አሜሪካ፡ ለትራምፕ የጎን ውጋት ሆነው የቆዩት ናንሲ ፔሎሲ ማን ናቸው?

ናንሲ ፔሎሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ካፒቶል ሂል የአሜሪካ 4 ኪሎ ማለት ነው። ቦታው የወንዶች የፖለቲካ አውድማ ሆኖ ነው የቆየው።

አሜሪካ "ሴቶች ወደ ማጀት" ማለት ካቆመች መቶ ዓመት ቢሆናት ነው።

በዚህ ዘመን የወንዶች ብቻ ተደርጎ የሚታሰበውን የፖለቲካ መድረክ እንደ ፔሎሲ ገብቶ ለማተራስ የበቃ ሴት ፖለቲከኛ የለም።

አሁን ፔሎሲ 80 ዓመታቸው ነው። በአፈ ጉባኤነት ለ4ኛ ዘመናቸው ተመርጠው ዜና ሆነዋል። ለማንም የማይመለሱ ብርቱ ሴት ናቸው። የካፒቶል ሂል ፖለቲከኞች ፔሎሲን ሲመለከቱ የሚናወጡት የሴትዮዋን ጥንካሬ አሳምረው ስለሚያውቁ ነው።

ሕግን ጠፍጥፎ የሚጋግረውና አብስሎ የሚያወጣው የታችኛው ምክር ቤት የ435 እንደራሴዎች የሙግት ቤት ነው።

ይህን የሙግት ምክር ቤት የሚመሩት ደግሞ እኚህ ብርቱ ሴት ናቸው።

የሕግ መምሪያው ምክር ቤት የአፈ ጉባኤ የሥልጣን ዘመን 2 ዓመት ነው።

ፔሎሲ እንደ አውሮፓዊኑ በ2007 ተመርጠው 2 የሥልጣን ዘመን አገልግለዋል።

ከዚያ ወዲያ በ2019 ተመልሰው መጥተው አሁን ለ4ኛ ዙር ተመርጠዋል፤ በትናንትናው ዕለት።

ፔሎሲ የዋዛሴት አይደሉም። 50 ዓመታት በአሜሪካ ፖለቲካ የጽኑ ብርቱ ሴት ናቸው። 50 ዓመት ከዲሞክራቲክ ፓርቲ ጋር ተጣምረው ኖረዋል።

ካምላ ሐሪስ መጥተው በአሜሪካ ፖለቲካ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ከመክፈታቸው፣ የፖለቲካ ሥልጣን ከመቆናጠጣቸው በፊት በአሜሪካ ቁጥር አንድ ኃያሏ ሴት ፖለቲከኛና ተጽዕኖ ፈጣሪ ማን ነበሩ ቢባል መልሱ ናንሲ ፔሎሲ እንጂ ሌላ አይሆንም።

አሁን የዲሞክራቶች ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት መግባትን ተከትሎ ናንሲ ፔሎሲ ወሳኝ ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል።

ለዲሞክራቶቹ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆ እና ምክትላቸው ሐሪስ የሚስማሙ አጀንዳዎችን ወደ ፊት ማምጣት። ማቀበል፣ ማስወሰን፣ ወዘተ ይኖርባቸዋል።

የአሜሪካ የታችኛው ምክር ቤት አሁንም ድረስ የዲሞክራት እንደራሴዎች ብልጫ ያለበት ቢሆንም ቁጥሩ ከቀድሞው ተመናምኖ ድንጋጤ ፈጥሯል።

ዲሞክራቶች ታችኛውም ሆነ ላይኛው ምክር ቤት አብላጫነት ከእጃቸው ተንሸራቶ ሊወጣ ጫፍ ላይ ነው ያለው።

ናንሲ ፔሎሲም ቢሆን ለ4ኛ ጊዜ በአፈ ጉባኤነት ሲመረጡ የተወሰኑ የእኔ የሚሏቸው ዲሞክራቶች ድምጽ ነስተዋቸው ለጥቂት ነው ያሸነፉት፤ እንጂማ ጉድ ሆነው ነበር።

