እውን የፈረንጆቹ 2020 መጥፎ ዓመት ነበር?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለብዙዎቻችን 2020 ማብቂያ የሌለው አሰስ ገሰሱን መከራ ይዞ የመጣ ነበር። አንዳንዶች ይህን ዓመት በጣም 'የተረገመ' ሲሉ ይጠሩታል።
ነገር ግን ወደ ኋላ ዞር ብለን ታሪክ ስንቃኝ 'የተረገመ' ባይባሉ እንኳ ብዙ መከራ ይዘው የመጡ ዓመቶች ነበሩ።
መጀመሪያ እስቲ ስላሳለፍነው የፈረንጆቹ 2020 ትንሽ እንበል። ከዚያ ከታሪካዊ 'የተረገሙ' ዓመታት ጋር እናነፃፅረው። ማን ያውቃል ይህም ነበር እንዴ ያስብል ይሆናል።
በ2020 ኮቪድ 19 በርካታ ሰዎችን ገድሏል
እስካሁን ድረስ ባለው መረጃ መሠረት 74.5 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ከ1.6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሞተዋል።
ይህን መረጃ ያቀናበረው ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ነው።
ነገር ግን ከዚህ ቀደም ከነበሩ ወረርሽኞች ጋር ሲነፃፀር ይህ ቁጥር ትንሽ ነው።
ለምሳሌ በ1346 የተቀሰቀሰው ጥቁሩ ሞት እየተባለ የሚጠራው ወረርሽኝ አውሮፓ ውስጥ ብቻ 25 ሚሊዮን ሰዎች ሲገድል በዓለም አቀፍ ደረጃ 200 ሚሊዮን ሰዎች እንደሞቱ ይነገራል።
በ1520 ደግሞ የፈንጣጣ ወረርሽኝ ከ60 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑ የደቡብ አሜሪካ ሰዎችን እንዳጠፋ ይገመታል።
ሌላኛው የ100 ዓመት ታሪክ ያለው ወረርሽኝ ስፓኒሽ ፍሉ ነው።
ከአንደኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በወታደሮች አማካይነት የተስፋፋው ይህ በሽታ 50 ሚሊዮን ሰዎችን ገድሏል። ይህ በወቅቱ ከነበረው የዓለም ሕዝብ ጋር ሲነፃፀር እስከ አምስት በመቶ የሚደርስ ነው።
በ1980ዎቹ የተቀሰቀሰው ኤችአይቪ/ኤድስ ደግሞ 32 ሚሊዮን ሰዎችን ገድሏል።
በ2020 በርካቶች ሥር አጥ ሆነዋል
ወረርሽኙ ያስከተለው የምጣኔ ሃብት ቀውስ እጅግ ከባድ ነው። የበርካቶችን በር አንኳኩቷል።
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ብዙ ሰዎች የዕለት ጉርስ ከሚያገኙበት ሥራቸው ተፈናቅለዋል።
ነገር ግን ዘንድሮ የታየው የሥራ አጥ ሰዎች ቁጥር በ1929-33 ከተሰተው 'ግሬት ዲፕሬሽን' ተብሎ ከሚጠራው ቀውስ አይበልጥም።
1933 እጅግ 'የተረገመ' ዓመት እንደነበር ታሪክ ይናገራል።
ጀርመን ውስጥ ከሶስት ሰዎች አንድ ሰው ሥራ አልነበረውም። የወቅቱን መሪ ደግሞ ብዙዎች ያውቁታል። አዶልፍ ሂትለር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በ2020 ጓደኞቼን ማግኘት አልቻልኩም
እርግጥ ነው በወረርሽኙ ምክንያት በርካቶች ቤታቸው ተከርችመው ከርመዋል። ዘመድ አዝማድ ማግኘት ተስኗቸው ቆይቷል።
ነገር ግን በ536 በርካታ የዓለም ዜጎች ሰማይን እንኳ ማየት አልቻሉም ነበር።
ከየት እንደመጣ ያልታወቀ ጉም አውሮፓን፣ መካከለኛው ምስራቅንና አንዳንድ የእስያ ሃገራትን ሸፍኖ ነበር። ይህ የሆነው ለ18 ወራት ነበር።
