ኮሮናቫይረስ፡ ሦስት የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት ከካፒቶል አመጽ በኋላ በኮቪድ መያዛቸው ተገለፀ

ቦኒ ዋትሰን ኮልማን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቦኒ ዋትሰን ኮልማን

ሦስት የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት ባለፈው ሳምንት በነበረው የካፒቶል ሒል ግርግር ወቅት ከሌሎች አባላት ጋር በአንድ ሥፍራ እንዲደበቁ ከተደረጉ በኋላ በኮቪድ-19 መያዛቸው ተገለፀ።

የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባል ሆኑት ቦኒ ዋትሰን ኮልማን፣ ፕራሚላ ዣይፓል እና ብረሰድ ሽናይደር የኮቪድ-19 የምርመራ ውጤታቸውን ይፋ አድርገዋል።

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ነውጠኛ የፕሬዝደናት ትራምፕ ደጋፊዎች ወደ ካፒቶል ሒል ጥሰው ከገቡ በኋላ፣ የምክር ቤት አባላቱ ለደኅንነታቸው ሲባል በአንድ ክፍል ውስጥ ተደብቀው እንዲቆዩ ተደርገው ነበር።

የተወሰኑ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አለማድረጋቸውን በወቅቱ የተቀረፁ ምስሎች አሳእተዋል።

በፐንችቦውል ኒውስ የተሰራጨው ተንቀሳቃሽ ምስል እንደሚያሳየው ከሆነ በርካታ የምክር ቤት አባላት የተሰጣቸውን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ለመቀበል ዳተኛ ሆነው ታይተዋል።

ይሁን እንጂ ሲቢኤስ ከካፒቶል አዳራሽ ውስጥ ተነሳ በሚል ያሰራጨው ምስል እንደሚያሳየው ራሳቸው ዣያፓል አንድ ቦታ ላይ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ አላደረጉም።

የጤና ባለሙያዎች በርካታ የምክር ቤት አባላቱ በተህዋሲው ተይዘው ሊሆን ይችላል ሲሉ የሰጉ ሲሆን፣ ይህም በአሜሪካ በከፍተኛ ፍጥነት የሚዛመተው ቫይረስ ስርጭቱ እየጨመረ ባለበት በዚህ ወቅት መሆኑ የበለጠ ስጋታቸውን አባብሶታል።

በአሜሪካ በመላው ዓለም ከፍተኛ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ስርጭቱም የመቀነስ አዝማሚያ እያሳየ አይደልም ተብሏል።

በአሁን ሰዓት በአሜሪካ 22.6 ሚሊዮን ሰዎች በተህዋሲው መያዛቸው ሲረጋገጥ ከእነዚህም መካከል 367,000 ያህሉ ሞተዋል።

ባለፈው ሳምንት በካፒቶል ሒል በነበረው አመጽ ወቅት በአንድ ስፍራ በጋራ ተጠልለው የነበሩ የምክር ቤት አባላት እና ሠራተኞች፣ የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንዲያደርጉ የምክር ቤቱ ከፍተኛ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ብራያን ሞናህን ጠይቀው ነበር።

ፕራሚላ ዣይፓል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ፕራሚላ ዣይፓል

"በእዚያ ክፍል ውስጥ የነበረው ቆይታ ለተወሰኑት ረዥም ለሌሎች ደግሞ አጭር ነበር" ያሉት ሞናሃን "በዚያ ወቅት ሰዎች ኮሮናቫይረስ ለተያዘ ሰው ራሳቸውን አጋልጠው ሊሆን ይችላል" ሲሉ አክለዋል።

ነገር ግን ሞናሃን ምን ያህል ሰዎች በአንድ ክፍል ውስጥ ተደብቀው እንደነበር ከመናገር የተቆጠቡ ሲሆን፤ አካላዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ እና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲጠቀሙ ግን ምክራቸውን ለግሰዋል።

በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጠው የምክር ቤት አባላት መካከል ኒው ጄርሲን የሚወክሉት ዲሞክራቱ ቦኒ ዋትሰን ኮልማን የመጀመሪያው ሰው ናቸው።

የ75ዓመቱ አዛውንት የምክር ቤት አባል በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ "ቀለል ያለ የጉንፋን ስሜት አለኝ" ብለው ለጥፈዋል።

ማክሰኞ ዕለት ደግሞ ዋሺንግተንን የወከሉት ዲሞክራቷ ዣያፓል እና የኢሊኖይስ ግዛት ተወካይ ሽናይደር በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ይፋ አድርገዋል።

ሦስቱም ዲሞክራቶች ባለፈው ሳምንት ረቡዕ አመጸኞች ምክር ቤቱን ሰብረው በገቡበት ወቅት ራሳቸውን ለማዳን በጋራ በተደበቁበት ክፍል ውስጥ የነበሩና የአፍ መሸፈኛ ጭምብል አላደርግም ብለው የነበሩትን የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላትን ተጠያቂ በማድረግ ኮንነዋል።

ጭምብል አላደርግም ማለት እንዲያስቀጣ በመጠየቅ "ማንኛውም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አላደርግም ብሎ የነበረ አባል ጤናችንን አደጋ ላይ በመጣሉ ተጠያቂ መሆን አለበት" ብለዋል ዣያፓል።

በአሜሪካ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰ ጊዜ አንስቶ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ ትልቅ ፖለቲካዊ ጉዳይ ሆኖ ሲያወዛግብ ቆይቷል። የተወሰኑ የምክር ቤት አባላት በይፋ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።

አርብ ዕለት የአሜሪካ በሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ዳይሬክተር ሮበርት ሬድፊልድ፣ ረቡዕ በካፒቶል ሒል የተከሰተው ግርግር የጤና ቀውስን ይዞ ሊመጣ እነደሚችል አስጠንቅቀቀው ነበር።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች ከቀሰቀሱት ግርግር ጋር በተያያዘ አራት ሰዎች ሞቱ