የአሜሪካ ምርጫ 2020፡ የጆርጂያ ግዛት ምርጫ ለምን አሜሪካውያንን አስጨነቀ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ከየግዛቱ እኩል 2 እንደራሴዎች የሚሞሉት የመቶ ወኪሎች ሸንጎ ነው። ይህ ምክር ቤት የፕሬዝዳንቱ ልጓም ነው ማለት ይቻላል። ባለ ትልቅ ሥልጣን ነው። ፕሬዝዳንቱ አገሪቱን ባሻቸው አቅጣጫ እንዳይጋልቧት ያደርጋል።
ሃምሳዎቹ የአሜሪካ ግዛቶች እያንዳንዳቸው ሁለት ወኪሎችን አስመርጠው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱን ይሞሉታል። ድምሩ ድፍን 100 ይመጣል። ለታችኛው ምክር ቤት ግን የግዛቶች ውክልና በሕዝብ ቁጥር ነው።
በአሁኑ ጊዜ 50ዎቹ እንደራሴዎች የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ናቸው። 48ቱ ደግሞ የዲሞክራት ፓርቲ አባላት ናቸው።
ሁለቱ ገለልተኛ ነን የሚሉ እንደራሴዎች ሲሆኑ አንገስ ኪንግ ከሜይን ግዛት እና በርኒ ሳንደርስ ከቬርሞንት ግዛት የተወከሉ ናቸው።
የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ የሚያጸድቀው ቁልፍ ጉዳይ ሲኖር ብዙዉን ጊዜ ሁለቱ ገለልተኛ የሸንጎው አባላት ከዲሞክራቶች ጋር ይወግኑና ድምጽ ሲሰጥ 50 ለ 50 እኩል ይሆናል። ፍጥጫ!
በዚህ ጊዜ ወሳኙ የመለያ ድምጽ ከየት ነው የሚመጣው? ከምክትል ፕሬዝዳንቱ ማይክ ፔንስ።
በሕግ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ሰብሳቢ ነው። ስለዚህ የፔንስ ድምጽ ቁልፍ ሚና የሚኖረው ለዚህ ነው።
ከ15 ቀናት በኋላ ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስን ካምላ ሐሪስ ትታካቸዋለች። የካምላ ድምጽ እጅግ ቁልፍ እንዲሆን ከጆርጂያ ሁለት ወኪሎች ሸንጎውን መቀላቀል አለባቸው። ቢያንስ እኩሌታዎቹ ዲሞክራቶች እንዲሆኑ።
የዲሞክራቶች የበላይነት በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ውስጥ እንዳይኖር ለማድረግ ዲሞክራቶች ሁለት ወኪሎችን እዚህ ሸንጎ ውስጥ ማስገባት ስላለባቸው ነው አሁን ጭንቅ የተፈጠረው።
ይህ ዛሬ እየተደረገ ያለው የጆርጂያ ምርጫ ለዲሞክራቶችና ለሪፐብሊካን ፓርቲዎች የሞት ሽረት ትግል የሆነውም ለዚሁ ነው።
የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ወሳኝ ፖሊሲዎችን ለማጸደቅ፣ የሕግ ማዕቀፎችን በድምጽ ለማሳለፍ፣ የከፍተኛ ባለሥልጣናትን ሹመቶችን ለማጸደቅ፣ ፕሬዝዳንቱን አስፈላጊ ሲሆን ለመክከሰስ፣ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞችን ሹመት ለማጽደቅ ወሳኙ ይህ የላዕላዩ ሸንጎ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሪፐብሊካኖች ይህን ሸንጎ ከ2014 ጀምሮ እንደተቆጣጠሩት ነው ያሉት።
ልክ ዲሞክራቶች ታችኛውን ምክር ቤት እንደተቆጣጠሩት ሁሉ ላይኛው ምክር ቤት የሪፐብሊካኖች መፈንጫ አዳራሽ ሆኖ ነው የቆየው።
ይህ ሁኔታ ቢቀየር ዲሞክራቶች፣ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት፣ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤትና ነጩን ቤተመንግሥት የግላቸው አደረጉት እንደማለት ነው።
ይህ ጆ ባይደንን እጅግ ጉልበተኛው ፕሬዝዳንት ሊያደርጋቸው ይችላል። ጆ ባይደን ቢያንስ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ሕይወታቸው ቀላል ይሆንላቸዋል።