ይህ ዓመት በሰው ልጅ ታሪክ እጅግ የተረገመው ሳይሆን አይቀርም የሚሉ በርካቶች ናቸው።
ባለፉት 2300 ዓመታት በጣም ከባድ ብርድ የታየውም በዚህ ዘመን ነበር። ሰብሎች ወድመዋል። በርካቶች ተርበዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በ2020 ለበዓል መጓዝ አልቻልኩም
እየተገባደደ ያለው የፈረንጆቹ ዓመት ለቱሪዝም ዘርፍ ዱብእዳ ይዞ የመጣ ነው። በርካቶች ከሃገር ሃገር፤ ከከተማ ወደ ገጠር መጓዝ አልቻሉም።
ነገር ግን ከ195 ዓመት በፊት የነበሩ ቀደምት የሰው ልጅ ዝርያዎች [ሆሞ ሳፒየንስ] በተመሳሳይ ከቦታ ቦታ መዘዋወር አልቻሉም ነበር።
ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የአየር ንብረት ነው። ወቅቱ እጅግ ቀዝቃዛ ሲያልፍ ደግሞ እጅግ ሞቃት ነበር። ቀደምት ሰው በዚህ ሁኔታ ለብዙ ሺህ ዘመናት ኖሯል።
አንዳንድ ሳይንቲስቶች በወቅቱ የነበረው ድርቅ የሰውን ልጅ ከምድረ ገፅ ሊያጠፋ ተቃርቦ ነበር ይላሉ።
አጥኚዎች እንደሚሉት የሰው ልክ ከዚህ ጥፋት የዳነው በአፍሪካ ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው [የኤደን ለምለም ሥፍራ] ተጠልሎ ከውቅያኖስ የሚያገኘውን እየተመገበ ነበር።
በ2020 የፖሊስ ጭካኔ የበረታበት ነበር
ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ በፖሊስ እጅ ከተገደለ በኋላ አሜሪካን ጨምሮ በመላው ዓለም የፖሊስ ጭካኔን የሚቃወሙ ድምፆች ከሌላው ጊዜ በላይ ጎልተው ተሰምተዋል።
ተቃውሞው ናይጄሪያ ደርሷል፣ ኮለምቢያ ገብቷል፣ ፈረንሳይን አጥለቅልቋል፣ ሆንግ ኮንግን አንቀጥቅጧል።
ነገር ግን ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
በ1992 አራት የሎስ አንጀለስ ከተማ ፖሊሶች ሮድኒ ኪንግ የተሰኘውን ጥቁር አሜሪካዊ በጭካኔ ሲቀጠቅጡ የሚታዩበት ምስል ከወጣ በኋላ ከባድ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር።
በዚህ ተቃውሞ ሳቢያ 54 ሰዎች ሞተዋል፤ ግምቱ 1 ቢሊዮን ዶላር የሆነ ንብረት ወድሟል። ይህን ተከትሎ ከተማዋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃ ነበር።
የተረገመው 2020
በአጠቃላይ 2020 በርካታ መከራ ያሳየን ዓመት ሆኖ ሊያልፍ ጥቂት ቀናት ቀርተውታል። ቢሆንም ግን የሰው ልጅ ከዚህ የበለጡ ብዙ መከራና ቸነፈር አልፎ እዚህ ደርሷል።
ዓመቱ የበርካታ ሰዎችን ኑሮ ቢያመሰቃቅልም መልካም የሚባሉ ክስተቶችንም አስተናግዷል።
የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ከየትኛው ጊዜ በላይ የሆነበት ነው 2020።
ሰዎች የዘር መድልዎን በመቃወም አደባባይ ወጥተው ለውጥ ለማምጣት የጣሩበት ዓመትም ሆኖ ተመዝግቧል።
'ዕድሜ' ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተፈጥሮም ውበቷን በዚህ ዓመት መልሳለች።
የሰው ልጅ ከመቼውም ጊዜ በላይ እጁን አብዝቶ የታጠበበት ዘመን ነው 2020።
በቀጣዩ ዓመት ቸር ወሬ ያሰማን።












