የአፈጉባኤዋ የትራምፕን ንግግር መቅደድ አነጋጋሪ ሆነ

ናንሲ ፔሎሲ የንግግሩን ወረቀት ሲቀዱ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአሜሪካው ፕሬዝዳናት ዶናልድ ለአገሪቱ ምክር ቤት አመታዊውን ንግግራቸውን ካደረጉ በኋላ አፈ ጉባኤዋ የንግግሩን ቅጂ ሲቀዱ መታየታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

ፕሬዝዳንቱ ንግግር ሲያደርጉ ከኋላቸው ተቀምጠው የሚታዩት የዴሞክራቲክ ፓርቲ አባልና የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ በንግግሩ ማብቂያ ላይ እጃቸው ላይ የነበረውን የፕሬዝዳንቱን ንግግር ቅጂ ሲቀዱ ታይተዋል።

ይህም የተከሰተው ፕሬዝዳንት ትራምፕ አፈጉባኤዋን ላለመጨበጥ ካንገራገሩና ረጅሙን ንግግራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ነበር።

አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ፕሬዝዳናት ትራምፕ ስልጣናቸውን ያለአግባብ ተጠቅመዋል በሚል ክስ እንዲመሰረትባቸውና ጉዳያቸው በምክር ቤቱ እንዲታይ ማስደረጋቸው ይታወሳል።

የዴሞክራቲክ ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት አፈጉባኤዋ መነጋገሪያ ከሆነው የፕሬዝዳንቱን ንግግር ቅጂ የያዘውን ወረቀት ከቀደዱበት ድርጊታቸው በኋላ ለምን ይህንን እንዳደረጉ በጋዜጠኞች ተጠይቀው መልስ ሰጥተዋል።

አፈጉባኤዋም የፕሬዝዳንቱ ንግግር "ቆሻሻ ንግግር ስለነበረ የፈጸምኩት የሚገባ ነገር ነው" ሲሉ ድርጊታቸውን አወድሰዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለአንድ ሰዓት ከ18 ደቂቃ ስለተለያዩ ጉዳዮች አንስተው ለምክር ቤቱ አባላት ንግግር አድርገዋል።

ፕሬዝዳንቱ ዓመታዊ ንግግራቸውን አጠናቀው ከምክር ቤቱ ሲወጡ የፓርቲያቸው የሪፐብሊካን አባላት ከአፈጉባኤዋ ከናንሲ ትችት በተለየ ፕሬዝዳንቱ ያደረጉት ንግር "ድንቅ" እንደነበር ሲናገሩ ተሰምተዋል።

ዴሞክራቶች ፕሬዝዳንቱ ባደረጉት ንግግር ላይ ከአፈጉባኤዋ ጀምሮ በግልጽ ደስተኛ አለመሆናቸውን አሳይተዋል። አንዳንዶቹ እንዲያውም ፕሬዝዳንቱ እየተናገሩ ምክር ቤቱን ለቀው ሲወጡም ታይተዋል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ከስልጣን ለማውረድ የተጀመረው እንቅስቃሴ ይሳካ ይሆን?