በጠባብ ልዩነት ማሸነፋቸው የናንሲ ፔሎሲ መጪዎቹ 2 ዓመታት ፈተና እንዴት ያለ እንደሚሆኑ አመላካች ነው ተብሏል።

ከቤት እመቤትነት እስከ ብርቱ ፖለቲከኛነት

ፔሎሲ የተገኙት ፖለቲካ የዕለት ተዕለት ቀለቡ ከሆነ ቤተሰብ ነው።

ገና የ12 ዓመት አዳጊ እያሉ ፔሎሲ የዲሞክቲክ ፓርቲ ስብሰባ ላይ ተገኝተዋል። ልጅ እያሉ በሪፐብሊካን ባንዲራ ያጌጠ አሻንጉሊት አልቀበልም እንዳሉ በአፈ ታሪክ ይነገርላቸዋል።

ጥብቅ ካቶሊክ እንደሆኑ የሚነግርላቸው ፔሎሲ በ20 ዓመታቸው ከጆን ኤፍ ኬኔዲ ጋር ተዋውቀዋል።

ብዙ ሰዎች እሳቸውን ከድሀውና ከጭቁኑ አሜሪካዊ የራቁ፣ ግራ ዘመምነት በጭራሽ የማይታይባቸው "የሳንፍራንሲስኮ ለዘብተኛ" እያሉ ይጠሯቸዋል። እውነታው ግን ያ አይደለም።

ፔሎሲ 6 ወንዶች ከሚገኙበት ትልቅ ቤተሰብ ውስጥ የመጨረሻ ሴት ልጅ ሆነው ነው ያደጉት።

በምሥራቃዊ አሜሪካ ሜሪላንድ፣ ባልቲሞር ነው የተወለዱት። አባቷ ደንበኛ ዲሞክራት ነበሩ።

አባቷ ቶማስ ዴ አሌሳንድሮ የባልቲሞር ከተማን ለ12 ዓመታት በከንቲባነት መርተዋል። አባቷ ብቻ ሳይሆን ወንድሟ ቶማስ ዴ አሌሳንድሮም ባልቲሞርን በከንቲባነት መርተዋል።

ፖለቲካ ወደ ፒሎሲ የተሸጋገረው በእውቀት ብቻ ሳይሆን በቤተሰብም ነው የሚባለው ለዚህ ነው።

ፔሎሲ ከዚያ በኋላ ዋሺንግተን ጆርጅ ታውን ኮሌጅ ገብተው ተማሩ። የአሁን ባላቸውን ፖል ፔሎሲን ያገኙትም እዚያው ኮሌጅ ነበር።

መጀመርያ ወደ ማንሐተን ከዚያም ወደ ሳንፍራንሲስኮ ሄደው መኖር ጀመሩ። ያን ጊዜ የቤት እመቤት ነበሩ።

አምስት ልጆችን በተከታታይ አፍርተዋል። አራቱ ሴቶች ናቸው። በአንድ አንድ ዓመት ልዩነት ነው ልጆቹን የወለዷቸው።

ፔሎሲ በ1976 ነበር ለመጀመርያ ጊዜ ፖለቲካ ውስጥ የገቡት።

የካሊፎርኒያው ገዥ ጄሪ ብራውን የምረጡኝ ቅስቀሳ ላይ ነበሩ። እርሳቸውን በማገዝ ፖለቲካን 'ሀ' ብለው ጀመሩ።

ከዚያ በኋላ በሜሪላንድ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ውስጥ ሊቀመንበር ከዚያም ደግሞ ኮንግረስ ተመራጭ ሆኑ። ይህም በ1988 ነበር የሆነው።

ናንሲ ፒሎሲ በቢል ኪሊንተን የሥልጣን ዘመን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በ2011 በታችኛው ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ለመሆን ተወዳደሩ። ይህ ሥልጣን በሕግ መምሪያው ምክር ቤት ውስጥ ሁለተኛው ትልቁ ሥልጣን ነበር።

