አሜሪካ ፡ 228 ዓመት ያስቆጠረው የካፒቶል ሒል ኪነ ሕንጻ አጭር የሕይወት ታሪክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካኖች ዲሞክራሲያችሁን በቃላት ሳይሆን በሕንጻ ግለጹበት ብትሏቸው ዋሺንግተን ዲሲ ይዘዋችሁ ይሄዳሉ፤ ካፒቶል ሒል ይዘዋችሁ ይገባሉ።
ያለ ምክንያት አይደለም። ካፒቶል ሒል የዲሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ በግብርም በሐሳብም የያዘ ሕንጻ ስለሆነ ነው። አንዳንድ ጸሐፊዎች ካፒቶል ሒልን "የዲሞክራሲ ቤተ መቅደስ" ብለው የሚጠሩት ለዚሁ ነው።
ዲሲ የመንግሥት መቀመጫ ከተማ ናት። አሜሪካ በመንግሥታዊ ቅርጽ ስትወለድ ከፊላደልፊያ ወደ ዲሲ ዞረች።
የአሜሪካ የመንግሥት መቀመጫን በአንድ ሕንጻ ማመላከት ግን ከባድ ነው። ምናልባት ለዚህ ቀረብ የሚለው ካፒቶል ሒል ነው።
ካፒቶል ሒል ለአሜሪካ 4 ኪሎ እንደማለት ነው፤ በግርድፉ።
የላዕላይና የታህታይ ምክር ቤቶች ፓርላማ ሕንጻ የሚገኘው እዚህ ነው። የጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚገኘውም በዚሁ ግቢ ነው። ኮንግረስ ላይብረሪ እዚህ ኮረብታ ላይ ነው። ዝርዝሩ ብዙ ነው።
ይህ ሕንጻ ብዙ ታሪክ የተሸከመ ነው። ለዚህም ነው በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚጎበኙት። ለዚህ ነው የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የቱሪዝም መዳረሻም የሆነው።
ከሕንጻዎቹ ንጣትና ምስስሎሽ የተነሳ ዋይት ሐውስና ካፒቶል ሒል አንድ የሚመስሏቸው ብዙ ናቸው። በሁለቱ ሕንጻዎች መሀል ግን የሁለት ማይል ወይም የ3.2 ኪሎ ሜትር ርቀት አለ። የግብርም ልዩነት አለ። ዋይት ሐውስ የአስፈጻሚው መሥሪያና ማደርያ ነው ብንል ይሻላል። በካፒቶል ሒል ግን ሕግ አውጪዎች ይበዙበታል።
ዋይት ሐውስ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት መኖርያ ቤትና ጽሕፈት ቤትን አጣምሮ የያዘ ነው።
ከፕሬዝዳንቱና ከ15ቱ የካቢኔ አባላት ጋር የተያያዙ፣ ረዳቶችና የረዳት ረዳቶችን ጨምሮ በርካታ የአስፈጻሚው አካላት አሉበት። ምዕራብና ምሥራቅ ክንፍን ይዞ የኦቫል ቢሮን አቅፎ 400 የሚሆኑ ሠራተኞች ፕሬዝዳንቱን በቀጥታም በተዘዋዋሪም ለማገዝ በ6 ወለል ውስጥ የተቀመጡ 132 ክፍሎች ያሉት ሕንጻ ነው - ዋይት ሐውስ።
ካፒቶል ሒልና ዋይት ሐውስን በመጠን ማነጻጸር ትክክል አይደለም። ካፒቶል ሒል እጅግ ግዙፍ ሕንጻ ነው።
በውስጡ የሚገኘው ኮንግረስ ቤተመጻሕፍት የተሸከመው 38 ሚሊዮን መጻሕፍት ብቻ ስለ ካፒቶል ሒል ግቢ ግዝፈት አፍ አውጥተው ይመሰክራሉ፡፡

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ካፒቶል ሒል መቼ ተገነባ?
