"መንግሥት ያለ አይመስልም ነበር"፡ በሰብአዊነት ላይ ወንጀሎች ተፈጽመዋል-ኢሰመኮ

የፎቶው ባለመብት, -
የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ቦታዎች የተፈጸሙ ጥቃቶች በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ናቸው ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዛሬ ባወጣው ሪፖርት አመለከተ።
ኮሚሽኑ እንዳለው ለወራት ክስተቱን በተመለከተ ባደረገው ምርመራ መሰረት ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ "በጥቃቱ በተሳተፉ ሰዎችና ቡድኖች በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸሙት ጥቃቶች በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ባሕርያትን የሚያሟሉ ናቸው" ብሏል።
ለዚህም ሪፖርቱ እንደማሳያነት ከጠቀሳቸው መካከል ለተከታታይ ጊዜያት ቢያንስ በ40 የተለያዩ ቦታዎች በአብዛኛው በቡድን የተደራጁ ሰዎች ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደላቸው፣ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት ማድረሳቸው፣ ንብረት ማውደማቸውና ነዋሪዎችን ማፈናቀላቸው ይገኙበታል።
በተጨማሪም ጥቃቱ ያነጣጠረው በከፊል በብሔርና በሐይማኖታቸው ተለይተው የተመረጡ ሰዎችን ከየቤታቸው ለይቶ በማሳደድና በማጥቃት፣ በከፊል ብሔርና ሐይማኖት ሳይለይ ሰላማዊ ነዋሪዎችን ወይም ሲቪል ሰዎችን ሆነ ብሎ በማጥቃት የተፈጸመ የወንጀል ድርጊት መሆኑ ገልጿል።
የሦስት ልጆች አባት ሆነው ታዋቂው ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ሰኞ ሠኔ 22/2012 ዓ.ም ምሽት አዲስ አበባ ውስጥ ገላን ኮንዶሚኒየም ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ በተተኮሰበት ጥይት ለህልፈት መዳረጉ ይታወሳል።
ኢሰመኮ በሪፖርቱ በወንጀል ድርጊቱ ሲሳተፉ የነበሩት ሰዎች፤ ተግባራቸው ስልታዊና የተቀናጀ ወይም የሰፊ ጥቃት አካል መሆኑን በማወቅ የተሳተፉበት እንደነበር ጠቅሶ፤ እነዚህ በቡድን የተፈፀሙት ጥቃቶች ጠቅላላ ድርጊቶቹና ውጤታቸው በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ የግፍና ጭካኔ ወንጀል መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል።
መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጨምሮም ምርመራ ባደረገባቸው 40 የኦሮሚያ አካባቢዎች፣ የአርቲስቱን ሞት ተከትሎ በነበሩት 3 ተከታታይ ቀናት በተከሰተው የፀጥታ መደፍረስ፣ የ123 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ቢያንስ በ500 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል ብሏል።
ሕይወታቸው ካለፈ ሰዎች ውስጥ 35ቱ በሁከቱ በተሳተፉ ግለሰቦችና ቡድኖች የተገደሉ መሆኑን ኢሰመኮ ጠቅሶ፤ በተጨማሪም ጥቃት ፈጻሚዎቹ በ306 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት አድርሰዋል ብሏል።
በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ እርምጃ ቢያንስ 76 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከ190 በላይ ሰዎች የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው አመልክቶ፤ በፀጥታ መደፍረስ ወቅት በተከሰተ ፍንዳታ፣ ቃጠሎና መሰል አደጋዎች 12 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ሪፖርቱ ገልጿል።
