"ሳሊን ፍለጋ"- የዚያ ትውልድ አሻራ ሲገለጥ

የሳሊ ፖስተር

የፎቶው ባለመብት, tamara mariam dawit

አራት ሴቶች መስዋዕትነት በተከፈለባት በአሲምባ ኮረብታ ላይ ጮክ ብለው ይጣራሉ።

"ሳሊ፣ ሳሊ፣ ሳሊ፤ ሰላማዊት" - ድምፃቸው በተራራው መካከል ይሰማል።

የገደል ማሚቶው ድምፅም ሳሊ፣ ሰላማዊት እያለ በከፍተኛ ድምፅ ያስተጋባዋል። ተራራውም ስሟን መልሶ የሚጣራ ይመስላል።

እነዚህ ሴቶች ማን ናቸው? ስሟን የሚጠሯትስ ሳሊ ወይም ሰላማዊትስ?

በእድሜ ጠና ያሉት እነዚህ ሴቶች ክብረ፣ መንቢ፣ ብሩክታዊትና ፅዮን ናቸው። የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓን) የትጥቅ ትግል ተቀላቅላ ከአርባ አመት በፊት የጠፋችው እህታቸውን ሳሊ (ሰላማዊት ዳዊትን) ስም ነው የሚጠሩት።

ከአስርታት በፊት አቆላምጠው እንደሚጠሯት ሳሊ፣ ሳሊ፤ ሰላማዊት ይላሉ።

ትግራይ ውስጥ የምትገኘው የአሲምባ ተራራ የወጣቶቹ የፅናትና ቆራጥነት ተምሳሌት፣ የአኬልዳማ መሬት፤ የህልም መነሻና መቀበሪያ፤ ታጋዮችን ውጣ ያስቀረች።

"ቢወቀጥ አጥንቴ ቢንቆረቆር ደሜ፤ ለአዲስ ሥርዓት ልምላሜ፤ ፍጹም ነው እምነቴ፤ ትግሉ ነው ሕይወቴ" ብሎ ያ ትውልድ የዘመረባት ቦታ ናት።

የአሲምባዋ ታጋይ ሳሊ የሕዝብን ትግል ትግሌ ብላ፣ ለሕዝብ የማንነት ጥያቄ ምላሽ፣ በጭቆና ለሚማቅቀው የነፃነትን ወጋገን ለማሳየት፣ በእራፊ ጨርቅ እጦት፣ በድህነት አለንጋ ለሚገረፈው፣ ጉርሱን ላጣው የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በቤታቸው በወጡበት ካልተመለሱት መካከል አንዷ ናት።

በዚህች ተራራማ ስፍራ መሸገው የነበሩ የዚያ ትውልድ የኢሕአፓ አባላትም በመንፈስ እየሰሙ ይሆናል - የእህትማማቾቹን ጥሪ።

ከአራት አስርት ዓመታት በኋላ በአሲምባ ተራራ ስር ያለችው የገጠር መንደር፣ በድንጋይ የተሰሩ ህድሞ ቤቶች፣ ጋቢያቸውን ደረብ አድርገው የሚመለከቱ አዛውንት፣ ነጠላቸውን የደረቡ እናቶች፣ በአቧራማው ሜዳ ላይ ኳስ የሚጫወቱ ህፃናትም የሳሊንና የሌሎቹን መስዋዕትነት ያወሱት ይሆን?

ለነፃነት ቆርጣ በረሃ የገባችው ሳሊ (ሰላማዊት) ፈገግታ የማይለያትና 'ቀይዋ' በሚል መለዮ ነበር የአካባቢው ነዋሪዎች የሚያውቋት።

ልክ እንደ ኢሕአፓ ጓዶቿ ፖለቲካዊ ትምህርት ከመስጠትም ባለፈ ለሴቶች ድጋፍ በማድረግ የታመሙትን በማከም 'ነርሷ' የሚል የቅፅል ስምም አትርፋ ነበር።

ለቤተሰቦቿስ? ሳሊ ፈገግታ የማይለያት፣ ሳቂታ፣ ለመቅረብ ቀለል ያለች፣ በጣም ጎበዝ፣ ውይይት የምትወድ፣ ፓርቲ የምታዘወትር፤ ፀጉሯንና ጥፍሯን ተሰርታም ዝንጥ ብላ መውጣትም ትወድ ነበረች። ይህ ግን ትግሉን ከመቀላቀሏ በፊት ነበር። ትግሉን ከተቀላቀለች በኋላስ?