ይህን ሕንጻ ጆርጅ ዋሺንግተን ነው አምጠው ያዋለዱት። ለመንግሥት መቀመጫነት ዋሺንግተን ዲሲን መረጡ።
የመጀመርያው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዋሺንግተን የመንግሥት መቀመጫ ዲሲ ውስጥ እንዲሆን ሲወስኑ አንድ ኮረብታ ታያቸው። የጀንኪንስን ኮረብታ።
በዚያች አነስተኛ ኮረብታ ላይ የሚቀመጥ ግዙፍ ሕንጻ አሰቡ። በርከት ያሉ ንድፎች ቀርበው ነበር። የዶ/ር ዊሊያም ቶርተን ንድፍ ቀልባቸውን ሳበው።
ለኪነ ሕንጻው መጀመሪያ የተጨነቀው ሰው ዶ/ር ዊሊያም ቶርተን ይባላል። የእሱ አእምሮ የፈጠረው ንድፍ ነው የጆርጅ ዋሺንግተንን ቀልብ የገዛው።
በመስከረም 18/1793 (እአአ) ጆርጅ ዋሺንግተን እዚህ ኮረብታ ላይ የመሠረት ድንጋይ አስቀመጡ።
ሆኖም ግንባታው በግንባታ እቃዎች አቅርቦት አለመኖርና በሰለጠነ የሰው ኃይል ማነስ ምክንያት በታሰበው ጊዜ ሊጀመር አልቻለም።
ስለዚህ ለጊዜው አንድ ክንፍ ሕንጻ ብቻ ቢገነባ ይሻላል በሚል የሰሜን ክንፍ ሕንጻ ሥራው ተጀመረ። ይህም መሠረት ድንጋዩ በተጣለ በ3ኛ ዓመቱ መሆኑ ነው።
ይህ የሰሜን ክንፉ ሕንጻ ሲገባበት 3ኛው ወለል ጭራሽ ያልተጠናቀቁ ብዙ ክፍሎች ይቀሩት ነበር። የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ የኮንግረስ ላይብረሪ ወለል፣ የዲስትሪክ ኦፍ ኮሎምቢያ ፍርድ ቤት ወለል በ1800 አካባቢ ተገባበት።
በ1803 ኮንግረስ የካፒቶል ሒል ግንባታ እንዲጠናቀቅ የሚያስችል በጀት አጸደቀ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በ1811 የደቡብ ክንፍ ሕንጻ ተጠናቀቀ። ደቡባዊ ሕንጻው የሕግ አውጪዎችን አዳራሽ አጠናቆ አገልግሎት ጀመረ።
ሆኖም በ1012 ጦርነት ነበር። የቀሩትን ሕንጻዎች ለመገንባትም በጦርነቱ የተነሳ ገንዘብ ጠፋ።
ጦርነቱ ቀጠለና በነሐሴ ወር 1814 የብሪታኒያ ወታደሮች ሕንጻውን እሳት ለቀቁበት። በአጋጣሚ ከፍተኛ ዝናብ በመዝነቡ እሳቱ ጠፍቶ የተወነሰው የሕንጻው ክፍል ተረፈ።
ከዚያ በኋላ አዲሱ አርክቴክት ቻርለስ ቡልፊች በአዲስ ጉልበት ካፒቶል ሒልን ማስፋት ጀመረ።
በ1819 ካፒቶል ሒልን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ለሕግ መምሪያው ምክር ቤትና ለሕግ መወሰኛው ምክር ቤት አዳራሾችና ቢሮዎች ምቹ አድርጎ አጠናቀቀው።
የኪነ ሕንጻ አዋቂው ቻርለስ ቡልፊች እነዚህን ሦስት ክንፎች ካጠናቀቀ በኋላ መሀል ላይ የሚገኘውን በመዳብ የተለበጠውን አሁን ጉልላት ያለበትን ሕንጻ ጀመረ።
በ1826 በመዳብ የተለበጠው የሕንጻውን ጉልላት የተሸከመው ሕንጻ ተጠናቀቀ። ከዚህ በኋላ ግቢውንና ሕንጻውን በማሳመር ረዥም ዓመታትን አጠፋ።
ሆኖም በ1850 በርካታ የአሜሪካ ግዛቶች ወኪሎቻቸውን እየላኩ አሜሪካ በመጠንና በውክልና እየሰፋች ስትመጣ ይህ የሕዝብ እንደራሴዎች፣ የሕግ አውጪዎችና የሕግ ተርጓሚዎች የሚርመሰመሱበት ሕንጻ እየጠበበ መጣ።
በዚያን ጊዜ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሚራልድ ፊልሞር በቃ አዲስ ማስፋፊያ ይጀመር አሉ። ቶማስ ዋልተር የሚባል የኪነ ሕንጻ አዋቂ ከፊላደልፊያ አስመጡና ሥራ አስጀመሩት።
