ሙዚቃ፡ ታዋቂው አሜሪካዊ ራፐር ዶ/ር ድሬ አገግሞ ከሆስፒታል ወጥቷል ተባለ

ዶ/ር ድሬ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታዋቂው አሜሪካዊ ራፐርና ፕሮዲዩሰር ዶ/ር ድሬ በአንጎል የደም ቧንቧ ችግር ሆስፒታል ገብቶ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት አገግሞ ወደ ቤቱ ተመልሷል ተብሏል።

የ55ቱ አመት ራፐር ጠበቃ በትናንትናው ዕለት እንዳሳወቁት ሙዚቀኛው ወደ ቤቱ ተመልሷል ከማለት ውጭ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ከቀናት በፊትም ራፐርና ተዋናዩ አይስቲ ከዶ/ር ድሬ ጋር እንዳወራና " ደህና ነው" በማለት በተሻለ ሁኔታ እንደሚገኝ ተናግሮ ነበር።

መረጃዎችን ፈልፍሎ በማውጣት የሚታወቀው ቲኤምዚ ራፐሩ ከሁለት ሳምንታት በፊት ራፐሩ ሎስ አንጀለስ፣ ካሊፎርኒያ በሚገኝ ሴዳርስ ሲናይ ሜዲካል ማዕከል ተወስዷል ብሎ ነበር።

በዚያኑ ወቅትም የራፐሩ ተወካዮች ባወጡት መግለጫ በመድረክ ስሙ ዶ/ር ድሬ ተብሎ የሚታወቀው አንድሬ ሮሜል ያንግ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

"ለቤተሰቦቼ፣ ጓደኞቼና አድናቂዎቼ ለመልካም ምኞታቸው ምስጋና ይድረሳቸው። በጣም ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለሁት። ከህክምና ቡድኑም ጥሩ እንክብካቤ እያገኘሁ ነው" በማለት ራፐሩ በኢንስታግራም ገፁ መልዕክቱን ማስተላለፉ የሚታወስ ነው።

"በቅርቡ ከሆስፒታል ወጥቼ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ። በሴዳርስ ለሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች በሙሉ ከፍተኛ ምስጋና ይድረሳቸው። ፍቅር ለሁላችንም" የሚል መልዕክት አስተላልፎ ነበር።

የ Instagram ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን Instagram ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በInstagram. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የInstagram ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ Instagram ይዘት መጨረሻ

ራፐሩ ታሞ ሆስፒታል መግባቱ ከተሰማ በኋላ ጓደኞቹ እንዲሁም ዝነኛ ሰዎች ከህመሙ እንዲያገግም መልካም ምኞቻውን ገልፀዋል።

በ1980ዎቹ ኤንደብልዩኤ (NWA) ተብሎ በሚታወቀው ታዋቂው ባንድ ውስጥ ከዶ/ር ድሬ ጋር አብሮ የነበረው የባንዱ አባል አይስ ኪዩብ "ለጓደኛዬ ዶ/ር ድሬ ከህመሙ እንዲያገግም በፀሎትና በፍቅር እያሰብኩት ነው" በማለት በትዊተር ገፁ ላይ አስፍሮ ነበር።

ለሙዚቃ ህይወቱ ከፍተኛ ሚና የተጫወተለት ሌላኛው ታዋቂው ራፐር ስኑፕ ዶግ እንዲሁ "እንዲሻልህ እመኛለሁ፤ ታስፈልገናለህ ቤተሰባችን" ብሎ ነበር።

ሌላኛዋ ታዋቂ ራፐር ሚሲ ኤሊየት እንዲሁ ራፐሩ በጥንካሬና በጤንነት እንዲመለስ ምኞታቸውን ከገለፁት መካከል አንዷ ናት።

በሂፕሆፕ ሙዚቃ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ራፐሩ ኤንደብልዩኤ (NWA) በሚባለው የሂፕ ሆፕ ቡድን፣ በግሉም የነበረው የሙዚቃ ህይወቱ ዝናን አትርፏል።

ከዚህም በተጨማሪ በፕሮዲውሰርነቱም ከፍተኛ ዝናን መጎናፀፍ የቻሉ እንደ 50 ሴንት፣ ኬንድሪክ ላማርና ኤሚኒየም የመሳሳሉ ሙዚቀኞች ጀርባ አሻራውን አሳርፏል።