ትራምፕ ላይ እንዲመሰክሩ የተጠሩት አምባሳደር ፕሬዝደንቱ አስፈራርተውኛል አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ትራምፕ ከሥልጣን ይወርዱ አይወርዱ ብሎ ለሚመክረው ኮንግረስ ሃሳባቸውን እንዲሰጡ የተጠሩት አምባሳደር ፕሬዝደንቱ ስለሳቸው በተናገሩት ነገር ሃሳብ ውስጥ መግባታቸውን አሳውቀዋል።
በዩክሬን የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ሜሪ ዮቫኖቪች ለኮንግረሱ ቃላቸውን በሰጡ ወቅት ፕሬዝደንት ትራምፕ ለዩክሬን አቻቸው ደውለው «መቼስ እሷም ብትሆን ብዙ ማየቷ አይቀርም» ሲሉ ስለኔ አስተያየት ሰጥተዋል ይላሉ።
ትራምፕ ላይ እየቀረበባቸው ያለው ዋናው ክስ ለዩክሬኑ ፕሬዝደንት ደውለው ስለ መጪው ምርጫ ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን መረጃ ስጠኝ ብለዋል የሚል ነው።
የጆ ባይደን ልጅ ሃንተር ባይደን ዩክሬን ውስጥ አንድ የነዳጅ አውጭ ኩባንያ አለው። ይህ ደግሞ ለትራምፕ ተመችቷቸዋል ባይ ናቸው ከሳሾቻቸው።
ሐምሌ 25 ለዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ስልክ የመቱት ትራምፕ አምበሳደሯን 'መጥፎ ዜና' ሲሉ ወርፈዋታል። ይህን ተከትሎ ነው ኮንግረሱ አምባሳደሯ ቀርበው እንዲመሰክሩ ጥሪ ያቀረበላቸው።
«እኔ ፕሬዝደንቱ ምን ማለት እንደፈለጉ አልገባኝም፤ ነገር ግን ያሉት ነገር አስጨንቆኝ ነበር። አሁንም ቢሆን ያሳስበኛል» በማለት ለኮንግረሱ ቃላቸውን ሰጥተዋል።
የበርካታ ዓመታት ልምድ ያላቸው ዲፕሎማቷ ምክር ይሰጡኝ እንደሁ ብለው በአውሮጳ ሕብረት የአሜሪካ አምባሳደር ለሆኑት ጎርደን ሶንድላንድ ሃሳባቸውን ቢያካፍሉም፤ የረባ ምላሽ አለማግኘታቸውን አሳውቀዋል። የትራምፕ ደጋፊ ናቸው የሚባልላቸው ጎርደን «ትራምፕን የሚያሞግስ ሃሳብ ትዊተር ላይ ብትለጥፊ ይሻላል» የሚል ምክር ነው የሰጡኝ ብለዋል አምባሳደሯ።
አምባሳደሯ ከዩክሬን ፍትህ ሚኒስትር ሳይቀር 'አካባቢዎትን ቢያጠኑ ይሻላል' የሚል መልዕክት እንደደረሳቸውና እና የትራምፕ የግል ጠበቃ የሆኑት ሩዲ ጁሊያኒ በተደጋጋሚ እሳቸውን የሚያጣጥል ሃሳብ መስጠታቸው ሁኔታው አስጊ ነው ብለው እንዲረዱ እንዳስገደዳቸው አልሸሸጉም።
አምባሳደር ሜሪ ባለፈው ግንቦት፤ ከሥራ ማለቂያ ቀነ ገደባቸው ወራት ቀደም ብሎ ነበር ሥራቸውን ለቀው ወደ አሜሪካ የተመለሱት።













