የአሜሪካ ምርጫ 2020፡ በጆርጂያ ምርጫ ዲሞክራቶችና ሪፐብሊካን አንገት ለአንገት ተናንቀዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትናንት በተጀመረው የጆርጂያ ግዛት ለሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ውክልና ምርጫ ዲሞክራቶችና ሪፐብሊካን ተናንቀዋል።
እስከአሁን ያሉ ቆጠራዎች እንደሚያሳዩት የሁለቱ ፓርቲ ዕጩዎች በጣም በተቀራረበ ውጤት ላይ ናቸው።
ሪፐብሊካን ፓርቲን የወከለችው ኬሊ ሎፍለር እንዲሁም ሌላኛው ዕጩ ዴቪድ ፐርዲዩ ከዲሞክራቶቹ ራፋኤል ዋርኖክና ጆን ኦሶፍ ጋር እልህ አስጨራሽ ትግል ላይ ናቸው።
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፓርቲያቸው የጆርጂያን ውክልና ማሸነፉ እጅግ ቁልፍ ጉዳይ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው "ይህ ምርጫ የመጨረሻው የሪፐብሊካኖች ምሽግ ነው" ሲሉ መራጮች ነገሩን እንደዋዛ እንዳይመለከቱት ቀስቅሰዋል።
የጆርጂያ ግዛት ምርጫ በዚህ ደረጃ ትኩረት ሊስብ የቻለው በሚቀጥሉት ዓመታት የአሜሪካንን የፖለቲካ መልክአ ምድር የመቀየር አቅም ስላለው ነው።
በጆርጂያ የዲሞክራቶች ማሸነፍ በአሜሪካ የፖለቲካ፣ የፖሊሲና የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ የጆ ባይደንና የቡድናቸውን ጉልበት የሚጨምር ይሆናል።
ሪፐብሊካኑ ከሁለቱ እጩዎች አንዱን እንኳ ማሸነፍ ከቻሉ በሴኔት ጠባብ የበላይነትን ይጎናጸፋሉ። ሴኔቱ ላለፉት ዓመታት በሪፐብሊካን የበላይነት መቆየቱ ይታወሳል።
ዲሞክራቶች ግን የጆርጂያን 2 እንደራሴዎች ምርጫ ማሸነፍ ከተቀናቃኞቻቸው ሪፐብሊካን ጋር እኩል 50 ወንበሮች እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ይህ እኩሌታውን ወንበር የማግኘቱ ነገር እንደ ድል የሚቆጠረው በካምላ ሐሪስ ምክንያት ነው።
የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት የሚመራው በምክትል ፕሬዝዳንት ስለሚሆን እኩል 50=50 እንደራሴዎች ድምጽ ሲሰጡ ምክር ቤቱን የሚመሩት ቀጣይ ምክትል ፕሬዝዳንት ካምላ ሐሪስ ስለሚሆኑ የእርሳቸው ድምጽ በሸንጎው ወሳኝ የመለያ ድምጽ ሆኖ እንዲቀጥል ያስችላል።
በዚህም የተነሳ ዲሞክራቶች በጆርጂያ ሁለት እንደራሴዎች ቢያሸንፉላቸው ሴኔትን መቆጣጠር ያስችላቸዋል ማለት ነው።
ናንሲ ፔሎሲ የሚመሩት የሕግ መምሪያው ምክር ቤት በዲሞክራቶች የበላይነት የተያዘ ሸንጎ ነው።
አሁን ቆጠራ ላይ የሚገኘው የጆርጂያ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የእንደራሴዎች ምርጫ ባለሀብቷ ሚስ ኬሊ ሎፍለር ከጥቁሩ የመብት ታጋይ ሚስተር ራፋኤል ዋርሎክ ጋር ተናንቀዋል።
ሚስተር ፐርዲዩ ደግሞ ከሚስተር ኦሶፍ ጋር አንገት ለአንገት ተያይዘዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በጆርጂያ 159 የምርጫ ወረዳዎች ሲኖሩ ከነዚህ ውስጥ እስከ አሁን 88 ከመቶው ድምጽ ተቆጥሯል። ሆኖም አሸናፊው አልተለየም።
ለጊዜው ሁለቱ የሪፐብሊካን ዕጩዎች በትንሽ ቁጥር እየመሩ እንደሆነ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው። ነገር ግን በሺህ የሚቆጠሩ ድምጾች ገና በመቆጠር ላይ ናቸው።
