“የክትባት ክፍፍሉ ለሞራል መላሸቅ ያጋልጠናል” ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ዓለም የኮሮናቫይረስ ክትባትን እየተከፋፈለ ያለበት ሁኔታ ለሞራል መላሸቅን የሚያጋጥ እንደሆነ ገለጹ።
ዶ/ር ቴድሮስ የክትባት ክፍፍሉ ሊፈጥር የሚችለው የሞራል ቀውስ እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል።
በዓለም ጤና ድርጅት ዋና የቦርድ አባላት ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት ዋና ኃላፊው፤ በርካታ ሀብታም አገሮች ዓለም አቀፍ የክትባት ክፍፍል ትብብር (ኮቫክስ) አሠራርን መጣሳቸውን ጠቁመዋል።
ኮቫክስ ክትባትን ለዓለም ሕዝብ በፍትሐዊ መንገድ ለማከፋፈል የተመሠረተ የትብብር መድረክ ነው። ኮቫክስ በተለይም ድሀ አገራት ክትባቱን ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ያመቻቻል።
ዶ/ር ቴድሮስ እንዳሉት ሀብታም አገራት የኮቫክስ የክትባት ክፍፍል ሂደትን በመጣስ ለዜጎቻቸው ክትባት እያከማቹ ነው። ይህ ደግሞ ድሀ አገራትን ችግር ውስጥ ይከታል።
"ዓለም እጅግ አስጊ በሆነ የሞራል ውድቀት ጫፍ ላይ ናት። ይህ ውድቀት በድሀ አገሮች የሚኖሩ ሰዎችን ሕይወት የሚቀጥፍና ኑሮንም የሚያከብድ ነው" ብለዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ ባደረጉት ንግግር "ስለ እኩል የክትባት ክፍፍል እየተናገርኩ ቢሆንም እንኳን አንዳንድ አገሮች እና ድርጅቶች ከኮቫክስ ውጪ የሁለትዮሽ ስምምነትን ያስቀድማሉ። ክፍ በመጨመር ከሌሎች አገራት ቀድመው ክትባት ለማግኘት ይሞክራሉ። ይህ ስህተት ነው" ሲሉም ተደምጠዋል።
የክትባት ክፍፍል ፍትሐዊ ካልሆነ ወረርሽኙን ማስወገድ እንደማይችልና በሽታው የሚያሳድረው ሰብአዊ እንዲሁም የምጣኔ ሀብት ቀውስ እንደማይገታ ተናግረዋል።
ሀብታም አገራት 'ቅድሚያ ለኛ' በሚል እየሄዱበት ያለው መንገድ ድሀ አገራትና ዜጎቻቸውን አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚከት ዶ/ር ቴድሮስ አስምረውበታል።
በተያያዥም ይህ አካሄድ ሀብታም አገራትንም ጭምር የሚጠቅም እንዳልሆ አስረድተዋል።
"ይህ እሽቅድድም ወረርሽኙ የሚቆይበትን ጊዜና ጉዳታችንን ያረዝመዋል። የሚጣሉ ገደቦችን እንዳይነሱ፤ ሰብአዊና ምጣኔ ሀብታዊ ቀውሱ እንዳይገታም ያግዳል" ብለዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ "የክትባት ክፍፍል ፍትሐዊ መሆን ያለበት ከሞራል አንጻር ብቻ ሳይሆን ለምጣኔ ሀብት ሲባልም ነው" በማለትም አክለዋል።