የፀረ-ኢምፔሪያሊዝም አቋሟ፣ የማኅበራዊ ፍትህ ጥያቄዋ፣ ደርግን እጥላለሁ ብላ ወደ ትጥቅ ትግል መግባቷ በቤተሰቡ ውስጥ የሚወራም አይደለም፤ ተዳፍኖ የቀረና የማይነሳ ጉዳይ ነው።

የሳሊ ደብዛ መጥፋት ለቤተሰቧ ጠልቆ የሚሰማ ህመም ያለው የማይድን ቁስል ነው። የእህታቸውን ትዝታ ተመልሶ መፈለግ የማይሽር የዘመን ጠባሳ መመልከትና በርካቶች መስማት የማይፈልጉትን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የጨለማ ጊዜንም መመልከት ነው።

ስለዚህ ትግሉም አይነሳም፤ ሳሊም አትወሳም። ለቤተሰቡ ህመም የሆነው የሳሊ የትግል ታሪክም መቀበር ለወንድሟ ልጅ ታማራ ማርያም ዳዊት፤ ሳሊ የምትባል አክስት እንደነበረቻት ይቅርና እስከነ መፈጠሯ እንዳታውቅ ምክንያት የሆናት።

በ30ዎቹም እድሜ ላይ ሆና ነው ሳሊ (ሰላማዊት) የምትባል አክስት እንዳለቻት፣ የኢህአፓ ታጋይ እንደነበረች የተረዳችው።

የአክስቷን ታሪክ፣ ማንነት ፍለጋ በዝምታ የተሸበበውን የቤተሰቡን ምስጢራዊ መጋረጃንም 'ፋይንዲንግ ሳሊ' [ሳሊን ፍለጋ] በሚለው ፊልሟ ታሳያለች።

ካናዳ ተወልዳ ያደገችው ታማራ ስለ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከስልጣን መገርሰስ፣ የተማሪዎች እንቅስቃሴ፣ የቀይ ሽብር ጭፍጨፋዎች ብትሰማም ከእሷ ቤተሰብ ጋር ግንኙነት አለውም ብላ አልጠረጠችም።

ነገር ግን ይህ ሁሉ የተቀየረው ከዘጠኝ ወይም ከአስር ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ለእረፍት በመጣችበትና የአንዲት ወጣት ሴት ትልቅ ፎቶ አያቷ ቤት ተሰቅሎ በተመለከተችበት ወቅት ነው።

በበርካታ ኢትዮጵያውያን ቤተሰብ ውስጥ የአጎት ልጅ፣ የአክስት ልጅ እንዲሁም ዘመድ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ማደግ የተለመደ ነው።

አያቶቿም የሚያስተምሯቸው አምስት ወይም ስድስት የቤተሰብ አባላት ነበሩ። ስታድግም የማታውቃቸው የድሮ ፎቶዎችም ታይ ነበር።

የማታውቀው ሰው ፎቶ ማየቷ ብዙ ባያስገርማትም ነገር ግን አያቷ ቤት የተሰቀለው ፎቶ ትልቅና ሳሎን ቤቱ መሃል ላይ መሆኑ ነበር ጥያቄ ያጫረባት።

ፎቶው ላይ ያለችው ማን ናት? ብላም አያቷን ስትጠይቅ "እንዴ ማን እንደሆነች አታውቂም? አክስትሽ ናት እኮ አሏት" አያቷ።

አክስት ሲባል ምናልባት ዘመድ ትሆናለች ወይ በማደጎ የመጣችም ትሆናለች ብላም አስባ ነበር።

"አያቴንም ስለነበር የጠየቅኳት ማን መሆኗን አለማወቄ በጣም ነው ያስደነገጣት፤ ሳሊ የምትባል ሰው በህይወት መፈጠሯንም አለማወቄ በጣምም ነው ያስገረማት" ትላለች ታማራ ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ።

ታማራ ስለ ሳሊ ማንነት፣ ለአገሯ ያደረገችውንም ተጋድሎና ታሪክ አላወቀችም ማለት መጪው ትውልድ ስለሷ ምንም አያውቅም ማለት ነው።

