ትራምፕ “ድምጽ አጭበርብሩልኝ” ሲሉ የተለማመጡበት የስልክ ንግግር ይፋ ሆነ

ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ትራምፕ ስልክ እየደወሉ ጆ ባይደንን እንዳሸንፈው ትንሽ ድምጽ እንዴትም ብላችሁ አሟሉልልኝ እያሉ የግዛት አስመራጮችን ይለምኑ እንደነበር ዋሺንግተን ፖስት አጋለጠ።

ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባለፈው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጆ ባይደንን እንዳሸንፍ ድምጽ ከየትም ብላችሁ ፈልጉ እያሉ ከደወሉባቸው የግዛት የምርጫ ኃላፊዎች አንዱ የጆርጂያ ግዛት ምርጫ አስፈጻሚ ብራድ ራፍነስፐርግ ናቸው።

ዋሺንግተን ፖስት ይፋ ባደረገው የስልክ ቅጂ ንግግር ትራምፕ ለብራድ እባክህ 11ሺ 780 ድምጽ ከየትም ብለህ ፈልግ እያሉ ሲለምኑ እንደነበር ያጋልጣል።

ብራድ በበኩላቸው የጆርጂያ ግዛት ቆጠራው በትክክል ተቆጥሮ መጠናቀቁን ለትራምፕ ሲናገሩ ይሰማሉ።

ሆኖም ትራምፕ ሰውየውን በማባበልና በማግባባት ትንሽ የተጭበረበሩ ድምጾችን ካገኘ እሳቸው አሸናፊ እንደሚሆኑ በማስረዳት እንደምንም ተባባሪ እንዲሆን ሲያበረታቱት ይሰማል።

ሚስተር ብራድን በማግባባቱ የስልክ ንግግር ውስጥ ትራምፕ እንዲህ ሲሉ ይሰማል "እንደምንም ብለህ ድምጽ ቆጠራው ላይ ስህተት ሰርተናል ብትልልኝ እኔን በቀላሉ አሸናፊ ያደርገኛል፤ ያን ብትል ምንድነው ችግሩ"

ሚስተር ብራድ በበኩላቸው "የተከበሩ ፕሬዝዳንት፣ ቆጠራው ስህተት ነው ብለው የያዙት መረጃ ስህተት መሆኑ ነው ችግሩ" ብለው ይመልሱላቸዋል።

ትራምፕ ምርጫ ኃላፊው ማባበያቸውን አልቀበል ሲሏቸው ቆጣ ብለው "ምርጫ ሲጭበረበር እያየህ ዝም ማለት ወንጀል እንደሆነ አታውቅም? ይሄ አንተንም ሆነ ጠበቃህን ብዙ ችግር ውስጥ የሚከትህ ነው የሚሆነው" እያሉ ለማስፈራራት ሞክረዋል።

ትራምፕ የጆርጂያ ግዛት ምርጫ አስፈጻሚን ለማግባባት የሞከሩት 11ሺ 780 ድምጽ ቢያገኙ አሸናፊ ሊያደርጋቸው ይችል እንደነበረ ስለተረዱ ነው።

ትራምፕ የተለማመጡትን የመራጭ ድምጽ ቢያገኙ በጆርጂያ ግዛት 2 ሚሊዮን 473ሺህ 634 ድምጽ በማግኘት አሸናፊ ያደርጋቸው ነበር። ጆ ባይደን ያገኙት ድምጽ 2 ሚሊዮን 473ሺህ 633 ስለነበር በትንሽ ድምጽ ልዩነት ግዛቲቱን ማሸነፍ ነበር የትራምፕ ግብ።

ጆ ባይደን ጆርጂያ ግዛትን ማሸነፋቸው አይዘነጋም። ጆርጂያ ትራምፕ ያሸንፉበታል ተብሎ የሚጠበቅ ግዛት ስለነበር ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ግዛት ከፍተኛ የማሸነፍ ፍላጎት ነበራቸው።

አሁን 50ዎቹም ግዛቶች ማን አሸናፊ እንደሆነ የሚያረጋግጥ ሰርተፍኬት ያተሙ ሲሆን ዶናልድ ትራምፕ ግን ውጤቱን ለማስቀልበስ ቢያንስ 60 የሚሆኑ የክስ ፋይሎችን ከፍተው ነበር።

የአሜሪካ ፍርድ ቤቶች 60ውን ክስ በተለያዩ ግዛቶች ውድቅ አድርገዋቸዋል።

ከነገ በስቲያ በጃንዋሪ 6 ኮንግረስ ተሰብስቦ የምርጫ ውጤቱን በይፋ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚያ በኋላ በጃንዋሪ 20 ጆ ባይደን ቃለ መሀላ ፈጽመው ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት ይገባሉ።

በጆርጂያ ግዛት ሁለት የሴናተር ወኪሎች ምርጫ ከሰሞኑ ይደረጋል። ውጤቱን የላይኛውን ምክር ቤት ለመቆጣጠር እጅግ ወሳኝ ይሆናል።

ለምሳሌ በምርጫው ዲሞክራቶች ቢያሸንፉ በሴኔቱ የሪፐብሊካንና የዲሞክራቶች ቁጥር አቻ ይሆናል። ይህም ማለት ምክር ቤቱን የሚመሩት ምክትል ፕሬዝዳንት የሚሆኑት ካማላ ሐሪስ ስለሚሆኑ እርሳቸው በሚሰጡት አንዲት ድምጽ የዲሞክራቶች ፍላጎት ተፈጻሚ መሆን ይችላል።

የታችኛው ምክር ቤት ግን አሁንም በዲሞክራት ወኪሎች የበላይነት የተያዘ ነው። ናንሲ ፒሎሲም በድጋሚ ለሌላ 4 ዓመት የታችኛው ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው በድጋሚ ተመርጠዋል።