በቀጣይ ዓመት ደግሞ በሕግ መምሪያ ምክር ቤት ውስጥ የተቃዋሚ ፓርቲ ተጠሪ ሆነው ተመረጡ።

ይህም ማለት በሕግ መምሪያ ምክር ቤት ውስጥ አነስተኛ መቀመጫ ያለውን ፓርቲ የመምራት ሥልጣን ማለት ነው።

ፔሎሲ በ2003 ትንሹ ቡሽ ኢራቅን ለመውረር ሲነሱ አምርረው ወረራውን በመቃወማቸው በይበልጥ ይታወሳሉ።

የእርሳቸው የያኔው አቋም በኋላ ላይ ወረራው ባስከተለው ጉዳት ተረጋግጧል።

ይህም የማይናወጥ አቋማቸው በ2006 ዲሞክራቶች ወደ ሥልጣን እንዲመጡና የሕግ መምሪያ ምክር ቤቱን ከ12 ዓመታት በኋላ በበላይነት እንዲይዙት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ከዚያ በኋላ በፓርቲያቸው የሕግ መምሪያው ምክር ቤት ተመራጭ ሆነው ረዥሙን የአፈ ጉባኤነት ሥልጣን ያዙ። በአሜሪካ ታሪክም የመጀመርየዋ ሴት አፈ ጉባኤ በመሆን አዲስ ታሪክ ሠሩ።

እሳቸው ሥልጣን በያዙ ከ4 ዓመት በኋላ ዲሞክራቶች የሕግ መምሪያውን ምክር ቤት ቁጥጥር ከእጃቸው ወጣ።

ፔሎሲ እጅ አልሰጥ ብለው ብዙ ትግል አደረጉ። ከዚህ ወዲያ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ በ2018 ዲሞክራቶች በምክር ቤቱ ተመልሰው መጡ።

የሕግ መምሪያው ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሥራ ምንድነው?

የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ መሆን ማለት በአሜሪካ የሥልጣን እርከን ከምክትል ፕሬዝዳንቱ ቀጥሎ ያለ ትልቅ ኃላፊነት ነው።

በካፒቶል ግቢ በተንጣለለው የምክር ቤቱ ሕንጻ የፔሎሲ ቢሮ ስፋት የሥልጣናቸውን ግዝፈት የሚያመላክት ነው ማለት ይቻላል።

የራሱ የሆነ ግዙፍ ባልኮኒ ያለውና በረንዳውም ወደ ዋሺንግተን ሐውልት የሚያሳይ ነው።

በሕግ ማውጣት ሂደት ውስጥ ዋናው ይህ የታችኛው ምክር ቤት ነው።

አፈ ጉባኤዋ እና ምክትላቸው እንዲሁም ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ተማክረው የትኛው ረቂቅ ሕግ ድምጽ ይሰጥበት በሚለው ላይ ይወስናሉ።

የመወያያ አጀንዳ የሚቀርጹት እርሳቸው ናቸው። ክርክሮች የሚመሩበትን ሕግ የሚወስኑትም አፈ ጉባኤዋ ናቸው። ምክር ቤቱ ዱላ ቀረሽ ክርክር ሲያደርግ እንደራሴዎችን አደብ የሚያሲዙ እርሳቸው ናቸው።

አፈ ጉባኤዋ በሕግ መምሪያው ምክር ቤት ውስጥ የፓርቲያቸውን የበላይነት እስካስጠበቁ ድረስ የመረጧቸው ረቂቆች ሕግ የማድረግ ጋሬጣ ላይጋረጥባቸው ይችላል።

አነዚህ ምክር ቤት የሚወስናቸው ውሳኔዎች በአሜሪካ ሕዝብ ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ የመፍጠር አቅም አላቸው።

ለምሳሌ ፔሎሲ አፈ ጉባኤ ሳሉ ከ2009 እስከ 2011 ድረስ ብቻ ምክር ቤቱ 840 ቢሊዮን ዶላር የምጣኔ ማነቀቂያ ገንዘብ እንዲረጭ ውሳኔ አሳልፏል።

ፔሎሲ ተመጣጣኝ የጤና መድኅን (Affordable Care Act) ተግባራዊ እንዲሆን ታላቅ ተጋድሎ ያደረጉ የኦባማ ቀኝ እጅ የነበሩ ብርቱ ሴት ናቸው። ለትራምፕ ደግሞ የጎን ውጋት።

ናንሲ ፒሎሲ ከፕሬዝዳንት ኦባማ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Alamy

ሎሲ የስላቅ ጭብጨባ

ፔሎሲ በ2018 ወደ ምክር ቤቱ የአፈ ጉባኤነት መዶሻቸውን ይዘው ሲመለሱ ነገሮች ተቀያይረው ነበር የጠበቋቸው።

ፕሬዝዳንት ትራምፕና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ተጠሪ ሚች ማኮኔል ለፔሎሲ ደንቃራ ሆኑባቸው።

