አሜሪካ፡ የፕሬዝዳንት ትራምፕ ካቢኔ አባላት በፈቃዳቸው ስልጣናቸው እየለቀቁ ነው

የፎቶው ባለመብት, White House handout
ከመላው ዓለም ውግዘት እየደረሰባቸው ያሉተረ ፕሬዝዳንት ካቢኔ አባሎች ረቡዕ ዋሽንግተን ውስጥ በተከሰተው ግርግር ምክንያት በፈቃደሰቸው ሥልጣን እየለቀቁ ነው።
ነውጠኛ ደጋፊዎቻቸው የመንግሥት መቀመጫና የሁለቱ ምክር ቤቶች አዳራሾች የሚገኙበትን ካፒቶል ሒልን ጥሰው መግባታቸውን ተከትሎ በርካታ የዓለም መንግሥታት ዶናልድ ትራምፕን አውግዘዋል።
የቅርብ ወዳጃቸው ናቸው የሚባሉት የታላቋ ብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ጭምር ጠንካራ ቃላትን ተጠቅመው የትራምፕን ንዝላልነት ተችተዋል። በእንዲህ ዓይነት ኩነቶች ዝምታን የሚመርጡት የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንጌላ መርክልም ትራምፕን ወቅሰዋል።
የዴንማርክ የኖርዌይ የፈረንሳይ መሪዎች በካፒቶል ሒል የታየውን ነውጥ ተችተዋል።
ከዓለም መንግሥታት ትችት በተጨማሪ ትናንት ሐሙስ ምሽት ሁለት የትራምፕ የካቢኔ አባላት ሥልጣናቸው በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸው ተሰምቷል።
የትምህርት ሚኒስትር ቤትሲ ዴቫስ ከሰዓታት በፊት መልቀቂያ አስገብተዋል።
ለረዥም ጊዜ ያገለገሉት ሚስስ ቤትሲ ዴቫስ በመልቀቂያቸው ዶናልድ ትራምፕ የወንበዴዎችን አመጽ በማቀጣጠልና ይሁንታን በመስጠት ወንጅለዋቸዋል።
ከሳቸው ቀደም ብሎ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ኤሌይን ቻዎ ሥልጣን ለቅቀዋል። በሆነው ነገር ስለተረበሽኩ ከትራምፕ ጋር ለመሥራት እቸገራለሁ ብለዋል በመልቀቂያቸው። ወ/ሮ ቻው በሴኔት የሪፐብሊካኑ ተጠሪ ሚች መከኔል ባለቤት ናቸው።
ከካቢኔ አባላት በተጨማሪ የትራምፕ ልዩ ረዳቶቻቸውም መልቀቂያ እያስገቡ ነው። በዲፕሎማሲ መስክ ልዩ መልእክተኛ ማይክ ማልቨኒ እንዲሁም የብሔራዊ ደኅንነት መኮንኖችና የቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ ረዳቶችም በብዛት ለቅቀዋል።
የስቴት ዲፓርትመንቱ አማካሪ ደግሞ ትራምፕ ለአሜሪካ አይመጥኑም ማለታቸውን ተከትሎ ከሥራ ተሰናብተዋል።
ይህንን ውግዘት ተከትሎ ዶናልድ ትራምፕ ለመጀመርያ ጊዜ ሰላማዊ የሥልጣን ርክክብ አደርጋለሁ ብለዋል። ይህን ያሉት ደጋፊዎቻቸው ካፒቶል ሒልን ጥሰው መግባታቸውን ተከትሎ በደረሰባቸው ዓለም አቀፍ ውግዘት ነው።
ከጥብቅ ማስጠንቀቂያ ጋር የትዊተር ሰሌዳቸው የተመለሰላቸው ዶናልድ ትራምፕ ከዓለም መሪዎችና ተጽእኖ ፈጣሪዎች ከፍተኛ ውግዘት ከደረሰባቸው በኋላ መሸነፋቸውን በግልጽ ቋንቋ ባያምኑም የሥልጣን ርክክቡ ግን ሰላማዊ ይሆናል ብለዋል።
ዲሞክራቶች በበኩላቸው ፕሬዝዳንቱ ሥልጣን ለማስረከብ 13 ቀናት ቢቀሯቸውም አሁኑኑ ከቤተ መንግሥት እንዲባረሩ ጥያቄ እያቀረቡ ነው።
ሽግግሩ ሰላማዊ ይሆናል ብለው የተናገሩት ትራምፕ ይህ ንግግራቸው ለመጀመርያ ጊዜ ሽንፈታቸውን ዋጥ ያደረጉበት ነው ተብሏል።
ዶናልድ ትራምፕ በባይደን የተሸነፍኩበት ምርጫው ተጭበርብሮ ነው ብለው ያምናሉ።
ሆኖም ለዚህ ክሳቸው አንድም ማስረጃ ማቅረብ አልቻሉም። ተጭበርብሯል ያሉባቸው የግዛት ምርጫ ጣቢያዎች ሁሉ ትራምፕ ያቀረቧቸው ማስረጃዎች በፍርድ ቤት ጭምር ውድቅ ተደርገውባቸዋል።
ሆኖም ዶናልድ ትራምፕ አሁንም ቢሆን የምርጫውን ውጤት በጸጋ መቀበል ተስኗቸዋል።
የትራምፕ ወደ ትዊተር መመለስ
ትራምፕ ወደ ትዊተር የተመለሱት ትናንት ሐሙስ ማታ ሲሆን ለ12 ሰዓታት የትዊተር ገጻቸው ተዘግቶ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ የትዊተር ሕግና ደንቦችን ጥሰዋል በሚል ነው። ፌስቡክና ኢኒስታግራም ግን ላልተወሰነ ጊዜ ተዘግቶባቸዋል።