ይሄ ደግሞ የቤተሰቡም ሆነ የኢትዮጵያ ታሪክ አካል ነው፤ መጥፋት እንዲሁም ከታሪክ መዛግብት መፋቅ ማለት እንደሆነም ተረዳች።

ከሁሉ በላይ ግን ለታማራ የገረማት፤ ለምንድን ነው ቤተሰቡ ስለ ሳሊ ማውራት የማይፈልገው? ማስታወስስ ለምን አይፈልግም? የሚለው ነው።

ታማራ አባቷ ኢትዮጵያዊ ሲሆን እናቷ ደግሞ ካናዳዊት ነጭ ናት። ከእናቷ ጋር ስላደገችና ከአባቷም ጋር የነበራት ቅርበት የተወሰነ በመሆኑም ይሆናል ስለ ሳሊ የማላውቀው የሚል ግምት አላት።

ሆኖም ከኢትዮጵያዊ ቤተሰቦቻቸው ጋር በቅርበት ያደጉት የአክስትና የአጎት ልጆች የሚያውቁትም በጣም ትንሽ ነው።

ህይወቷ ምን እንደነበር? ስለተሳተፈችበት ትግልም ምንም አይነት መረጃ አልነበራቸውም።

በቅርቡም ለሰራችው 'ፋይንዲንግ ሳሊ' ለሚለው ጥናታዊ ፊልሟም መነሻ የሆናት ይኸው አጋጣሚ ነው። አያቷን፣ አክስቶቿን እንዲሁም የሳሊን ጓደኞችና ጓዶቿን ወደ ኋላ አራት አስርት ዓመታት እንዲጓዙ ታደርጋቸዋለች።

ለዓመታት በዝምታ ተሸብቦ የነበረው ዝምታና ምስጢርም ይገለጣል። 'ፋይንዲንግ ሳሊ' የአገሪቱን ህመም፣ ያልሻረ ቁስል ቤተሰብ፣ ፍቅር፣ የተዳፈኑ ታሪኮች፣ ያልሻራ ጠባሳን ፍንትው አድርጎ ያሳያል።

በአያቷ እንዲሁም በአክስቶቿ ላይ ቀይ ሽብር ያሳረፈው ጠባሳ ምን ያህል እንዳልሻረ ፊልሙ ያሳያል። ታሪክን የኋሊት በመመለስም በወቅቱ የነበረችውን ኢትዮጵያ ለመመልከት ሞክራለች- ታማራ።

'ፋይንዲንግ ሳሊ'፣ አክስቷን የመፈለግ ጉዞ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን የኋላ ታሪክና በአሁን ጊዜ ያጠላውን ጥላም ያሳያል።

ፊልሙ ሲጀምር በእድሜ የጠገቡ አዛውንት ከመኪና ወጥተው በእድሜ እኩያቸው የሆኑ ሌላ አዛውንትን ለማግኘት ወደ ቤታቸው ሲራመዱ ነው።

የእድሜ ባለፀጋዋ ውጭ እየጠበቋቸው ነበር። ተቃቀፉ፣ ጉንጭ ለጉንጭም ተሳሳሙ። እጃቸውንም ተጨባብጠው ተላቀሱ። ወደ ቤትም እየተራመዱ የቀድሞው አልፏል በመባባል ይፅናናሉ።

ሁለቱ አዛውንቶች የሳሊ [ሰላማዊት] እና የኢሕአፓ አመራር የነበረው ፀሎተ ህዝቅያስ እናት ናቸው። ሁለቱም ልጆቻቸውን በትግሉ መስዋዕት አድርገዋል።

የፀሎተ እናት ለአንድ ወር ያህል ታስረው ልጃቸው ሲሰቃይም እንዲመለከቱ ተገደዋል። ሦስት ልጆቻቸውንም በአብዮቱ አጥተዋል።

ሐዘኑ፣ ፀፀቱ፣ ቁጭቱ የፈጠረው ዘመን ያልሻረው ህመምም ይነበብባቸዋል። በርካታ ያልተወሩ፣ ያልተነገሩ ህመሞች በሁለቱ አዛውንት እንባ ውስጥ አለ።

"ስንቱ አልፎ እዚህ ደረስን" እያሉ ይጫወታሉ። የሁለቱ እናቶች ብቻ ሳይሆን እህቶቿን የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር ሁሉም ማጣትን ያውቁታል።

