ኮሮናቫይረስ፡ አፍሪካ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የኮቪድ ክትባት መስጠት ትጀምራለች ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዓለም ጤና ድርጅት ሁሉም የአፍሪካ አገራት እስከ የካቲት ወር መጨረሻ ድረስ "ከፍተኛ ቅድሚያ" ለሚሰጣቸው ሰዎች የኮሮናቫይረስ ክትባት መከተብ አለባቸው አለ።
ኮቫክስ 90 ሚሊዮን ክትባቶችን ወደ አፍሪካ በቅርቡ ማሰራጨት ይጀምራል ያለው የዓለም ጤና ድርጅት፣ የስርጭት መጠኑም የሚወሰነው አገራት ባላቸው የሕዝብ ብዛት መጠን መሆኑ ተመልክቷል።
ለእያንዳንዱ አገር የሚከፋፈለው ክትባት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ከፊት ተሰልፈው እየሰሩ ያሉ የጤና ባለሙያዎች ብቻ የሚያገኙት ሳይሆን፣ ከፍተኛ ቅድሚያ የሚሰጣቸው አካላትንም ለመከተብ ያስችላል ብሏል።
ሁሉም የአፍሪካ አገራት የኮቪድ-19 ክትባት እንዲያገኙ የሚሰራው ኮቫክስ የተሰኘው ጥምረት ክትባቱን መቼ እነደሚያጓጉዝ እና የትኛው አገር ምን ያህል እና መቼ ያገኛል የሚለውን ዝርዝር አውጥቶ መጨረሱ ተገልጿል።
የዓለም ጤና ድርጅት ሁሉም የአፍሪካ አገራት የኮሮናቫይረስ ክትባትን በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ መስጠት መጀመር አለባቸው ብሏል።
በዓለም ጤና ድርጅት ከክትባት ጋር በተያያዘ የሚሰሩት ዶ/ር ሪቻርድ ሚሂንጎ ክትባቱ በሚቀጥሉት አንድና ሁለት ሳምንታት መሰጠት እንዲጀምር "አገራት የመጀመሪያውን ደረጃ ዝግጁነት ያሟላሉ ብለን ተስፋ አእናደርጋለን" ካሉ በኋላ በየካቲት ወር መጨረሻ ክትባቱ መሰጠት እነደሚጀምር ገልፀዋል።
ይህ ኮቫክስ ለአፍሪካ አገራት የሚሰጠው 90 ሚሊዮን ክትባት የመጀመሪያው ዙር ሲሆን እስከ ፈረንጆቹ 2021 መጨረሻ ድረስ 600 ሚሊዮን ያህል ክትባቶች ለአፍሪካ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠብቅ ተገልጿል።
ይህ ክትባት አገራት ካላቸው የሕዝብ ብዛት ውስጥ እስከ 20 በመቶ ድረስ መከተብ ያስችላቸዋል ተብሏል።
በፈረንጆች 2022 እያንዳንዱ አፍሪካዊ የኮሮናቫይረስ ክትባትን ያገኛል ተብሎ እቅድ መቀመጡንም ጤና ድርጅቱ አስታውቋል።
ከኮቫክስ በአቻነት የአፍሪካ ሕብረት የጀመረው ጥረት መኖሩን የተናገረው የዓለም ጤና ድርጅት በእነዚህ ሁለት መንገዶች በሚገኝ ክትባት በ2021 መጨረሻ እስከ 40 በመቶ የሚደርሱ አፍሪካውያን ክትባቱን ያገኛሉ ተብሎ ታቅዷል።
ይህም በ2022፣ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑ አፍሪካውያን ክትባቱን ማግኘት ያስችላቸዋል ማለት ነው።
ኮቫክስ ምንድን ነው?
ኮቫክስ (COVAX) ምጣኔ ኀብታቸው ደካማና መካከለኛ ለሆኑ አገራት ክትባቱን ለማቅረብ ያለመ፣ በዓለም ጤና ድርጅት እና በሌሎች ዓለም አቀፍ የጤና ተቋማት የተመሰረተ ኢኒሼቲቭ (ጅማሮ) ነው።
ሁሉም የአፍሪካ አገራት ይህንን ጅማሪ ተቀብለውታል።
ይህም ማለት አፍሪካ በዚህ ጅማሮ በኩል ክትባቱ ፍቃድ ካገኘና ከፀደቀ በኋላ፣ 220 ሚሊዮን ክትባቶችን ታገኛለች።
እኤአ በ2021 መጨረሻ ላይ ኮቫክስ 2 ቢሊዮን የኮቪድ-19 ክትባቶችን ለመግዛት እቅድ ይዟል።
ክትባቱን ቀድሞ የሚያገኘው ማን ነው?
ይህ አገራቱ የኮቪድ-19 ክትባትን ስርጭት እንዴት ለማካሄድ በሚወስኑት ውሳኔ ላይ ይመሰረታል።
የዓለም ጤና ድርጅት መመሪያ የጤና ባለሙያዎች የኮሮና መካለከል ላይ ከፊት ያሉ በመሆኑ ክትባቱን ቅድሚያ ማግኘት እንዳለባቸው ያስቀምጣል።
በመቀጠል ደግሞ ወደ አገራት መግቢያና መውጫ ላይ የሚሰሩ ግለሰቦች፣ በእድሜ የገፉ ሰዎችና የተለያዩ ተያያዥ የጤና ችግር ያለባቸው ግለሰቦች ክትባቱን ከሌሎች ዜጎች ቀድመው ያገኛሉ ሲል አስቀምጧል።
ቀሪው ሕዝብ እነዚህ ዜጎች ከተከተቡ በኋላ ይሰጠዋል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት በመመሪያ ላይ አመልክቷል።
