በሁከቱ በህይወትና በሰዎች አካል ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው፣ በግለሰቦች፣ በንግድ ድርጅቶች እንዲሁም በመንግሥት ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ መፈጸሙን የኮሚሽኑ ሪፖርት አመልክቷል።

የፎቶው ባለመብት, -
አሰቃቂ ድርጊቶች
ባለ 64 ገጹ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው በዚህ ዝርዝር ሪፖርት ላይ በጥቃቶቹ ብዙ ቁጥር ያላቸው ከቦታ ቦታ በቡድን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰዎች እንደተሳተፉበት ገልጾ ለድርጊቱም የተለያዩ ነገሮችን መጠቀማቸውን ገልጿል።
ጥቃት አድራሾቹ በሰዎች ላይ ድብደባ መፈጸማቸውን፣ የአካል ጉዳት ማድረሳቸውንና "ፍጹም ግፍና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በማሰቃየት ወይም በማረድ ጭምር ሰዎችን ገድለዋል" ሲል ድርጊቱ በሰለባዎቹ ቤት ውስጥና በመንገድ ላይ ጭምር የተፈጸመ እና አሰቃቂ እንደነበር ገልጿል።
አክሎም አጥቂዎቹ ከፈጸሙት ድብደባ፣ ግድያና ንብረት ማውደም በተጨማሪ ተጎጂዎችንና የተጎጂ ቤተሰቦችን "ብሔርን መሰረት ያደረጉ ስድቦች ሲሳደቡ፣ ሲያንቋሽሹ፣ ሲያስፈራሩና ሲዝቱባቸው" እንደነበር ሪፖርቱ ጠቅሶ ይህም ሰላማዊ ነዋሪዎች በብሔር ወይም በሐይማኖታቸው ምክንያት ለጥቃት የመጋለጥ ከፍተኛ ስጋትና የሥነ-ልቦና ጭንቀት እንደፈጠረባቸው ኢሰመኮ መገንዘቡን ጠቅሷል።
ይህ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ይፋ የተደረገው ሪፖርት እንደሚለው የጥቃቱ ባሕሪና መጠን እንደ የአካባቢው ሁኔታ የሚለያይ ቢሆንም "በአመዛኙ የክርስቲያን እምነት ተከታዮች በብዛት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ጥቃቱ በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፤ የእስልምና እምነት ተከታዮች በብዛት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ደግሞ በኦርቶዶክስ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ላይ ያነጣጠረ ነበር" ብሏል።
ጥቃቱ በተፈጸመበት ጊዜ ቀድሞ ከመከላከልና ከማስቆም አንጻር የፀጥታ ኃይሎች የነበራቸው ሚና ከቦታ ቦታ የተለያየ መሆኑን ያመለከተው ሪፖርቱ "በተወሰኑ አካባቢዎች የፀጥታ ኃይሉ ቅድመ ዝግጅት በማድረጉ ጉዳቱን ለመከላከል፣ ለማስቆም ወይም ለመቀነስ ተችሏል" ሲል ገልጿል።
በአንጻሩ በተለይ ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የነዋሪዎችና ተጎጂዎች ለየአካባቢው አስተዳደርና ለፀጥታ አካላት በተደጋጋሚ እርዳታ ቢጠይቁም አዎንታዊ ምላሽ አለማግኘታቸውን አመልክቷል።
ይልቁንም "በበላይ አካል አልታዘዝንም፣ የግለሰብ ንብረት ጠብቁ አልተባልንም፣ የምንጠብቀው የመንግሥትን የልማት ተቋማትን፣ ባንኮችን እና የሐይማኖት ተቋማትን ነው" የሚል ምላሽ ሲሰጣቸው እንደነበር ኮሚሽኑ መረዳቱን ገልጾ፤ በተወሰኑ ቦታዎች ፖሊስ ጥቃቱን እያየ በዝምታ ማለፉን በመጥቀስ የዓይን እማኞች በምሬት "መንግሥት ያለ አይመስልም ነበር" ማለታቸውን አመልክቷል።