የሚወዱት ሰው ዝም ብሎ ደብዛው ሲጠፋ ምንስ ይደረጋል? በትግል እንደወጡ የቀሩ፣ በቀይ ሽብር የተነጠቁት ሁሉ ሐዘናቸውን በውስጣቸው ደብቀው፣ በፍራቻ ተሸብበው፣ ከባድ ሸክም ተሸክመው ለመኖር ተገደዋል።

ከቤተሰቧ ጋር መቆራረጧ በተለይም ልባቸውን ምን ያህል እንደሰበረውም 'ፋይንዲንግ ሳሊ' በሰላማዊት አድርጎ የዚያን ትውልድ ህይወት በር ያንኳኳል።

ሳሊ ማን ናት?

ሳሊ የዲፕሎማት ልጅ ናት፣ ከላይኛው መደብ የሚመደቡ የሃብታም ልጅ ። አባቷ በአፄ ኃይለ ሥላሴ አገዛዝ ወቅት አምባሳደር ስለነበሩ ሳሊም ሆነ ሌሎች እህቶቿ አዲስ አበባ ቢወለዱም አባትየው በተመደቡባቸው በሌሎች አገራት ነበር ያደጉት።

ሳሊም ሆነ ቤተሰቡ በናይጄሪያ፣ በጋና፣ በሱዳንና በሌሎችም አገራት ውስጥ ኖረዋል። ወደ ካናዳም የመጡት በ1968 (እአአ) ነበር። በካናዳ፣ ካርልተን ዩኒቨርስቲ የፖለቲካና የሶሺዮሎጂ ትምህርትን አጥንታለች።

ሳቂታ፣ ሙዚቃ የምትወድ፣ በርካታ ጓደኞች ያሏት ነበረች። ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቷም በፊት ኑሮዋ በካናዳ ነበር።

አባቷ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ማደጎ ልጅና ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ ነበሩ። በተደጋጋሚም "ውጭ አገር የምንኖረው ለኢትዮጵያ መንግሥት እየሰራን ስለሆነ ነው። ኢትዮጵያንም ወክለን ነው። መመለስ አለባችሁ፤ አገራችሁንም ልታውቁ ይገባል" የሚል ፅኑ አቋም እንደነበራቸው ታማራ ለቢቢሲ ተናግራለች።

"መመለስ ብቻ አይደለም ለአገራችሁም ልትሰሩ ይገባል ይሉ ነበር። ምናልባትም አብዮቱ ባይፈጠር ኖሮ ሁሉም ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ያገለግሉ ነበር" ትላለች ታማራ።

ኢትዮጵያ የመጣችው በ1973 (እአአ) ነበር። ወቅቱም የሽግግር ጊዜ ወቅት ነበር። ሥነ ጽሁፉ፣ ሙዚቃው፤ የምሽት ክበቡ፣ የዘመናዊነት (ሞደርኒዝም) ፅንሰ ሃሳብ የጎለበተበት፣ ከተሜነት የሚቀነቀንባትና ድምቅ ወዳለችው አዲስ አበባ።

ጎን ለጎንም እንዲሁ ሰልፉ፣ ተቃውሞውና ውጥረት የነገሰበት ዘመን። ወቅቱ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በተለያዩ አገራት ያሉ ትግሎች የተጋጋሉበት ነበር። የዓለም ዓቀፉ ፀረ- ኢምፔሪያሊዝም፣ ፀረ-ቅኝ ግዛት እንዲሁም የፀረ ዘረኝነት ትግሎችም ጎን ለጎን ነበሩ።

አሜሪካ በቬትናም ላይ ያደረገችውን ወረራን በመቃወም፣ የፍልስጥኤም ጥያቄ፣ የደቡብ አፍሪካ የፀረ- አፓርታይድ ትግልና በላቲን አሜሪካ ለነፃነት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችም የእነ ሳሊም ጥያቄዎች ነበሩ። ለምሳሌ በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር ልሳን ከነበረው 'ታጠቅ' ላይ የሚከተለው ፅሁፍ ሰፍሮ ነበር።

"በፊውዳሊዝም እና በኢምፔሪያሊዝም መቃብር ላይ የሁላችን የሆነች ሕዝባዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት ኢትዮጵያውያን የሆንን ሁሉ እፍኝ ከማይሞሉት ጨቋኞችና ደጋፊዎቻቸው በቀር በአንድ የትግል ግንባር ውስጥ ተሰብስበንና ተደራጅተን በአንድነት መራመድ አለብን" ይላል።