ነገሩን ገልብጠን ብናስበው ደግሞ ሪፐብሊካኖች የላዕላይ ምክር ቤቱን ብልጫ ይዘው፣ የአብላጫ መቀመጫ ወኪሉ ሚች ማኮኔል በሚመሩት ሸንጎ ውስጥ ሁለት ዓመት እንዲቀመጡ ቢፈቀድ ባይደን የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት የጭንቅ ዓመታት ይሆኑባቸዋል።
ምክንያቱም ሪፐብሊካኖች የጆ ባይደን አጀንዳዎች ከሕግ መምሪያ ምክር ቤት አልፈው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ሲደርሱ ሊታነቁባቸው ይችላሉና ነው።
ለዚህ ነው የዛሬው የጆርጂያ ግዛት የእንደራሴ ምርጫ ጭንቅ የሆነው።
ለምሳሌ በጆርጂያ ሁለቱ ተወካዮች ከሪፐብሊካን ቢሆኑ ባይደን ከዚያ በኋላ እያንዳንዱን አጀንዳ በምክር ቤቱ በኩል አጸድቆ ለማሳለፍ ሲሹ ሁልጊዜም ሁለት ሦስት ሪፐብሊካን እንደራሴዎችን ማባበልና መለማመጥ ሊኖርባቸው ይችላል።
ይህን የፖለቲካ ልምምጥ ለማስቀረት የዛሬው የጆርጂያ ምርጫ ወሳኝ ሆኗል።
አሁን ሁለቱም ፓርቲዎች የጆርጂያን ውጤት በጭንቀት እየጠበቁ ያሉት ከዚህ አንጻር ነው። ሁለቱም ፓርቲዎች በሙሉ ጉልበት እየቀሰቀሱ ሰንብተዋል።
እንዲያውም ሪፐብሊካኖች ለማስታወቂያ ብቻ እስከ 400 ሚሊዮን ዶላር ፈሰስ አድርገዋል ነው የሚባለው።

የፎቶው ባለመብት, EPA
በጆርጂያ እየተፎካከሩ ያሉት እነማን ናቸው?
ጆርጂያ ግዛት የሪፐብሊካን ታማኝ ይዞታ ሆና ነው የቆየችው። ባይደን ናቸው ታሪኩን የቀየሩት።
አትላንታ የሚገኙት ተመራጩ ፕሬዝዳንት መራጮችን "ዲሞክራቶቹን እጩዎች መርጣችሁ ታሪክ ሥሩ" እያሉ ሲቀሰቅሱ ነበር።
ተመራጯ ምክትል ፕሬዝዳንት ካምላ ሐሪስም ጆርጂያ ነው ያሉት። ከፍተኛ ቅስቀሳ ይዘዋል።
ጆርጂያ ለሕግ መወሰኛውም ምክር ቤት የወከለቻቸው ሁለት እጩዎች ሪፐብሊካን ነበሩ። አሁን በሚደረገው ምርጫ ላይ ወንበራቸውን ለማስጠበቅ እየተፋለሙ ነው ያሉት።
አንደኛው ዴቪድ ፐርዲዩ ናቸው። ከ2015 ጀምሮ በሸንጎው ውስጥ ቆይተዋል። እሳቸውን አስወጥቶ ለመግባት እየሞከረ ያለው ወጣቱ ጆን ኦሶፍ ነው። ቀድሞው ጋዜጠኛ ጆን 33 ዓመቱ ነው።
ሁለቱ እጮዎች በቅስቀሳ ላይ መዘላለፍ አብዝተዋል። የዲሞክራቱ እጩ ጆን ሚስተር ዴቪድን በሕገ ወጥ ንግድ ይከሳቸዋል። እሳቸው የቀድሞ የሪቡክ ብራንድ ሥራ አስፈጻሚ ነበሩ።
ሁለቱ እጩዎች የቴሌቪዥን የቀጥታ ክርክር ለማድረግ ተቀጣጥረው አልተሳካላቸውም። የሪፐብሊካኑ ዴቪድ ሊገኝ አልቻለም።
ሌሎቹ ሁለቱ ተፎካካሪዎች የሪፐብሊካኑ ኬሪ እና የዲሞክራቱ ሬፍ ራፋኤል ዋርኖክ ናቸው።
ኬሪ እውቅ ሀብታም ሴት ናት። የቅርጫት ኳስ ቡድንን በባለቤትነት የምታስተዳድር አዱኛ የበዛላት ባለሀብት ናት።
ዋርኖክ በበኩሉ በጆርጂያ የመጀመሪያው ጥቁር እንደራሴ ለመሆን ነው እየተፎካከረ ያለው። ዋርኖክ በአትላንታ የአቤኔዘር ቤተክርስቲያን ሰባኪ ሲሆን፤ እንደ ታላቁ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ሁሉ እሱም እውቅናው ከቤተክርስቲያን የሚነሳ ነው።
በነገራችሁ ላይ ማርቲን ሉተር ኪንግ ድሮ በዚህ የአቤኔዘር ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው መስበክ የጀመረው። አባቱም የዚህ ቤተክርስቲያን መሥራች ነበሩ።
ራፋኤል ዋርኖክ ልክ እንደ ማርቲን ሁሉ እውቅ የጥቁሮች መብት ተቆርቋሪ ከመሆኑም በላይ "የብላክ ላይቭስ ማተር" ንቅናቄ ንቁ ደጋፊ ነው።
ከአነጋገሩ ጀምሮ ብዙ ነገሮቹ ከዝነኛ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ጋር ይመሳሰላል ይላሉ የአሜሪካ ሚዲያዎች።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በጆርጂያ ለምን ድጋሚ ምርጫ ይደረጋል?
