎማ ይደረግለት ነበር ተብሏል።

ግለሰቡ ላይ ምርመራ የተጀመረበት በአሜሪካዋ ኑሮዋን ያደረገች ኬንያዊት በህፃናቱ ማሳደጊያ አካባቢ ቤተሰቦቿን ልትጎበኝ በሄደችበት ወቅት የሰማችውን ሪፖርት ማድረጓን ተከትሎ እንደሆነ ዋሽንግተን ፖስት በዘገባው አስነብቧል።

ማርጋሬት ሩቶ የተባለችው ይህችው ግለሰብ ከህፃናቱ ማሳደጊያ አምልጠው የመጡ የ12 አመትና የ14 አመት ታዳጊዎች የደረሰባቸውን ወሲባዊ ጥቃት ለአካባቢው ነዋሪዎች ማጋራታቸውን ተከትሎ የተነሳውን ቁጣ ለዋሽንግተን ፖስት አጋርታለች።

ግለሰቧ በራሷ ተነሳሽነት ምርምሯን በመቀጠል ልጆቹን አዋርታ ቃላቸውንም ተቀብላቸዋለች።

ያላትን መረጃ በሙሉ ለኤፍቢአይ ከሰጠች በኋላ፣ ኤፍቢአይ የደረሰውን ጥቆማ ተከትሎ ባደረገው ምርመራ ከ2013-2017 ድረስ ቢያንስ አራት ታዳጊዎች ላይ ጥቃት መፈፀሙን ደርሸበታለሁ ብሏል።

"ሁለቱ ታዳጊዎች ጥቃቱ ሲጀመርባቸው እድሜያቸው 11 ነበር። የተከሳሹ ባለቤት ራሷ ታዳጊዎች የወሊድ መከላከያ በክንዳቸው እንዲቀበር በማድረግ የተባበረች ሲሆን፤ ግለሰቡ ለአመታት ታዳጊዎችን ያረግዙ ይሆን የሚለውን ፍራቻ በማስቀረት ለአመታት ወንጀሉን ሲፈፅምባቸው ነበር" በማለት የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ግለሰቡ ኬንያ ከመሄዱ በፊትም በአውሮፓውያኑ 1996 በአሜሪካ በፈፀመው ወሲባዊ ጥቃት በማስጠንቀቂያ እንዲሁም ለአስር አመት ያህልም "ህፃናት ደፋሪ" በሚልም ስም እንዲመዘብ ተደርጎ ነበር።