ኮሮናቫይረስ፡ በእንግሊዝ 10 አዳዲስ የኮቪድ-19 ክትባት መስጫ ማዕከላት ሊከፈቱ ነው

የክትባት ማዕከል

የፎቶው ባለመብት, PA Media

እንግሊዝ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ አዳዲስ የኮሮናቫይረስ ክትባት መስጫ ማዕከላትን ልትከፍት እንደሆነ አስታውቃለች።

ይህ የሆነው መንግሥት ከአንድ ወር በኋላ በዩናይትድ ኪንግደም 15 ሚሊዮን ሕዝብ ለመከተብ ያቀደውን ግብ ለማሳካት ነው።

ብላክበርን ካቴድራል እና ቅዱስ ሄለንስ ራግቢ ግራውንድ (ሜዳ) አሁን አገልግሎት እየሰጡ ያሉትን ሰባት ማዕከላት ይቀላቀላሉ።

የእንግሊዝ ብሔራዊ ጤና አገልግሎት [ኤንኤችኤስ] ማዕከላቱ በሳምንት በሺዎች የሚቆጠሩ ክትባቶችን እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በብሔራዊ የክትባት ዘመቻው የተሳተፉትን አመስግነዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም እስካሁን በቫይረሱ ከተያዙት 3.3 ሚሊዮን ሰዎች ቁጥር በላይ ማለትም 3.5 ሚሊዮን ሰዎች ክትባቱን ወስደዋል።

ሆኖም ከተመዘገበው ቁጥር በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች እንደሚኖሩ ይታመናል።

መንግሥት ቁጥራቸው 15 ሚሊዮን ለሚሆኑ፤ ከ70 ዓመት ዕድሜ በላይ ለሆኑ፣ ለበሽታው ተጋላጭ ለሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች እና የእንክብካቤ ማዕከላት ሰራተኞችን በሙሉ በየካቲት ወር አጋማሽ ክትባቱን ለመስጠት ቃል ገብቷል።

በእንግሊዝ ታሪክ ሰፊው በሆነው በዚህ የክትባት መርሃ ግብር ሕዝቡ አረጋዊያንን በመርዳትና በቀጠሯቸው እንዲገኙ በማገዝ ድርሻውን እንዲወጣ መንግሥት አሳስቧል።