በተለይም ከአትላንታ ከተማ ወጣ ብለው በሚገኙ ትንንሽ የምርጫ ጣቢያዎች በርካታ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ደጋፊዎች በመኖራቸው የሪፐብሊካን ዕጩዎች መሪነት ሊቀለበስ ይችላል ተብሎ ተገምቷል።
ከትናንት ማክሰኞ በፊት ብቻ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ የጆርጂያ ነዋሪዎች ድምጽ ሰጥተዋል፤ ይህም ድምጹን ለመስጠት ከተመዘገበው ጠቅላላ ሕዝብ 40 ከመቶው ነው።
በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደታየው ከምርጫ ቀን በፊት ድምጽ የሚሰጡት በብዛት የዲሞክራቲክ ፓርቲ ደጋፊዎች ናቸው።
በፕሬዝዳንትነት ውድድር መሸነፋቸውን ለመቀበል ዳገት የሆነባቸው ዶናልድ ትራምፕ በጆርጂያ የእንደራሴዎች ምርጫ ላይም እምነትን የሚሸረሽሩ መልዕክቶችን በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ መጻፋቸውን ቀጥለውበታል።
ከሰሞኑ ዶናልድ ትራምፕ የጆርጂያ ግዛት ምርጫ አስፈጻሚን በስልክ ድምጽ እንዲያጭበረብርላቸው ሲወተውቱ የሚያስደምጥ የተቀዳ የስልክ ልውውጥ በዋሺንግተን ፖስት ይፋ ተደርጎባቸው ትልቅ ውግዘትን ሲያስተናግዱ እንደነበር አይዘነጋም።
የጆርጂያ ግዛት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የእንደራሴዎች ምርጫ አሁን እየተደረገ ያለው በድጋሚ ለ2ኛ ጊዜ ነው።
ለመጀመርያ ጊዜ የተደረገው ባለፈው ኅዳር ከአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጎን ለጎን ነበር።
ድጋሚ ምርጫ የተጠራበት ምክንያት ደግሞ በጆርጂያ ግዛት የምርጫ ደንብ መሰረት ዕጩዎች ከ50 ከመቶ በታች ድምጽ ካገኙ ድጋሚ የውክልና ምርጫ እንዲደረግ ስለሚያዝ ነው።
በአሜሪካ ፖለቲካዊ መዋቅርና አካሄድ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤትን በበላይነት መያዝ ለተመራጩ ፕሬዝዳንት ቁልፍ ጉዳይ ነው የሚሆነው።
ምክንያቱም ተቀናቃኞቻቸው ለሚያወጡት ሕግና ፖሊሲዎች ተግባራዊ እንዳይሆኑ ማነቆ እንዳይሆኑባቸው ይረዳል።
ለምሳሌ ሪፐብሊካኖች በጤና መድኅን፣ በአየር ንብረት ለውጥና በሌሎች ቁልፍ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚወጡ ሕጎችን በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ድምጽ በመስጠት ውድቅ ሊያደርጓቸው ይችላሉ።
ይህ ሸንጎ በዲሞክራቶች ከተያዘ ግን በቀላሉ አስፈላጊ ፖሊሲዎችንና ሕጎችን ለማሳለፍ እንዲሁም ለከፍተኛው ፍርድ ቤትና ለከፍተኛው የአገሪቱ ሥልጣን ካቢኔ ባይደን የሚያጯቸውን ሰዎች ያለ ድካም ለማጸደቅ ይረዳል።
በጆርጂያ ግዛት የዲሞክራቲክ ፓርቲ እጩዎቹ ኦሶፍ እና ዋርኖክ ሁለቱም ቢያሸንፉ የሕግ መምሪያውን፣ የሕግ መወሰኛውና ነጩ ቤተመንግሥት ሙሉ በሙሉ በዲሞክራቶች ቁጥጥር ሥር እንዲወድቅ ያደርገዋል።
ይህ ሆኖ የሚያውቀው በ2008 ባራክ ኦባማ ባሸነፉበት ዓመት ብቻ ነው።
ጆርጂያ በአመዛኙ ለሪፐብሊካን የምታደላ ናት። አንድ ዲሞክራት የሕዝብ እንደራሴ ላለፉት 20 ዓመታት በጆርጂያ አሸንፎ አያውቅም። ጆ ባይደንም ግዛቷን ሲያሸንፉ ከ30 ዓመት በኋላ የመጀመርያው ሰው ናቸው።
የዲሞክራቱ ዕጩ ራፋኤል ዋርኖክ የጆርጂያን ውክልና ካሸነፈ የመጀመርያው የግዛቲቱ ጥቁር የሴኔት ሸንጎ እንደራሴ በመሆን አዲስ ታሪክ ያስመዘግባል ተብሎ ይጠበቃል።