ትራምፕ በትዊተር ሰሌዳ በቪዲዯ ባስተላለፉት መልእክት የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ባይደን 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ ስላጸደቀ በጃንዋሪ 20 ሥልጣን አስረክባለሁ ብለዋል።
በዚህ ንግግራቸው ትራምፕ ነውጠኛ ደጋፊዎቻቸውን ያደነቁ ሲሆን ምስጋና ካቀረቡላቸው በኋላ 'ትግላችን ጀመረ እንጂ መቼ አበቃና' ብለዋል።
የትራምፕ ደጋፊዎች የመንግሥት መቀመጫ የሆነውን ካፒቶል ሂልን ጥሰው መግባታቸው በስብሰባ ላይ የነበሩት የሕዝብ እንደራሴዎች ለጊዜው ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸውና ወደ መደበቂያ እንዲወሰዱ አስገድዶ ነበር።
ትራምፕ ያሰማሯቸው ነውጠኛ ደጋፊዎች ካፒቶል ሒልን ጥሰው ሲገቡ ታህታይና ላእላይ ምክር ቤት አባላት የባይደንን መመረጥ ከግዛት ተወካዮች የማረጋገጥ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ይህንኑ በመካሄድ ላይ ነበሩ።
አፈ ጉባኤ ናንሲ ፒሎሲና ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስም በሸንጎ ላይ ተገኝተው ነበር። ሁለት የተለያዩ ነውጠኞች ካፒቶል ሂልን ሰብረው ከገቡ በኋላ በናንሲ ፒሎሲ ወንበር እንዲሁም ማይክ ፔንስ በሚቀመጡበት የሰብሳቢ ወንበር ላይ እግራቸውን ሰቅለው ተቀምጠው ታይተዋል።
ይህንን ለአሜሪካ እንግዳ የሆነ ድርጊት ተከትሎ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፒሎሲ 25ኛውን የሕገ መንግሥት አሜንድመንት በመጥቀስ ትራምፕ አሜሪካንን ለመምራት ብቁ ስላልሆኑ ከዋይት ሐውስ እንዲባረሩ ጥያቄ አቅርበዋል።
ይህን ጥያቄ በርካታ ዲሞክራቶችና ጥቂት ሪፐብሊካኖች ጭምር ድጋፍ ሰጥተውታል። የሴኔት ዲሞክራት ተጠሪ ቸክ ሹመር ትራምፕ አመጽ በማቀጣጠላቸው ከሥራ ሊባረሩ ይገባል ብለዋል።
25ኛው አሜንድመንት አንድ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የአእምሮ ጤና ከራቀው በአስቸኳይ ተወግዶ ምክትል ፕሬዝዳንቱ አገሪቱን እንዲመሩ ያዛል።
ሆኖም ይህ እንዲተገበር ናንሲ ፒሎሲን ጨምሮ በትንሹ 8 የካቢኔ አባላት በጉዳዩ መስማማት አለባቸው። ይህ የመሆን እድሉ ለጊዜው ጠባብ ነው ተብሏል።
ዶናልድ ትራምፕ ከዋይት ሐውስ እንዲወገዱ እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን ለድርጊታቸው ክስ እንዲመሰረትባቸውም ናንሲ ፒሎሲ ጥሪ አድርገዋል። ክሱ ተፈጻሚ እንዲሆን ግን ዲሞክራቶች የሪፐብሊካኖችን ድጋፍ ማግኘት አለባቸው። ምክንያቱም ክሱ እንዲፈጸም የምክር ቤቱ ሁለት ሦስተኛው ድምጽ ስለሚያስፈልግ ነው። ይህ የመሳካት እድሉም አነስተኛ ነው።
በአሜሪካ ታሪክ እምብዛምም ባልተለመደ ሁኔታ የትራምፕ ደጋፊዎች ነውጥ እንዴት ሊከሰት ቻለ የሚለው እያነጋገረ ነው፤ በተለይም የካፒቶል ሒል ጥበቃ መላላት ነገሩ የጸጥታ ኃይሎች ድጋፍ እንደነበረው ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
ከትናንት በስቲያ በነበረው ነውጥ እስካሁን 4 ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል።
ከሳንዲያጎ ካሊፎርኒያ የመጣቸው የ35 ዓመቷ የአሜሪካ አየር ኃይል የቀድሞ ባልደረባ አሽሊ ባቢት በፖሊስ ተተኩሶባት መሞቷ ተረጋግጧል።
ሌሎቹ ሟቾች ማንነትም የተለየ ሲሆን ቤንጃሚን ፊሊፕስ ከፔኒሲልቬኒያ ኬቭን ግሪንሰን ከአለባማ ሮዘን ቦይላንድ ከጆርጂያ መሆናቸው ፖሊስ ይፋ አድርጓል።
ከነዚህ ሟቾች በተጨማሪ 14 ፖሊሶች ላይ የመቁሰል አደጋ ተመዝግቧል።












