የተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2020 ምርጥ ፊልሞች የትኞቹ ናቸው?

ማ ሬይኒስ ብላክ ቦተም

የፎቶው ባለመብት, David Lee/Netflix

የቢቢሲ የፊልም ሀያሲዎች ኒኮላስ ባርበር እና ክሬይን ጄምስ በተጠናቀቀው 2020 ጎልተው ወጥተዋል ያሏቸውን ምርጥ ፊልሞች ይፋ አድርገዋል። ለመሆኑ እነዚህ ፊልሞች የትኞቹ ናቸው?

ማንግሩቭ (Mangrove)

የዚህ ፊልም ዳይክተር ስቲቭ ማክዊን በርካታ ጥቁር እንግሊዛያውያን እና የካረቢያን ማህበረሰቦች ከ1960ዎቹ እስከ 1980ዎቹ ባሉት ጊዜያት ውስጥ ያሳለፏቸውን መከራዎች በማሳየት ይታወቃል።

ማንግሩቭ ደግሞ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ሲሆን በ1960ዎቹ አካባቢ አንድ የምግብ ቤት ባለቤት ላይ ፖሊስ ስለሚያደርሰው መከራ ያሳያል። ዋናውን ገጸ ባህሪ ወክላ የምትጫወት ሌቲሺያ ራይት በወቅቱ የነበረውን የጥቁሮች እንቅስቃሴ ትመራለች።

በፊልሙ ላይ ፖሊስ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ የሚወስደው እርምጃ በወቅቱ ምን ያክል ጭካኔ የተለመደ እንደነበር ማሳያ ነው ይላሉ ኒኮላስ ባርበር እና ክሬይን ጄምስ።

ዎልፍዎከርስ (Wolfwalkers)

ይህ የአኒሜሽን ፊልም በርካቶችን ማስደነቅ ችሏል። የዋና ገጸ ባህሪ ሮቢን ድምጽ በሻን ቤን የተሰራ ሲሆን በ1600 አካባቢ በአየርላንድ ውስጥ የነበረች አዳኝ ሴት ልጅ ላይ ያተኮረ ነው።

የሮቢን አባት ከጫካ ውስጥ ተኩላዎችን ሲያጠፋ በፊልሙ ላይ ሮቢን አንድ ተኩላ ወደ ሰውነት መቀየር እንደሚችል ታስተውላለች። አባቷ ለማጥፋት የሚተጋውን ተኩላ ለማዳንና ጫካውን ባለበት ለማቆየት የምታደርገው ፍልሚያ አስገርሞናል ብለዋል ባለሙያዎቹ።

አም ቲንኪንግ ኦፍ ኤንዲንግ ቲንግስ (I’m Thinking of Ending Things)

ይህ የቻርሊ ኮፍማን አስፈሪ ድራማ በዓመቱ ካየናቸው ፊልሞች ሁሉ ይለያል። ዋናውን ገጸ ባህሪ ወክላ የምትጫወተው ጄሲ ባክሊ በፊልሙ ላይ የፍቅር ጓደኛዋን ቤተሰቦች ለመተዋወቅ በበረዶ የተሞላ አካባቢ በመኪና ትሄዳለች።

ቤተሰቦቹ ጋር ከተዋወቀች በኋላ ለመረዳት የሚከብዱ ነገሮችን ማስተዋል ትጀምራለች። ቤተሰቦቹ ልብሳቸው አይቀየርም፣ እድሜያቸው ደግሞ ቶሎ ቶሎ ይቀያየራል። እሷም ብትሆን ስሟን ማስታወስ ያቅታታል።

ይህ ፊልም በጣም ግራ የሚያጋባ፣ የሚያስፈራና በሌላ በኩል ደግሞ የሚያጓጓ ነው።

አኖማይት (Ammonite)

ታዋቂዋ ተዋናይ ኬት ዊንሰልት በዚህ ፊልም ላይ እጅግ ድንቅ የተባለ የትወና ችሎታዋን ማሳየት የቻለችበት ነው። በፊልሙ ላይ ኬት ዊንስሌት በ19ኛው ክፍለ ዘመን የፓሊዮንቶሎጂ ዘርፍን የቀየረ የቅሪተ አካል ያገኘችው ሜሪ አኒንግን ወክላ ነው የምትጫወተው።

