ዶናልድ ትራምፕ በስሎቬኒያ የባለቤታቸው መኖሪያ ቤት ሐውልት ቆመላቸው

የዶናልድ ትራምፕ ከእንጨት የተሰራ ሐውልት ከባለቤታቸው ሜላኒያ ሐውልት በስተግራ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የዶናልድ ትራምፕ ከእንጨት የተሰራ ሐውልት ከባለቤታቸው ሜላኒያ ሐውልት በስተግራ

አነጋጋሪው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስሎቬኒያ በሚገኘው የባለቤታቸው መኖሪያ ቤት ከእንጨት የተሰራ ሐውልት ቆመላቸው።

8 ሜትር የሚረዝመው ሐውልት የቆመው በግለሰብ ይዞታ ላይ ሲሆን ጭንቅላታቸውና አገጫቸው አራት መዓዘን ቅርፅ ይዞ የተሰራ ነው። ዶናልድ እጃቸውን በድል ምልክት ወደላይ ዘርግተው ይታያል።

ሰማያዊ ሙሉ ልብስ በቀይ ክራቫት ለብሰውም የኒዮርኩን የነፃነት ሐውልት ያስታውሳሉ።

ታዲያ በርካቶች በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት አልተቆጠቡም።

የሐውልቱ ቀራፂ ለኤ ኤፍ ፒ የዜና ወኪል እንዳለው የሕዝቡን ስሜት ለማንፀባረቅ መስራት እንደፈለገ ተናግሯል። ሐውልቱ የተሰራውም የባለቤታቸው ሜላኒያ ትራምፕ ሐውልት በትውልድ ቦታዋ ስቭኒካ ከቆመ በኋላ ነው።

ሐውልቷ ከእንጨት ተፈልፍሎ የተሰራ ሲሆን ሰማያዊው ኮት ለብሳ እጇን ወደ ላይ ዘርግታ ይታያል። አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎችም "ክብረ ቢስ! የቀዳማዊት እመቤት ሳይሆን የአሻንጉሊት ቅርፅ ይመስላል" ሲሉ ተሳልቀውበታል።

አዲሱ የትራምፕ ሐውልትም ከሰሜን ምስራቅ ጁቢልጃና 32 ኪሎሜትር በሚርቅ ሥፍራ ነው የቆመው። ቀራጺውም ቶማስ ስችሌግል ሐውልቱ ለአክራሪ ፖለቲከኝነታቸው ግብረ መልስ እንደሆነ ተናግሯል።

የዶናልድ ትራምፕ ሐውልት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ሐውልቱ የተቀረፀው በስሎቬኒያዊው ቀራፂ ቶማዝ ስችሌግል ነው

"ተመልከት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እየሆነ ያለውን፤ አክራሪ ፖለቲከኞች እንደ አሸን እየፈሉ ነው። የእንግሊዙን ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰንን፣ ትራምፕን፣ የአገራቸንን ፕሬዚዳንት እንዲሁም የሀንጋሪን ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶርን ተመልከታቸው! ይህ ዓለም ወዴት እያመራ ነው እንድትል ያደርጉኻል። ሰዎች ዲሞክራሲ ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንዲያውቁ እና ዐይናቸውን እንዲከፍቱ እንፈልጋለን" ብሏል።

ቀራጺው እንደሚለው በእንጨቱ ውስጥ የተቀመጠው ጥበባዊ ቅርፅ፤ የሀውልቱ ስሜት ተለዋዋጭ እንዲሆን ያግዛል። "በሳምንቱ የአዘቦት ቀናት በጣም ተግባቢ፥ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ደግሞ አስፈሪ ሆኖ እንዲለዋወጥ የሚረዳ ነው። ተምሳሌትነቱም የአክራሪ ፖለቲከኞች ግብዝነት ማሳየት ነው።" ብሏል።

ባለፈው ቅዳሜ በነበረው የሐውልቱ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ አንድ የአካባቢው ነዋሪ በቁጣ ትራክተሩን እያሽከረከረ መጥቶ ሊደመስሰው ነበር።

አንዳንድ የኦንላይን ተጠቃሚዎች ደግሞ 'የእንጨት ብክነት' ሲሉ ሀውልቱን ተቃውመዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ለስሎቬኒያ ምልክት እየሆኑ መጥተዋል፤ በአውሮፓዊኑ 2016 ሥልጣን ላይ ከወጡ አንስቶም የባለቤታቸው ትውልድ አገር የቱሪስት መዳራሻ ሆናለች።

ጎብኝዎች ሲሄዱም የሜላኒያ ምስል ያለበት ነጠላ ጫማ፣ ኬክና በርገር ይቀርብላቸዋል።

ምንም እንኳን ባለፈው ወር የተሰራው የሜላኒያ ሐውልት ትችት ቢሰነዝረበትም አንድ የአካባቢው ነዋሪ 'ጥሩ ሃሳብ ነው' ሲሉ ለኤ ኤፍ ፒ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

"ሜላኒያ የስሎቬንያ ጀግና ናት፤ በአሜሪካ ትልቁን የፖለቲካ ማማ ወጥተዋለች" ሲሉ የ66 ዓመቷ ካትሪና አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።