የየአካባቢዎቹ የፀጥታ አካላትና የመንግሥት ኃላፊዎች ጥቃቱ ድንገተኛና በብዙ ስፍራዎች ብዙ ቁጥር ያላችው ሰዎች የተሳተፉበት ስለነበር በሚፈለገው መጠንና ፍጥነት ለማስቆም አስቸጋሪ እንደነበር መናገራቸውን የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ ነዋሪዎችን ከዚህ አይነት ጥቃት አስቀድሞ ለመከላከል "በክልሉ መንግሥት የተደረገ በቂ ዝግጅት አለመኖሩ፣ በተለይ ቀደም ሲል መሰል ብሔርንና ሐይማኖትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በተፈጸሙባቸው ቦታዎች አንዳችም ዝግጁነት አለመኖሩ ዜጎችን በአሳዛኝ ሁኔታ ለተደጋጋሚ ጥቃትና በደል አጋልጧል" ብሏል።
የፀጥታ አካላት ኃይል አጠቃቀም
በየቦታው የተከሰተውን የፀጥታ መደፍረስ ለፀጥታ ኃይሉ ኃላፊነቱን ለመወጣት እጅግ ፈታኝ የነበረ መሆኑን የገለጸው ሪፖርቱ፤ ነገር ግን በተወሰኑ ቦታዎች የነበረው "የኃይል አጠቃቀም ተመጣጣኝነት ከፍተኛ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው" ብሏል።
የፀጥታ አካላት ኃይል አጠቃቀምን በተመለከተ በሪፖርቱ ላይ እንደተጠቀሰው ሁከት ባጋጠመባቸው በተለያዩ ስፍራዎች "በመንግሥት የፀጥታ አካላት ጭንቅላታቸው፣ ግንባራቸው፣ ደረታቸውና ጀርባቸው ላይ በጥይት ተመትተው የተገደሉ ሰዎች" እንደሚገኙ ጠቅሶ፤ ከተጎጂዎች መካከል ምንም ተሳትፎ ያልነበራቸው ሰዎች በመንገድ ወይም በቤታቸው በር ላይ የተገደሉ፣ የአገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ የአዕምሮ ህመምተኛና ሕፃናት ይገኙበታል ብሏል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በሪፖርቱ ላይ ጨምሮም በተወሰኑ አካባቢዎች በተፈጠረው ሁከት ውስጥ መሳሪያ የያዙ፣ ጥይት የተኮሱ፣ ቦምብ የወረወሩ መኖራቸውንና በዚህም የተነሳ የፀጥታ ኃይል አባላት መቁሰላቸውንና መገደላቸውን ጠቅሶ፤ ይህም የፀጥታ ኃይል አባላት የጦር መሳሪያ እንዲጠቀሙ ያስገደደ ሁኔታ እንደነበር መገመት ይቻላል ብሏል።
በዚህም በአብዛኞቹ አካባቢዎች የፀጥታ ኃይል አባላት መለስተኛ ጉዳት በሚያስከትሉ መሳሪያዎች ሳይሆን፣ ሕይወት ሊያጠፋ የሚችል መሳሪያዎች መጠቀማቸው ለሰልፈኞቹ፣ በአካባቢው ለነበሩ ሰዎችና ለየፀጥታ ኃይል አባላቱ ጭምር የሕይወትና የአካል ደኅንነት አደጋን መፈጠሩን ገልጿል።
ይህንንም ተከትሎ ኮሚሽኑ ምርመራውን ባደረገባቸውና የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ የሰው ሕይወት በጠፋባቸው አካባቢዎች "በፌዴራል ወይም በክልል መንግሥት አካላት የደረሰውን የሕይወት መጥፋት ምርመራ በማድረግና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የተጀመረ ሥራ መኖሩን ለማረጋገጥ አልቻለም" በማለት የተወሰደ እርምጃ አለመኖሩን ገልጿል።
ምክረ ሐሳብ
በዝርዝር ሪፖርቱ ላይ ከአርቲስት ሃጫሉ ግድያ በኋላ በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጸመውን ጥቃት "በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል" በማለት የገለጸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የፌደራል መንግሥቱና የክልሉ መንግሥት መውሰድ ያለባቸውን እርምጃዎችን ጠቁሟል።
በዚህም መሠረት በኮሚሽኑ የቀረቡ መረጃዎችን በመመርኮዝ የወንጀል ምርመራ በማድረግ በጥቃቶቹ የተጠረጠሩ ሰዎች ተለይተው ተጠያቂ እንዲሆኑና በኦሮሚያም ሆነ በሌሎችም ክልሎች ተመሳሳይ "የግፍና የጭካኔ ወንጀል ሊከሰት እንደሚችል በመገንዘብ" መከላከል የሚያስችል የተቀናጀ የቅድመ ማስጠንቀቂያና የመከላከያ ሥርዓት እንዲዘረጋ አሳስቧል።
