በአሜሪካ ምክር ቤት መሪዎች መኖሪያ ቤት ላይ ጥቃት መፈጸሙ ተነገረ

ሚች ማኮኔል እና ናንሲ ፔሎሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሚች ማኮኔል እና ናንሲ ፔሎሲ

በአሜሪካ ምክር ቤት አፈጉባኤ ናንሲ ፔሎሲና የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት የብዙሃን መሪው ሚች ማኮኔል መኖሪያ ቤት ላይ ጥቃት መፈጸሙ ተነገረ።

ካሊፎርኒያ ውስጥ ከሚገኘው የናንሲ ፔሎሲ ቤት ውጪ አንገቱ የተቆረጠ አሳማና ደም የሚመስል ቀለም የተገኘ ሲሆን ግድግዳውም በተለያየ ጽሁፍ ተበላሽቶ ተገኝቷል።

ኬንተኪ ውስጥ በሚገኘው የሪፐብሊካኑ ማኮኔል ቤት ግድግዳ ላይ ደግሞ "ገንዘቤ የታለ" የሚል ጽሁፍና የስድብ ቃላት ተጽፈው ተገኝተዋል።

ይህ በባለስልጣናቱ መኖሪያ ላይ የተፈጸመው ጥቃት የተከሰተው በኮሮናቫይረስ ምክንያት ያጋጠመውን ችግር ለመቅረፍ በቀረበው የድጋፍ ዕቅድ ላይ በምክር ቤት ከባድ ፖለቲካዊ ውዝግብ መካሄዱን ተከትሎ ነው።

ባለፈው ማክሰኞ በዲሞክራቶች በሚመራው የአሜሪካ ምክር ቤት የ40 ሪፐብሊካን አባላት ድጋፍን በማግኘት በኮሮናቫይረስ ምክንያት ገቢያቸው ለተጎዳ ዜጎች እንዲሰጥ ሐሳብ ቀርቦበት የነበረውን የ600 ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ወደ 2000 ዶላር ከፍ እንዲል ተወስኖ ነበር።

ምንም ችንኳን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀረበውን ረቂው የምክር ቤት አባላቱ እንዲያጸድቁ ቢጠይቁም በሪፐብሊካኖች የሚመራው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ከፍተኛ የገንዘብ ወጪን የሚጠይቀውን በጀት ሳይቀበለው ቀርቷል።

ረቡዕ ዕለት ሚች ማኮኔል እንደተናገሩት በሚደረግ ማንኛውም ጫና "በብድር የሚገኘውን ገንዘብ ድጋፉ ለማያስፈልጋቸው ለዲሞክራት ሐብታም ወዳጆች በጥድፊያ እንዲሰጥ አናደርግም" ሲሉ ተደምጠው ነበር።

ሚች ማኮኔል ቅዳሜ በቤታቸው ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ባወጡት መግለጫ ላይ "ቢስማሙም ባይስማሙም" በምክር ቤቱ የሥራ ሂደት ወቅት የተሳተፉትን በሙሉ አመስግነዋል።

ጨምረውም "ይህ የተለየ ጉዳይ ነው" በማለት የተፈጸመውን ጥቃት በመቃወም "ንብረት ማውደምና ጉዳት ማድረስ እንዲሁም ፍርሃት ለመፍጠር የሚደረገው ፖለቲካም በማኅበረሰባችን ውስጥ ቦታ የለውም" ብለዋል።

የሳንፍራንሲስኮ ፖሊስ በአፈጉባኤዋ ቤት ላይ በተፈጸመው ጥቃት ዙሪያ ምርመራ እያደረጉ ሲሆን ፔሎሲ ግን እስካሁን ምንም አስተያየት አልሰጡም።

ባለፈው አርብ የአሜሪካ ምክር ቤት በፕሬዝዳንት ትራምፕ የስልጣን ዘመን አጋጥሞ በማያውቅ ሁኔታ የፕሬዝዳንቱን ውሳኔ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።

በቅርቡ በተደረገው ምርጫ ለአሜሪካ ምክር ቤት አባልነት የተመረጡ የኮንግረስ አባላት ዛሬ እሁድ ቃለ መሐላ ይፈጽማሉ።