በጆርጂያ ግዛት የምርጫ መተዳደርያ ሕግ ዕጩዎች ከ50 በመቶ በታች የነዋሪ ድምጽ ካገኙ ምርጫው ይደገማል ይላል።
ባለፈው ኅዳር ወደ ውድድር የገቡት ዕጩዎች ታዲያ አንዳቸውም 50 ከመቶ ድምጽ ሊያገኙ አልቻሉም።
ሊዮፍለር እና ዋርኖክ እየተወዳደሩ ያሉት ግን በጤና ምክንያት አንድ የጆርጂያ እንደራሴ በገዛ ፈቃዳቸው ውክልናቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ነው።
ባለፈው ምርጫ ዲሞክራቱ ዋርኖክ ያገኙት ድምጽ 32.9 በመቶ ሲሆን ኬሊ ሊዮፍለር 25.9 በመቶ ድምጽ በማግኘት 2ኛ ሆናለች።
በሌላኛው ውድድር ደግሞ ዴቪድ ፕርዱዩ 49.3 በመቶ ሲያገኝ ጆን ኦሶፍ 47.95 ከመቶ ድምጽ ማግኘት ችለው ነበር። ሁሉም ያገኙት ድምጽ ከ50 ከመቶ በታች በመሆኑ ድጋሚ ምርጫው ዛሬ ሊሆን ችሏል።
ላለፉት 20 ዓመታት በጆርጂያ አንድም እንደራሴ ከዲሞክራቲክ ፓርቲ ወጥቶ ያሸነፈና ወደ ላዕላይ ምክር ቤት መግባት የቻለ የለም።
እንኳንስ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ይቅርና ለፕሬዝዳንቶችም ደቡባዊ አሜሪካ ጆርጂያ ፈተና ሆና ነው የኖረችው።
ጆ ባይደን በጆርጂያ ሲያሸንፉ ከ30 ዓመት በኋላ መሆኑ ስለ ግዛቱ ምንነትና ማንነት ብዙ ይነግረናል።
ጆ ባይደንም ሆኑ ትራምፕ የጆርጂያ ውጤት ለሚቀጥሉት ረዥም ዓመታት አሜሪካ ምን እንደምትመስል የሚወስን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ ጽሑፍ እስኪጠናቀር ድረስ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ ጆርጂያዊያን ድምጽ ሰጥተዋል። ይህም ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገበው ሕዝብ 40 እጁ ይሆናል።
ሪፐብሊካኑ ኬሊና ዴቪድ አሁን የሸንጎው አባል ናቸው። ከሸንጎው ሊፈነቅሏቸው እየተጉ ያሉት ጆን እና ጥቁሩ ዋርኖክ ናቸው።
ትናንት ሰኞ ጆ ባይደን በጆርጂያ ዋና ከተማ አትላንታ ቅስቀሳ ሲያደርጉ "ጆርጂያ መላው አሜሪካ አንቺን እየተመለከተ ነው። በረዥም የፖለቲካ ሕይወቴ አንድ ግዛት 4 ዓመትን ብቻ ሳይሆን የመላው አሜሪካንን የፖለቲካ እጣ ፈንታ ሲወስን አይቼ አላውቅም፤ ጆርጂያ አንቺ የመጀመሪያዋ ነሽ" ሲሉ ሕዝቡ ድምጽ እንዲሰጣቸው ተማጽነዋል።
ይህን ሲናገሩ የዲሞክራቶቹ እጩዎች ጆን እና ዋርኖክ በግራና ቀኝ አብረዋቸው ቆመው ነበር።
ዶናልድ ትራምፕም ወደ ጆርጂያ ወርደዋል። በቅስቀሳ ወቅት ባደረጉት ንግግር "ጆርጂያ የመጨረሻዋ የሪፐብሊካኑ ምሽግ" ሲሉ ነገሩን ከጦርነት ጋር አነጻጽረውታል።
የሪፐብሊካን እና የዲሞክራቶች የአሁኑ ጊዜያዊ የሸንጎ ቁጥር 52 ለ 48 ነው። ዛሬ ማታ ወይም ነገ በሚታወቀው ውጤት ሁለቱም የዲሞክራቲክ እጩዎች ድል ቢቀናቸው አሜሪካ የዲሞክራቶች አገር ሆነች የማለት ያህል ነው።















