የአሜሪካ 50 ግዛቶች ነውጥ ይነሳል በሚል በተጠንቀቅ ላይ መሆናቸውን አሳወቁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በመጪው ረቡዕ በዓለ ሲመታቸው የሚፈፀመው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን ሹመትን ለማስተጓጎል በትጥቅ የታገዘ አመፅ ይኖራል በሚል አምሳዎቹ ግዛቶች በተጠንቀቅ ላይ ናቸው ተባለ።
በተለይም ከበዓሉ በፊት ባለፈው ሳምንት ካፒቶል ሂል እንደነበረው ሁከት ይፈጠራል በሚልም የአገሪቱ ብሔራዊ ዘብም ዋሽንግተን ዲሲ ላይ ሰፍሯል።
ከቀናት በፊት በ50ዎቹ ግዛቶች በሙሉ የተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ደጋፊዎች በጦር መሳሪያ የታገዘ ሁከትና አመፅ ሊያስነሱ ይችላሉ የሚል ማስጠንቀቂያ የፌደራሉ የምርመራ ቢሮ ኤፍቢአይ አስተላልፎ ነበር።
መጪው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንም ሹመታቸውን ከሚረከቡበት ቀንም ቀድመው ሊከሰቱ እንደሚችሉ ቢሮው መረጃ ደርሶኛል ብሏል።
በጦር መሳሪያ የታገዙ ሁከቶች ዋሽንግተን ዲሲን ጨምሮ በአምሳ የተለያዩ ግዛቶች መታቀዳቸውን ሪፖርቶች ቢሮው አግኝቷል።
ከረቡዕ በፊትም በርካታ የዋሽንግተን ዲሲ አካባቢዎች ይዘጋሉ፤እንቅስቃሴም አይኖርም። በሺዎች የሚቆጠሩ የብሔራዊ ዘብ በጥብቅ የሚቆጣጠሩ ይሆናል።
ባለፈው ሳምንት ነውጥ የተነሳበት ካፒቶልን የሚያዋስኑ እንዲሁም በአቅራቢያው ያሉ ጎዳናዎች በሙሉ በብረት ታጥረዋል።
ከዚህ ቀደም በርካቶች የፕሬዚዳንቶችን ሹመት የሚከታተሉበት ናሽናል ሞል የተባለው እንዲዘጋ የፕሬዚዳንቱን ደህንነት በበላይነት የሚቆጣጠረው ብሄራዊ ደህንነት ቢሮ ትእዛዝ አስተላልፏል።
የባይደን ቡድን ኮቪድ-19 ወረርሽኝ መዛመት እንዳይኖር በሚል አሜሪካውያን ለበዓለ ሲመቱ ሲሉ ወደ መዲናዋ እንዳይመጡ ጠይቋል።
የተለያዩ ግዛቶች ባለስልጣናትም ቢሆኑ ዝግጅቶቹን በርቀት ሊከታተሉ እንደሚገባም በተጨማሪም ተነግሯል።
በዛሬው ዕለትም የትራምፕ ደጋፊዎችና ፅንፈኞች በትጥቅ የታገዘ የአመፅ ጥሪ እንደሚኖር ማሳወቃቸውን ተከትሎም ከፍተኛ ጥበቃ ይኖራል ተብሏል።
አንዳንድ የፅንፈኞች ቡድን ደጋፊዎቻቸውን የዛሬውን የአመፅ ጥሪ ከፍተኛ የደህንነትና ጥበቃ ስለሚኖር ከዚህም በተጨማሪ ፖሊስ እንደ ወጥመድ ያዘጋጀው ነው በማለትም እንዳይሳተፉ ጠይቀዋል።
በትናንትናው ዕለትም መሳሪያ የታጠቀ አንድ ግለሰብ መሳሪያና 509 ተቀጣጣይ ነገሮች ይዞ በፍተሻ እንደተያዘ የካፒቶል ፖሊስ አረጋግጧል።
ነገር ግን ይህ ዌስሊ አለን ቢለር የተባለው ግለሰብ ወዲያው እንደተፈታም ለማወቅ ተችሏል። ግለሰቡ በግል የደህንነት ኩባንያ ተቀጥሮ እንደሚሰራና ወደ ዋሽንግተንም ሲመጣ የጦር መሳሪያ ይዞ ለመምጣት አስቦ እንዳልነበር ለዋሽንግተን ፖስት ተናግሯል።
ባይደን በዓለ ሲመታቸው ከተጠናቀቀ እንዲሁም በይፋም ስልጣናቸውን ካወጁ በኋላ በቀድሞው አስተዳደር የተሰሩ አንዳንድ ውሳኔዎችን እንደሚቀለብሱ የአሜሪካ ሚዲያዎች የደረሳቸው መረጃ ጠቁሟል።
ዋይት ሃውስ በገቡ በሰዓታት ውስጥ ይወስዷቸዋል ከተባሉ እርምጃዎች መካከል፦
- የካርበን ልቀትን ለመቀነስና ለመቆጣጠር የተፈረመውን አለም አቀፉን የፓሪስ ስምምነት አገራቸው እንድትመለስ ያደርጓታል።
- ከፍተኛ የሙስሊም ህዝብ ቁጥር ባላቸው አገራት የተጣለውን አወዛጋቢውን የጉዞ ገደብ ያነሱታል።
- በመንግሥት መስሪያ ቤቶችም ሆነ ሌሎች ከተሞች ላይ ዜጎች ሲጓዙ ማስክ (ጭምብል) ማጥለቅ ግዴታ ይሆናል የሚሉ ናቸው።
ልክ እንደ ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ባይደንም ቢሆኑ በርካታ ጉዳዮች ምክር ቤቱን በማለፍ በበላይ ውሳኔ ማስፈፀም ይችላሉ። ነገር ግን ባለፈው ሳምንት ያወጁት የ1.9 ትሪሊዮን ዶላር የምጣኔ ኃብት ማዕቀፍ፣ እንዲሁም በስደተኞች ጉዳይ ያቀረቡት ረቂቅ በምክር ቤቱ መፅደቅ ይኖርበታል።
የአሜሪካ ህግ መምሪያ ምክር ቤት እንደራሴዎች ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት የተከሰተውን የካፒቶሉን ነውጥ አነሳስተዋል በሚል እንዲከሰሱ ውሳኔ ማስተላፋቸው የሚታወስ ነው።
ከስልጣን ሊለቁ ቀናት የቀራቸው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲገፈፍና በአመፅና ሁከት እንዲከሰሱም ለማስቻል እንደራሴዎቹ በአብላጫ ድምፅ ነው የወሰኑት።
በዚህም መሰረት በስልጣን ላይ እያሉ ሁለት ጊዜ እንዲከሰሱ የተወሰነባቸው ወይም ኮንግረሱ በወንጀሎች የጠየቃቸው የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት አድርጓቸዋል።