ካናዳ በነበረችበት ወቅት ማኅበራዊ ፍትህ ላይ ትሰራ የነበረችው ሳሊ አዲስ አበባ ስትደርስ "ፋኖ ተሰማራ ፋኖ ተሰማራ፣ ፋኖ ጫካ ግባ ትግሉን ልትመራ፤ እንደ ሆቺሚኒ እንደ ቼ ጉቬራ" በአዲስ አበባ መንገዶች የሚሰማበት፤ የአብዮት ታሪኮች በወጣቱ ልብ የተቀጣጠሉበት ጊዜ ነበር የተቀበላት።

የተንሰራፋው ሥራ አጥነት፣ ረሃብ እንዲሁም ኢ-ፍትሃዊነት መስፈን "መሬት፣ መሬት፣ መሬት ላራሹ፣ ተዋጉለት አትሽሹ" በሚሉ መፈክሮችም፣ ሰላማዊ ሰልፎችና የሥራ ማቆም አድማዎች መካከል ሥርዓቱ ሲንገዳገድ ነበር የመጣችው።

ኢትዮጵያ መጣች፤ አልተመለሰችም። እንደወጣች ቀረች፤ አብዮቱን ተቀላቀለች። የ23 ዓመቷ ሳሊ በነፋስ ስልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስተማር ጀመረች።

በርካታ የተማሪዎች እንቅስቃሴ አራማጆችን በኋላም የኢሕአፓ መስራቾች ጋር መገናኘት ጀመረች።

በጥቂት ወራትም ውስጥ ሳሊ ህይወቷ ከስር መሰረቱ ተቀየረ።

ፓርቲ ለፓርቲ የምትሄደው፣ ዝንጥ ብላ ሽቶ የምትቀባባው ሳሊ ኮሚዩኒስት ሆነች። ወደ ትግሉ ዓለም ስምጥ ብላ ገባች። አለባበሷ፣ ሁሉ ነገሯ ተቀየረ።

ፊልሙ ለቤተሰቧ የፖለቲካ ህይወቷ እንዴት ሊዋጥላቸው እንዳልቻለ፣ ሁሉን ነገር መስዋዕት ማድረጓ፣ ከቤተሰቧም በላይ ለፖርቲው የነበራት ታማኝነትና ለለውጥ የነበራት ቁርጠኝነትን ያሳያል።

የእሷም የሆነ የትውልዱ መፈክር "እዋጋለሁኝ ለመብቴ ላንገብጋቢው የእግር እሳቴ፤ የትግል መርህ ቅኝቴ ትግል ነውና ህይወቴ" የሚል ነበር።

በተለይም በ20ዎቹ መጀመሪያ የነበረችው ሳሊ የኢሕአፓ አመራር ከነበረው ፀሎተ ህዝቅያስ ጋር ሊጋቡ መሆኑን ሲያውቁ ቤተሰቡን ግራ እንደተጋባ ፊልሙም ሆነ ታማራ ትናገራለች።

በትልቅ ሠርግና ድል ባለ ድግስ ታገባለች ብለው ሲጠብቁ አነስ ባለ የምሳ ሥነ ሥርዓት ነበር ጋብቻቸው የተፈጸመው። የለበሰችውም ሱሪ ነበር። እንደተጠበቀው ትልቅ የኢትዮጵያ ባህላዊ ሠርግም አልነበረም።

ፊልሙም ሳሊ የኢሕአፓ አመራር ከነበሩት መካከል አንዱ ከሆነው ፀሎተ ህዝቅያስ ጋርም የነበራቸውን ጥልቅ ፍቅርን ያሳያል።

ለእህቶቿም ይህቺ ሳሊ ናት ብሎ መቀበል ቀላል አልነበረም። ከቤተሰቡ ጋር የነበራትንም ግንኙነት መቀነስ ነበረባት።

በተለይም አቃቂ በነበረ የሴቶች ምርቃት ላይ ያደረገችው ንግግር መንግሥትን የሚተችና የሚያወግዝም ስለነበር በመንግሥት ጠላት ተብላ ለመፈረጅ ጊዜም አልወሰደባትም።