በሕግ መምሪያ ምክር ቤት በእርሳቸው አርቃቂነት አብላጫ ድምጽ ተሰጥቶባቸው ወደ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ሲላኩ ውድቅ እየተደረጉ ተቸገሩ።

ከሕግ መወሰኛ ሲያልፍ ደግሞ ትራምፕ ጠልፈው ይጥሉት ጀመር።

ከዚህ ወዲያ ትራምፕና ፔሎሲ ተቃቃሩ። ይህ መቃቃራቸውም አንዳንድ ጊዜ ግላጭ ከመውጣቱ የተነሳ ለአሜሪካ ሚዲያ መዝናኛ ሆነ።

ለምሳሌ #PelosiClap (የፔሎሲ የሹፈት ጭብጨባ) የሚለው የኢንተርኔት የስላቅ ኢሞጂ የተፈጠረው በዚህን ጊዜ ነበር።

ፔሎሲ የስላቅ ጭብጨባውን ያደረጉት ዶናልድ ትራምፕ በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ወቅት ተንኳሽ ንግግር ባደረጉበት ቅጽበት ነበር።

ፔሎሲ በዚህን ጊዜ ገና ሥልጣኑን ከያዙ አንድ ወራቸው ነበር።

ዛሬም ድረስ ይህ የናንሲ ፔሎሲ የስላቅ ጭብጨባ የኢንተርኔት ተወዳጅ የደቂቀ ምሥል ገላጭ (ኢሞጂ) መግባቢያ ሆኖ ቀጥሏል።

ያን ቀን ምሽት ደግሞ ሌላ አስደናቂ ድርጊት ፈጸሙ።

ፔሎሲ ለትራምፕ እጃቸውን ሲዘረጉ ትራምፕ ሳይጨብጧቸው ቀሩ። ፔሎሲ ደነገጡ። አፈሩም።

ትራምፕ የሚያደርጉት ንግግር ግልባጭ ለሁሉም እንደራሴዎች ታድሎ ነበር።

በጽሑፍ ለምክር ቤት አባላት የታደለውን የትራምፕን ንግግር ናንሲ ፔሎሲ ካሜራ ፊት እንደ ቆሻሻ ወረቀት ቡጭቅጭቅ አድርገው ቀዳደው ሲጥሉት በቀጥታ በቴሌቪዥን ታየ።

ይህ ትልቅ መነጋገርያ ሆኖ ቆየ። ትራምፕና ናንሲ ፔሎሲ ዓይንና ናጫ ሆነው ይኸው ትራምፕ ከነጩ ቤተ መንግሥት ሲወጡ፣ ፔሎሲ ወደ ካፒቶል ሂል ሰተት ብለው በድጋሚ እየገቡ ነው።

ፔሎሲ ከትራምፕ ጋር በግንብ አጥር የበጀት ጉዳይ ከፍ ዝቅ ተደራርገው ተሰዳድበዋል። ይህም በብዙ ሰዎች የተጋራ የፖለቲካ ቪዲዮ ሆኖ ነበር።

ፔሎሲ በአሜሪካ ታሪክ ሦስተኛው ተከሳሽ ፕሬዝዳንት በነበሩት ትራምፕ ላይ ክሱን ለመምራት አቅማምተው ነበር።

በኋላ ላይ ግን ትራምፕ ከዩክሬን ጋር የገቡበትን ቅሌት ሲሰሙ ክሱን ለመምራት ፍቃደኛ ሆኑ።

ትራምፕ በሥልጣናቸው ባልገዋል። ይህ ደግሞ ቸል ሊባል አይገባም ብለው መቀነታቸውን አጥብቀው ተነሱ።

ትራምፕ በዚህን ጊዜ የዩክሬን ባለሥልጣናት በጆ ባይደንና በልጁ ላይ አንዳች ጥፋት እንዲያፈላልጉና እንዲከሱ፣ አለበለዚያ ግን ለጦር መሣሪያ የሚሰጥ እርዳታ እንደማይለቀቅላቸው እያስፈራሩ ነበር።