በተጨማሪም ሪፖርቱ በአገሪቱ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር "የዘር ማጥፋት ወንጀልን ጨምሮ የዚህ አይነት የግፍና ጭካኔ ወንጀሎች ስጋት መኖሩን የሚያመላክት ስለሆነ" መንግሥት ከባለድርሻ አካላትጋር በመተባበር እንዲህ አይነት የግፍና የጭካኔ ወንጀል መከላከያ ስትራቴጂ አዘጋጅቶ ሥራ ላይ እንዲያውል ጠይቋል።
በተጨማሪም ኮሚሽኑ ካወጣው ሪፖርት አንጻር የአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ጨፌ ኦሮሚያ እንዲሁም መገናኛ ብዙሃንና የማኅበረሰብ አንቂዎች ከዚህ በፊት ስለተፈጸመው ጥቃትና ወደፊት ሊያጋጥም ከሚችለው ተመሳሳይ ክስተት አንጻር ማድረግ የሚጠበቅባቸውን በዝርዝር በሪፖርቱ ላይ አመልክቷል።
የሃጫሉ ግድያ
አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ በጥይት ከተመታ በኋላ በኋላ የህክምና እርዳታ እንዲያገኝ ወደሚገኘው ሆስፒታል ቢወሰድም ህይወቱ ሊተርፍ እንዳልቻለ ፖሊስ በወቅቱ አስታውቆ ነበር።
ግድያውን ተከትሎ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በድምጻዊው ሞት የተሰማቸውን ሀዘን "ውድ ህይወት አጥተናል" በማለት ድንጋጤና ሐዘናቸውን የገለጹ ሲሆን ከፍተኛ የአገሪቱ ባለስልጣናትም ሐዘናቸውን በወቅቱ ገልጸው ነበር።
ሃጫሉ በኦሮሚኛ ሙዚቃዎቹ ታዋቂነትና ተወዳጅነትን አትርፎ የነበረው ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ በተለይ በኦሮሚኛ ተናጋሪው ዘንድ በሥራዎቹ ከፍ ያለ ተወዳጅነትን ለማግኘት ችሎ ነበር ስለነበር የሞቱ ዜና እንደተሰማ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ ቁጣና ሐዘን ተፈጥሮ ነበር።
በዚህም ሳቢያ በተለያዩ ቦታዎች ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ከተከሰተ ግጭትና በነዋሪዎች ላይ ከተፈጸሙ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና አባላትን ጨምሮ አስር ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በተለያዩ አካባቢዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው በወቅቱ መገለጹ ይታወሳል።
ከግድያው ጋር ተያይዞ አለመረጋጋቱ በተከሰተበት ጊዜ በአገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎት ለሳምንታት ተቋርጦ ነበረ።
አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ከተገደለ ከቀናት በኋላ ወንጀሉን ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሦስት ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑ ይታወቃል።
አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሰኔ 22/2012 ዓ.ም መገደልን ተከትሎ በአዲስ አበባና በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ለቀናት በተከሰተው ሁከትና አለመረጋጋት የበርካታ ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት ለውደመትና ለዝርፊያ መዳረጉን ቀደም ሲል የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።















