ኬ2 ተራራ፡ ኔፓላዊያን የዓለማችን ሁለተኛውን ትልቅ ተራራ በመውጣት አዲስ ክብረወሰን አስመዘገቡ

የኔፓል ተራራ ወጭዎች

የፎቶው ባለመብት, Nimsdai Purja

አስር አባላት ያሉት የኔፓል ተራራ ወጪዎች የዓለማችን ሁለተኛውን ትልቅ ተራራ ወጥቶ በማጠናቀቅ የመጀመሪያ በመሆን አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን አስመዘገቡ።

በርካታ ተራራ ወጪዎች 8ሺህ 611 ሜትር ከፍታ ያለውን ኬ2 ተራራ ወጥቶ ለማጠናቀቅ ተስፋ ሰንቀው ነበር የተነሱት።

ይሁን እንጂ አንድ ስፔናዊ ተራራ ወጪ ተራራውን በመውረድ ላይ ሳለ በመውደቁ ሕይወቱ አልፏል።

ከዓለማችን ትልቁ ተራራ ኤቨረስት በ200 ሜትር ብቻ የሚያንሰው ኬ2 ተራራ፤ በፓኪስታንና ቻይና ድንበር የሚያልፈው ካራኮራም ተራራ አካል ነው።

ኬ2 ከ8 ሺህ ሜትር በላይ ከፍታ ካላቸው 14 ረዥም ተራራዎች አንዱ ነው። በክረምት ወራት ከሁሉም ተራራዎች ተመራጭ እንደሆነም ይታሰባል።

ኬ2 ለረዥም ጊዜ 'አረመኔው ተራራ' በሚል መጠሪያ ይታወቃል። ይህን ስያሜ ያገኘው አሜሪካዊው ተራራ ወጪ ጆርጅ ቤል እአአ በ1953 ተራራውን ለመውጣት ጥረት በሚያደርግበት ጊዜ ከተናገረው የተወሰደ ነው።

ጆርጅ "አንተን መግደል የሚፈልግ አረመኔ ተራራ ነው" ሲል ነበር በወቅቱ የተናገረው።

በ2008 አስራ አንድ ተራራ ወጪዎች በዚሁ ተራራ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ኔፓላዊያን ተራራ ወጪዎች 60 ሰዎችን ከያዘው ከሦስት ወይም ከአራት ተወዳዳሪ ቡድን ጋር ተበታትነው ነበር ተራራውን መውጣት የጀመሩት።

በኋላ ላይ ግን አስሩ ኔፓላዊያን ታሪካዊውን ድል በኔፓል ስም ለማስመዝገብ በማለም አንድ ቡድን በመመስረት ተራራውን ወጥተው ማጠናቀቅ ችለዋል።

ተራራ ወጪው ኒርማል ፑርጃ ያስመዘገቡትን ድል አስመልክቶ " የታሪኩ አካል በመሆናችን ኮርተናል፤ ትብብር፣ የቡድን ሥራ እና ቀና አመለካካት የማይቻል የሚመስልን ነገር ለመቻል እንደሚረዱ ለማሳየት ችለናል። " ብሏል።

ይህን ተራራ ለመውጣት እአአ1987 እስከ 1988 በክረምት ወራት በቡድን በመሆን በርካታ ሙከራዎች የተደረጉ ሲሆን፤ እስካሁን ግን ከ7ሺህ 650 ከፍታ በላይ መውጣት የቻለ የለም።