በከተማ ትግል ብቻ አልተወሰነችም አሲምባ የትጥቅ ትግል ለማድረግ ገብታ ጠፋች - እንደወጣች ቀረች። ፀሎተ ህዝቅያስም እንዲሁ።

ለዓመታትም ያህል ቤተሰቦቿ በአውሮፓ፣ በተለያዩ አፍሪካ አገራትና በአሜሪካም ፈለጓት። አለችበት የተባለበት ቦታ ሁሉ ፎቶዋን እያሳዩም ዱካውን፣ ጥላዋን ተከታተሉ፤ አላገኟትም።

የሳሊ የትግል ህይወት

የሳሊ የትግል ህይወት ለቤተሰቡ ድብቅ ነበር። ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታም ግንኙነቷን አቋርጣም ስለነበር ታማራ ከትግል ጓዶቿ በተለይም ከፍቅርተ ጋር በማውራት ነው የትግል ህይወቷን ለማወቅ የቻለችው።

በተለይም ከ1975 (እአአ) በኋላም ድብቅ ህይወት ነበራት። ከአንዲት እህቷ ጋር ብቻ የተወሰነ ግንኙነት ነበራት። አሲምባም እያለችም ሁለት ደብዳቤ ፅፋለች።

አዲስ አበባም በድብቅ ሬድዮ፣ ገንዘብና የኢሕአፓን አቋም የሚያስተጋቡ መፈክሮች፣ በራሪ ወረቀቶችና መረጃዎች ታዘዋውር ነበር።

ለታማራ ያስደነቃትና ከአያቷ የሰማችው ነገር ቢኖር ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምን ለመግደል በተጠነሰሰው ሴራ ውስጥ አንዷ መሆኗ፤ ከዚህም በተጨማሪ የቦሌ አየር ማረፊያን ለማፈንዳትም በነበረው ሙከራም እንዲሁ መሳተፏ ነው።

"ምስጢራዊ የሆኑ በራሪ ወረቀቶችን ማሰራጨትም ሆነ ሌሎች ተግባራት እንዳሉ ሆነው በዚህ መንገድ በትጥቅ ትግሉ ተሳታፊ መሆኗ ለእኔ አስገራሚ ነበር" ትላለች ታማራ።

በተለይም በቦሌ አየር ማረፊያ ውስጥ የፍንዳታ ጥቃት ሙከራ ጋር ተያይዞ የደርግ መንግሥት በጥብቅ ከሚፈልጋቸው አንዷ ነበረች።

በወቅቱ አሜሪካ የምትኖረውም አክስቷ በፖስታ ሳጥኗ ደብዳቤ ደረሳት። ሳሊ መንግሥት በሞትም ይሁን በህይወት ከሚፈለጋቸው ሰዎች ዝርዝር ውስጥ መካተቷን የሚጠቅስ ነበር።

መረጃውም እንደሚያሳየው ፀረ- አብዮተኛ ተብላ የተፈረጀችው ሳሊ ቦሌ አየር ማረፊያን ለማፈንዳት ሙከራ አድርጋለች ይላል። ይህችው እህቷም ከዚህ ቀደም አርቲፊሻል ፀጉር፣ የቀዶ ጥገና መቀስ ልካላት ነበር።

ታማራ ሳሊ ስለነበራት ተሳትፎም በዝርዝር ለማጣራት ባደረገችው ሙከራ፤ 'የአሲምባ ፍቅር' የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ ካሕሳይ አብርሃ ብስራት (አማኑኤል ማንጁስ)ን ጠይቃለች።

ካህሳይ በተወሰነ መልኩ ከሳሊ የሰማውን መንግሥቱን ለመግደል ያለመውን ሙከራም ነግሯታል። ከዚህም በተጨማሪ ከሳሊ ጋር በአንድ ህዋስ ውስጥ የነበረውና የፀሎተ ታናሽ ወንድም የተገደለውም መንግሥቱን ለመግደል ካልተሳካው ሙከራ ጋር ተያይዞም እንደሆነም ሰምታለች።

በኢሕአፓ ውስጥ መረጃዎች ሲተላለፉ የነበሩት በከፍተኛ ምስጢር በመሆኑ እንዲሁም ይህንንም የሚያውቁት በውጭ አገራት ያሉና አንዳንዶቹም ለመናገር ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ስለ ሳሊ ተሳትፎ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ የላትም።