የፊልሙ ጸሀፊና ዳይሬክተር ፍራንሲስ ሊ ሜሪ በእድሜዋ አጋማሽ አካባቢ ስላጋጠማት የፍቅር ሕይወት፣ ስራ እና የጾታ ተጽዕኖ ለማሳየት ሞክሯል።

ሮክስ (Rocks)

የዚህ ፊልም ዳይሬክተር ሳራህ ጋቨርን ናት፤ ጸሀፊ ደግሞ ቴሬሳ ኢኮኮ እና ክሌር ዊልሰን። አንዲት ታዳጊ እና ታናሽ ወንድሟ እናታቸው በድንገት ከቤት ከጠፋች በኋላ ስለሚያሳልፉት ሕይወት ይተርካል።

ታዳጊዋን ሆና የምትተውነው በኪ ባክሬይ በፊልሙ ላይ በርካታ ስህተቶችን ብትሰራም ጥሩ ጓደኞች ግን አሏት።

ልብን በሀሴት የሚሞላና ተስፋ የሚሰጥ ፊልም ነው ብለውታል ኒኮላስ ባርበር እና ክሬይን ጄምስ።

ማ ሬይኒስ ብላክ ቦተም (Ma Rainey's Black Bottom)

በቅርቡ በሞት የተለየን ታዋቂው የብላክ ፓንተር ተዋናይ ቻድዊክ ቦዝማን የሚተውንበት ይህ ፊልም በ1924 በቆዳ ቀለሙ ምክንያት በሚደርስበት ጥቃት የተጎዳ ሙዚቀኛ ሆኖ ነው የሚተውነው።

ገጸ ባህሪው ሊቪ የሚሰኝ ሲሆን በልጅነቱ በደረሰበት የዘር ጥቃት የአዋቂነት ሕይወቱ ሲቃወስ ያሳያል። አምቆት የቆየው ቁጣው የሆነ ሰአት ላይ ሲፈነዳም ይታያል። ሊቪ ተጫዋች፣ ዳንስ የሚወድ፣ ሳቂታ ወጣት ነው። ቻድዊክ ደግሞ ገጸ ባህሪውን በደንብ ተላብሶ ተጫውቶታል።

ዳ 5 ብለድስ (Da 5 Bloods)

ስፓይክ ሊ ከሰራቸው ፊልሞች መካከል ይሄኛው በጣም ምርጥ ከሚባሉት ነው ብለዋል ኒኮላስ ባርበር እና ክሬይን ጄምስ። አራት ጥቁር አሜሪካውያን በወጣትነታቸው ለጦርነት ወደሄዱባት ቬትናም ይመለሳሉ።

ዋናው አላማቸው ደግሞ በጦርነቱ ሕይወቱን ያጣውን ጓደኛቸውን አስክሬን ይዞ ለመመለስና የደበቁትን ወርቅ ለማምጣት ነው። በዚህ ፊልም ላይ የአራቱን ጓደኛማቾች አስገራሚ የሕይወት ጉዞ እና በአሜሪካ ያለውን ዘረኝነት ይታያል።

ዘ ሃንት (The Hunt)

ይህ ፊልም ገና ለተመልካች ይፋ ሳይደረግ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር። በፊልሙ ላይ ሀብታም አሜሪካውያን ግራ ዘመም ደሀ አሜሪካውያንን አግተው ወስደው እንደ እንስሳ እያሳደዱ ሲያድኗቸው ይታያል።

በአሜሪካ ባጋጠሙ ሁለት ጥቃቶች ምክንያት ፊልሙ ሁለት ጊዜ የሚለቀቅበትን ጊዜ ለማራዘም ተገድዷል። በመጨረሻ ፊልሙ ይፋ ሲደረግ በርካቶችን ያስደሰተ ፊልም መሆን ችሏል።

ፊልሙን እየተመለከቱ ማን ቀጥሎ ይሞት ይሆን፣ማን ከማን ጋር አብሯል፣ መጨረሻው ምን ይሆን የሚሉ ጥያቄዎችን አለመጠየቅ በጣም ከባድ ነው።