ትራምፕ የሕንዱን ጠቅላይ ሚኒስትር አሞካሹ

በዝግጅቱ ላይ ከ50ሺህ በላይ ታዳሚዎች ተሳታፊ ነበሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በዝግጅቱ ላይ ከ50ሺህ በላይ ታዳሚዎች ተሳታፊ ነበሩ

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሕንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ በቴክሳስ ግዛት ሂውሰትን ከተማ በተዘጋጀ መደረክ ላይ ሲሞጋገሱ አምሽተዋል።

"ዛሬ እዚህ በቴክስሳ ከአሜሪካ ቁልፍ አጋር፣ ታታሪ እና ታማኝ ወደጅ ከሆኑት ከጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር በመገኘቴ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል" በማለት ለ50ሺህ ታዳሚዎች የተናገሩት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው።

ጠቅላይ ሚንስትር ሞዲ በበኩላቸው፤ ፕሬዝደንት ትራምፕን በዋኃይት ሃውስ የሚገኝ "እውነተኛ ጓደኛ" ብለው ከገለጹ በኋላ፤ "ከዋና ሥራ አስፈጻሚ ወደ የአሜሪካ ጦር ጠቅላይ አዛዥ፣ ከቦርድ ስብሰባ አዳራሽ ወደ ዋኃይት ሃውስ፣ . . . ትራምፕ በየሄዱበት አሻራቸውን ጥለው የሚያልፉ መሪ" ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል።

ትራምፕ "እጅግ አስደናቂ እና ታሪካዊ ክስተት'' ሲሉ በገለጹት መድረክ ከ50ሺህ በላይ ሰዎች ተሳታፊ ሆነውበታል።

ለ 90 ደቂቃ የቆየው ዝግጅት በአሜሪካ ታሪከ ለውጪ ሃገር መሪ ከተሰናዱ ደማቅ አቀባበሎች መካከል አንዱ ነው ተብሎለታል።

ዶናልድ ትራምፕ እና ናሬንድራ ሞዲ እጅ ለእጅ ተያይዘው ታዳሚውን ሲሰናበቱ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዶናልድ ትራምፕ እና ናሬንድራ ሞዲ እጅ ለእጅ ተያይዘው ታዳሚውን ሲሰናበቱ።

ይህ መድረክ በ 2020 ለሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ትራምፕ ትውልደ ሕንድ የሆኑ አሜሪካውያንን ድጋፍ ለማገኘት እንደሚረዳቸው ታምኗል። ለጠቅላይ ሚንስትር ሞዲ ከትራምፕ የተቸራቸው ውዳሴ በሕንድ እየቀረበባቸው ያለውን የሰላ ትችት ያለዝበዋል ተብሏል።

ትራምፕ በስታዲየሙ ተሰብሰበው ለነበሩት ትውልደ ሕንድ አሜሪካውያን ታዳሚዎች "አሜሪካዊ ሆናችሁ ከእኛ ጋር ስለሆናችሁ ኩራት ይሰማናል" ብለዋል።

የሕንዱ ጠቅላይ ሚንሰትር አንድ ሳምንት በሚቆየው የአሜሪካ ጉብኝታቸው ከአሜሪካ ጋር በንግድ ላይ ያተኮረ ውይይት እንደሚያደርጉ የሚጠበቅ ሲሆን በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ስብሰባ ላይም ተሳታፊ ይሆናሉ።