ተደብቆ ስለ ሞት ቅጣት ፊልም የሠራው ኢራናዊ ዳይሬክተር ተሸለመ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኢራናዊው 'ዳይሬክተር' ስለ ሞት ቅጣት የሠራው ፊልም በበርሊን ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ላይ ሽልማት አገኘ።
ሞሐመድ ራሶሎፍ፤ ኢራን ውስጥ ፊልም እንዳይሠራ የታገደው በግሪጎሪ አቆጣጠር 2017 ላይ ቢሆንም ተበድቆ የሠራው 'There Is No Evil' የተሰሠው ፊልም ሊያሸልመው ችሏል።
ግለሰቡ ቀድሞ በሠራቸው ፊልሞች ምክንያት በተጣለበት ዕግድ ምክንያት ከሃገር መውጣት አይችልም። በፊልሙ ላይ በትወና የተሳተፈችው የዳይሬክተሩ ልጅ ባራን በአባቷ ስም 'ጎልደን ቢር' የተሰኘውን ሽልማት ተቀብላለች።
የፊልም ሽልማቱ ዳኛ ዤሬሚ አይረንስ፤ 'ስለ አራት የሞት ቅጣት ታሪኮች የሚያወራው ፊልም የኢራን መንግሥት ምን ያህል ተራ ዜጎችን እየሰለለ እንደሆነና ኢ-ሰብዓዊ ጥቃት እንደሚያደርስ የሚያሳይ ነው' ብለዋል።
'Never Rarely Sometimes Always' የተሰኘውና ስለ ውርጃ የሚያትተው አሜሪካዊ ፊልም ሁለተኛውን ሽልማት አግኝቷል።
በተጣለበት እግድ ምክንያት ሽልማቱን መታደም ያልቻልው ሞሐመድ ከቤቱ ሆኖ በልጁ ስልክ አማካይነት ከሽልማቱ በኋላ የሚካሄደውን ጋዜጣዊ መግለጫ ታድሟል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዳይሬክቱ በፊልሙ ማሳየት የፈለግኩት ስለ ኃላፊነት ነው ብሏል። «ሰዎች ኃላፊነትን ከራሳቸው ያገላሉ። ውሳኔው የተሰጠው ከእኛ በላይ በሆኑ ኃላፊዎች ነው ይላሉ። ነገር ግን አይሆንም ማለት ይችላል። ይህ ደግሞ ጥንካሬያቸውን ማሳያ ነው።»
«እያንዳንዱ የፊልሙ ክፍል የራሴ ሕይወት ታሪክ ነው» ሲል ሞሐመድ በተንቀሳቃሽ ስልክ የቪድዮ ጥሪ መልዕክቱን አስተላልፏል። አንደኛው የፊልሙ ክፍል እሥር ቤት እያለ ያሰቃየው የነበረ ሰው ከባንክ ቤት ሲወጣ ሲያየው የተሰማውን ስሜት የገለፀበት እንደሆነ ሞሐማድ ይናገራል።
«ትንሽ ከተከተልኩት በኋላ እንደ ሁሉም ሰው መሆኑን ተረዳሁ። ምንም ዓይነት ሰይጣናዊ ባሕሪ አላየሁበትም። ልዩነቱ ሰውየው ድርጊቴ ምን ዓይነት ጉዳት ያደርሳል ብሎ አለማሰቡ ነው።»
ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ቡድኖች ኢራን ውስጥ በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሞት ቅጣት ይሞታሉ ሲሉ ያወግዛሉ።