ትራምፕ ላይ የተነሳው ክስ ገፍቶ ሄዶ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ደርሶ የነበረ ቢሆንም በትራምፕ ወዳጆች የተሞላው የላይኛው ምክር ቤት ክሱን ውደቅ አድርጎታል።

ፔሎሲ ለትራምፕ የጎን ውጋት ሆነውባቸው ነው ዘመናቸውን ሁሉ ያሳለፉት።

የሜክሲኮን ድንበር በግንብ አጥር እጋርዳለሁ ገንዘብ ስጡኝ ያሉት ትራምፕ፣ ገንዘብ ይፈቀድ አይፈቀድ በሚለው ዙርያ ፔሎሲ ለትራምፕ አስጨናቂ ሆነውባቸው እንደነበር አይዘነጋም።

ይህን ተከትሎ ነበር ትራምፕና ፒሎሲ በሚዲያ ፊት መተነኮኳኮስ የጀመሩት።

ናንሲ ፔሎሲ የንግግሩን ወረቀት ሲቀዱ

የፎቶው ባለመብት, AFP

መጪዎቹ የፒሎሲ ዘመናት ያስፈራሉ

የባይደንን ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት መጠጋትን ተከትሎና ከዚያ ቀደም በነበሩ የሕዝብ ስሜቶች ተመርኩዘው ፔሎሲ የሚመሩት የሕግ መምሪያ ምክር ቤት የበላይነቱን አጠናክሮ ይቀጥላል የሚል መተማመን ነበር።

የሆነው ግን በተቃራኒው ነው። ዲሞክራቶች ከአንድ ደርዘን በላይ እንደራሴ ወንበሮችን ለሪፐብሊካን ለመስጠት ተገደዋል።

ከዚህ በኋላ የፔሎሲ የምክር ቤት ወንበር ቀላል አይሆንም።

ለግራ ዘመሙ ፓርቲያቸው የሚስማማ አጀንዳዎችን መቅረጽ፣ ከዚያም ረቂቅ አድርጎ ማወያየት፣ አወያይቶም ማጸደቅ እንደ ከዚህ በፊቱ ቀላል ተግባር አይሆንም።

የቢቢሲው የአሜሪካ ፖለቲካ ተንታኝ አንተኒ ዘርቸር እንደሚለው የፔሎሲ የ50 ዓመታት ፖለቲካዊ ተጋድሎ ከባዱ ፈተና ከዚህ በኋላ ያለው ነው የሚሆነው። ፈተናውን እንዴት ይወጡት ይሆን?

"አንዱ መንገድ ለዘብተኛ የሪፐብሊካን እንደራሴዎችን ወደ እርሳቸው ሐሳብ እያግባቡ ማምጣት ነው። ሁለተኛው ተስፋቸው በሕግ መወሰኛ ምክር (ሴኔት) ቤት ዲሞክራቶች አብላጫ ወንበር ማግኘት ከቻሉ ነው" ይላል አንተኒ።

ነገ ለጆርጂያ ግዛት 2 የምክር ቤት አባላት ይወዳደራሉ።

ከተሸነፉ የላይኛው ምክር ቤት በሪፐብሊካን የበላይነት ይያዛል። ይህ ደግሞ ለጆ ባይደንና ለሐሪስ አዲስ ራስ ምታት ነው።

ነገ የጆርጂያ ውክልና በዲሞክራቶች አሸናፊነት ከሆነ ግን ምክር ቤቱ እኩል የሪፐብሊካንና የዲሞክራቶች ተወካዮች ይኖሩታል።

ይህ ከሆነ ደግሞ የሕግ መወሰኛውን ምክር ቤት ሊቀመንበርነት ከማይክ ፔንስ የሚረከቡት ተመራጭዋ ምክትል ፕሬዝዳንት ካምላ ሐሪስ የልዩነት ድምጽ የሚሰጡ ወሳኝ ሰው ይሆናሉ ማለት ነው።

ይህ የመሆን ዕድሉ ግን ጠባብ ነው።

አምስት ልጆችና ዘጠኝ የልጅ ልጆችን ያፈሩት ፔሎሲ ምናልባትም በፖለቲካ የመጨረሻው ዘመናቸው ፍሬያማ ላይሆን ይችላል።