ይህ ሰው በካፒቶል ሒል የሰሜንና የደቡብ ተጨማሪ ክንፎችን እገነባለሁ ብሎ ተነሳ።
በሰሜን አቅጣጫ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ግዙፍ መሰብሰቢያ አዳራሽ፣ በደቡብ አቅጣጫ ደግሞ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አዳራሽን ገነባ።
እነዚህ በካፒቶል ሒል ክንፍ ላይ ግራና ቀኝ ተጨማሪ ክንፍ ሆነው የተጨመሩት አዳራሾች ካፒቶል ሒልን እጅግ ግዙፍ አደረጉት።
ሕንጻው ሲገዝፍ ደግሞ ላዩ ላይ የተከመረበት በመዳብ የተለበጠው ጉልላት ኮሳሳ እየሆነ መጣ።
ስለዚህ የሕንጻውን ግዝፈት የሚመጥን አዲስ ጉልላት ያስፈልጋል ተባለ።
በ1855 የመዳቡ ጉልላት ፈርሶ ሌላ በብረት ጥልፍልፎሽ የሚደገፍ የግዙፍ ጉልላት ግንባታ ተጀመረ። ይሄ ጉልላት የዋዛ አይደለም፤ በጣም ግዙፍና 108 መስኮቶች ያሉት ነው።
በ1863 (እአአ) 19 ጫማ ወይም 6 ሜትር የሚረዝመው የነጻነት ሐውልት በነሐስ ተለብጦ በተጠናቀቀው የሕንጻው ጉልላት ላይ እንዲቀመጥ ተደረገ።
ይህ ዝነኛ ሐውልት ሄልሜት ያጠለቀች የሴት ምሥል ሲሆን 15ሺህ ፓውንድ ወይም 6ሺህ 800 ኪሎ ግራም የሚመዝን እጅግ ግዙፍ ሐውልት ነው።
ይህ ሕንጻ 200 ዓመታትን በፈጀው ዘመኑ በጣም በርካታ ማሻሻያዎች የተደረጉለት ሲሆን መጨረሻ ላይ የተጨመረለት የጎብኚዎች ምድር ቤት ነው።
ይህ የጎብኚዎች ምድር ቤት ግዙፍና ሙሉ በሙሉ ከወለል በታች ሆኖ የተገነባ ዘመናዊ አዳራሽ ነው። በየዓመቱ በዚህ አዳራሽ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች የሕንጻዎቹን አገልግሎቶች ሳያውኩ፣ የሕዝብ እንደራሴዎችን ሳይረብሹ ጉብኝት አድርገው ይወጣሉ።
አሁን አሜሪካ ከ50 ግዛቶቿ ሁለት ሁለት እንደራሴዎችን ወደ ካፒቶል ሒል አምጥታ ታከራክራቸዋለች። 100 ሆነው የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ውስጥ ይከራከራሉ።
በግራ በኩል ደግሞ ናንሲ ፔሎሲ ቆፍጠን ብለው የሚመሩት የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አዳራሽ አለ። እዚያ ደግሞ 50ዎቹ ግዛቶች እንደ ሕዝብ ብዛታቸው በቁጥር የተለያዩ የሕዝብ እንደራሴዎችን ይልኩና ሕግ በማውጣት ይጠመዳሉ። እነዚህ የታችኛው ምክር ቤት የሚሰበሰቡት እንደራሴዎች ቁጥር 435 ነው። ድምጽ መስጠት የሚችሉት እነዚህ ናቸው።
ብዙዎቹ ቢሯቸው እዚህ ካፒቶል ሒል ነው። ዋና ዋና ቢሮዎች ብቻ ቢቆጠሩ 540 ይሆናሉ።
የትራምፕ ነውጠኛ ደጋፊዎች የካፒቶል ሒልን የፊተኛውን ክፍል ጥሰው ገብተው ነው ይህ ሕንጻ በድጋሚ የሕይወት ታሪኩ እንዲጻፍ፣ የዓለም ሚዲያ እንዲያወራለት ያደረጉት። ምክንያቱም ይህ ሕንጻ ተራ ሕንጻ አይደለም። የዲሞክራሲ ቤተ መቅደስ እያሉ ነው የሚጠሩት።
ለማንኛውም የትራምፕ ደጋፊዎች ሌላ ነውጥ ካላስነሱ ከ13 ቀናት በኋላ ጆ ባይደን ካፒቶል ሒል ፊት ለፊት 46ኛው ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሀላ ይፈጽማሉ።
228 ዓመት ያስቆጠረው ካፒቶል ሒል እሳቸውንም ታሪክ እስኪያደርጋቸው ድረስ። ታሪክ የማይሆን ማን አለ?