ከካህሳይ በተጨማሪ ስለ ሳሊ የሰማችው አሲምባ ሆና እንደ 'ፐብሊክ ዲፌንደር'፣ ጠበቃ ወይም የህግ ባለሙያ መቅጠር ለማይችሉ ሰዎች በመቆምታገለግል ነበር።

ለኢሕአፓም ሆነ ለፓርቲው ወታደራዊ ክንፍ ለሆነው ጦር የሚያስፈልገውን የፍርድ ሂደት ለማከናወን ፍርድ ቤትም ተቋቁሞ ነበር። ይሄም ጉዳይ በአሲምባ ፍቅር ውስጥ ተካቷል።

ፊልም ሰሪዋ ታማራ

የፎቶው ባለመብት, tamara mariam dawit

በዝምታ የተሸበበ ታሪክ

የሳሊ ቤተሰቦች ዝምታ በዘመኑ የደረሱ በደሎችና ግፎች ነፀብራቅ ናቸው።

የኢትዮጵያን ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሁኔታዎችን ያጠኑ ሰዎች ድብቅነቱ፣ በዝምታ መሸበቡ የአንድ ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን የአጠቃላይ የህዝቡ ፍራቻ መገለጫም እንደሆነ ይናገራሉ።

ኢትዮጵያን ለዘመናት የገዟት መንግሥታት በጠመንጃ ኃይል አገሪቷን እንደ ሰም አቅልጠው፣ ህዝቡን በጭቆና በመግዛታቸው መንግሥት የሚለው ቃል የሚፈራ ኃይል ከሚለው ጋር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ትርጉም እንዲሰጠው ሆኗል።

ለምሳሌ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተደባብሶና በጀግንነት ስም ተለውሶ የሚነገሩ የጭካኔ ታሪኮችን ማንሳት ይቻላል።

በ1950ዎቹ ከሚታወቁት የፊውዳል ገዥዎች መካከል ጃራ ተብሎ የሚታወቀው የራስ መስፍን ልጅ በጭሰኛ ገበሬዎች የሽጉጥ ኢላማ መለማመዱ 'በጀግንነቱ፣ በወንድነቱ እንዲሁም በአልሞ ተኳሸነቱ' እንዲሞካሽ አድርጎታል። መሳፍንቱንና ነገስታቱን እንደ አምላክ ማየትና መፍራት የጭቁኑ አርሶ አደር እውነታ ነበር።

ከአፄ ኃይለ ስላሴ መገርሰስ በኋላ ስልጣኑን የተቆጣጠረው ደርግም ከጠመንጃ አስተዳደር ባለመውጣቱ እንዲሁም የተከሰተው እልቂት ሽብር አነገሰ። ፍራቻው ዝምታም እንደ ሃገር፣ እንደ ህዝብ፣ የያንዳንዱ ቤተሰብም መገለጫ ሆነ።

የደርግ መንግሥትም "የፍየል ወጠጤ ልቡ ያበጠበት፤ እንዋጋ ብሎ ለነብር ላከበት፤ የማትረባ ፍየል ዘጠኝ ትወልዳለች ልጆቿም ያልቃሉ እሷም ትሞታለች" እንደሚለው ተረቱ ወጣቱን"የፍየል ወጠጤ" በማለት በመፈረጅ፣ ግድያዎች፣ ጭፍጨፋዎች ቀጠሉ።

መንግሥት "የአብዮቱ ጠላቶች' በሚላቸው ብቻ ሳይሆን፤ በሕዝቡም ዘንድ እርስ በርስ መፈራራት፣ መጠራጠርን አነገሰ። ቤተሰብ እርስ በርስ የማይተማመንበት ወቅት፤ እርስ በርስ መጠቋቋምና ማኅበራዊ ትስስሮችም ላሉ።

የቤት ለቤት አሰሳው ተጠናከረ፤ 'አብዮት ይፋፋምብን' የሚሉ ጽሁፎች የተለጠፈባቸው በወጣቶች ላይ የሚፈጸሙ የመንገድ ላይ ግድያዎች ተበራከቱ። የአብዮቱ ጠላቶች ተብለው ለተገደሉት ማዘን፣ እርም ማውጣትም የተከለከለ ነበር።

