የጆርጂያን ድል ተከትሎ ዲሞክራቶች የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱን ተቆጣጠሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
"ሁለተኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ" የሚል ስም የተሰጠው የጆርጂያ ግዛት እንደራሴዎች ምርጫ በዲሞክራቶች የበላይነት ተጠናቋል።
ሚስተር ዋርኖክ እና ሚስተር ኦሶፍ ድል ቀንቷቸዋል።
ሁለቱ እጩዎች በቀጥታ የሴኔት አባል በመሆናቸው ሪፐብሊካኖች በላዕላይ ምክር ቤት ውስጥ የነበራቸውን የበላይነት አጥተዋል።
ዲሞክራቶቹ ራፋኤል ዋርኖክ እና ጆን ኦሶፍ ተቀናቃኞቻቸውን ኬሊ ሊዮፍለርን እና ዴቪድ ፐርዲዩን ያሸነፉት በጠባብ ልዩነት ነው።
ይህ በመሆኑም ከእንግዲህ በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ውስጥ የዲሞክራቶችና የሪፐብሊካኖች ቁጥር እኩል 50=50 ሆኗል። ከእንግዲህ በድምጽ አሰጣጥ ሂደት ወሳኙ እጅ ከምክትል ፕሬዝዳንት ተመራጭ ካሜላ ሐሪስ የሚመጣ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም የላእላይ ምክር ቤቱን ሸንጎ የሚመሩት እርሳቸው ስለሚሆኑ ነው።
ዲሞክራቶች ናንሲ ፒሎሲ በአፈ ጉባኤነት የሚመሩትን የታችኛው ምክር ቤትን ብቻ ነበር በበላይነት የሚመሩት። አሁን ግን የጆርጂያን ድል ተከትሎ ሴኔቱም የዲሞክራቶች ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዲሞክራቶች የሕግ መምሪያን፣ የሕግ መወሰኛንና ዋይት ሐውስን በአንድ ጊዜ መቆጣጠር ሲችሉ ከ2009 ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ነው።
በጆርጂያ ሴኔትን የሚወክል የሕዝብ እንደራሴ ምርጫ 4 ሚሊዮን ነዋሪዎች ድምጽ ሰጥተዋል። ምርጫው የተካሄደው በድጋሚ ነው።
ይህ ምርጫ ባለፈው ኅዳር ተደርጎ አንዳቸውም እጩዎች ከ50 በላይ የሕዝብ ድምጽ ማግኘት ስለተሳናቸው ነው ባለፉት ቀናት በድጋሚ እንዲካሄድ የተደረገው።
በመጀመርያ ድል የተሰማው ከራፋኤል ዋርኖክ ነበር። ዋርኖክ በታሪክ ውስጥ በባሪያ አሳዳሪነቷ በምትታወቀው ጆርጂያ ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ የሕዝብ ይሁንታን አግኝቶ ሴኔት የገባ ጥቁር የሕዝብ እንደራሴ ለመሆን በቅቷል።
በአሜሪካ ታሪክም ዋርኖክ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ሴኔት ለመግባት 11ኛው ጥቁር ሰው ነው።
ዋርኖክ ማሸነፉን ተከትሎ የድሉን መታሰቢያ ለ82 ዓመት እናቱ አውሎታል። እናቱ ጥቁር በመሆናቸው በጥጥ እርሻ ውስጥ የጉልበት ሥራ ሲሰሩ የነበሩ ናቸው።
ዋርኖክ በአትላንታ አቤኔዘር ቤተክርስቲያን ሰባኪ ሲሆን፣ ይህ ቤተክርስቲያን በታሪክ እንደሚታወቀው ዝነኛው የጥቁሮች መብት ታጋይ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ሲሰብክበት የነበረ ቤተእምነት ነው።
ሁለተኛው የዲሞክራት ተመራጭ ጆን ኦሶፍ እድሜው ገና 33 ሲሆን የተወለደው በአትላንታ ነው። በሙያው የዘጋቢ ፊልም አሰናጅ የሆነው ኦሶፍ፣ የ2ኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ከዝነኛው የጥቁሮች መብት ታጋይ ከጆን ልዊስ ጋር አብሮ በመሥራቱ ዝናን አግኝቷል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ጆን ኦሶፍ በ2012 በሎንዶን መቀመጫውን ያደረገ የምርመራ ጋዜጠኛ ቡድን ጋር መሥራት ከጀመረ ወዲህ ነው ይበልጥ እየታወቀ የመጣው።
50ዎቹ የአሜሪካ ግዛቶች እኩል 2 እንደራሴዎችን በመላክ የሚወከሉበት ሴኔት በዲሞክራቶች ቁጥጥር መዋሉ ቀጣዩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሚሾሟቸው ባለሥልጣናትና ዳኞች እንዲሁም ፖሊሲዎችና ሕጎች በቀላሉ በሁለቱም ምክር ቤቶች በድምጽ ብልጫ እንዲጸድቁላቸው ያግዛቸዋል።
በተለይም ሪፐብሊካኖች አምርረው በሚቃወሟቸው የጤና መድኅን እና የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ዙርያ ባይደን ፍላጎታቸው ለማስፈጸም ትልቅ እድል ያገኛሉ ተብሏል።
ሪፐብሊካኖች በጆርጂያ ለገጠማቸው ሽንፈት ፕሬዝዳንት ትራምፕን ተጠያቂ ማድረግ ጀምረዋል።