ይባስ ብሎ ቤተሰቦቻቸው ለተገደሉባቸው የጥይት ዋጋ መክፈል፣ እንዲሁም ድጋፋቸውን ማሳየት ነበረባቸው። በርካቶች በዝምታ ተዋጡ፤ ፍራቻም ነገሰ፤ ይህም ለትውልድ ተረፈ።

ታማራም በፊልሟ በርካታ ሰዎች የተገደሉባቸውን ቪዲዮዎችን እያሳየች ለዘመናት ሐዘናቸውን በውስጣቸው ደብቀው የፈጠረውን ስሜትም አጋርታለች።

በባህሉ ውስጥ ያለው ዝምታና ምስጢራዊነት በሳሊ ወይም በሰላማዊት ዙሪያ ባለው በቤተሰብ የሚታየውም በአብዛኛው ቤተሰብ ውስጥም የሚንፀባረቅ ነው።

"አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እንደ ሳሊ ወይም ሰላማዊት አይነት ተመሳሳይ ታሪክ ይኖረዋል። የሞተ፣ የተደበቀ፣ የተንገላታ ወይም ስቃይ የደረሰበት እንዲሁም ሌላ፣ ሌላ አይነት የተደበቀና የማይነገር የቤተሰብ ታሪክ አለ። ራሳቸውም ላይ ቢደርስ ከፍተኛ ህመም ስላለው በርካቶች ከምስጢሩ ጋር መሰቃየትን ይመርጣሉ፤ ታሪኩን መናገር አይፈልጉም" ትላለች ታማራ።

ይህ ሁኔታ በቤተሰብ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ "እንደ አገር በጉዳዩ ላይ ከመወያየት በአማራጩ ዝምታን የመረጠ ሕዝብ ነው። ቤተሰቦች ከልጆች ጋር፣ ትምህርት ቤቶችም አይወያዩበትም። እናም ይሄ ህመም ያድጋል፤ ለአገሪቱም በጣም ትልቅ ችግር ነው" በማለትም ታማራ ታሪክን ወደኋላ በመመልከት ምንስ መማር ይቻላል? የሚለውንም አንገብጋቢ ጥያቄ ታነሳለች።

አክስቷን ለማግኘት በምታደርገው ሙከራም በወቅቱ የተፈጠሩት ሁኔታዎች ላይ ውይይት እንዲኖር፤ መግባባት እንዲፈጠር፤ በአገር ደረጃም ሕዝቡ ከህመሙ እንዲድንም ለማድረግ ፊልሙን ሰርታለች።

በመቶ ሺዎች ባለቁበትም በዚህ ጭፍጨፋ ኢትዮጵያውያንን አስደንግጦ በዝምታ የሸበባቸውም የሳሊ ቤተሰቦች እውነታ የአገሪቱንም እውነታ ያንፀባርቃል። ሳሊን ፍለጋ የእናቷን ናፍቆት፣ የእህቶቿ ህይወትና የሳሊ መጉደል የፈጠረው ክፍተት፣ የዘመን አሻራን ያስቃኛል።

ከቤተሰቡ የተገኙ የቀድሞ ፎቶዎች፣ ቪዲዮዎች፣ አዲስ አበባ በወቅቱ ምን ትመስል ነበር? ለሚለውም 'ፋይንዲንግ ሳሊ' ምላሽ አለው። ማን ናት ሳሊ? ሳሊ እንዴት አብዮተኛ ሆነች የሚለው በቀይ ሽብርና በዚያን ወቅት አብዮትና ትግል ህይወታቸውን ያጡ የመቶ ሺዎችም ታሪክ ነው።

ታማራ ዳዊት ኢትዮጵያዊ ካናዳዊ የፊልም ባለሙያ ናት፤ በርካታ ሙዚቃዎችን፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ፕሮዲውስ አድርጋለች፤ ለምሳሌም ያህል ለሲቢሲ፣ ለብራቮ፣ ለኤምቲቪ፣ ለሬድዮ ካናዳ ከሰራችላቸው መካከል የተወሰኑት ናቸው።

በአዲስ አበባም 'ጎበዝ' ሚዲያ የሚባል የፕሮዳክሽን ኩባንያ አላት። ከዚህ ቀደም 'ግራንድ ማ ኖውስ ቤስት' የሚልም አጭር ፊልም ሰርታለች። በአሁኑ ወቅትም 'ቄሮ' የሚል ጥናታዊ ፊልም እየሰራች ነው።