የ'ፍሬንድስ' ፊልም ተዋናዮች እንደገና ቢመለሱስ?

ፍሬንድስ ፊልም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፍሬንድስ ተዋናዮች እንደገና ቢመለሱስ? ተመልሰው አዲስ ተከታታይ ፊልም ቢሰሩስ?

የተወዳጁ ተከተታይ ሲትኮም የ'ፍሬንድስ' አድናቂዎች የመጨረሻው ክፍል ከታየበት ከአስራ አምስት ዓመታት ጀምሮ የሚጠይቁት ጥያቄ ቢኖር የፍሬንድስ ተዋናዮች እንደገና እንዲሰባሰቡ ነው።

ለአስር ዓመታት ያህልም ብዙዎች የስድስቱን ጓደኞች ውጣ ውረድ በፍቅር ተመልክተውታል። ከተሰራበት ከአሜሪካ ውጪ ወጥቶ የተለያዩ ትውልዶችን፤ ዘሮችንና ህዝቦችንም ማገናኘት ችሏል።

አሁንም ብዙዎች በናፍቆት ይጠብቁታል፤ እንደገና ቢሰባሰቡስ? የሚሉ ጥያቄዎችም ይሰማሉ።

በቅርቡም ይህንን ሃሳብ እውን የሚያደርግ ነገር ተከስቷል፤ ተዋናዮቹ ኮርትኒ ኮክስ (በፍሬንድስ ገፀ ባህርይ ስሟ ሞኒካ) ቤት ተሰባስበው ነበር።

በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በእንግሊዝም ለሁለት ዓመታት ያህል የከፍተኛ ቁጥር ያለው ተመልካችን ከመሳብ አንፃር ብዙዎችን የመሰባሰባቸው ዜና አስደስቷቸው ነበር።

በተመልካቾች ቁጥር ብቻ አይደለም ፊልሙ የሚመራው፤ በፊልሙ ዙሪያ ዲዛይን የተደረጉ አልባሳትም ሆነ ሌሎች ቁሳቁሶች በከፍተኛ ደረጃ ይቸበቸባሉ።

ይህ ማለት የፍሬንድስ መመለሻ ጊዜ አሁን ይሆን?

ፍሬንድስ ፊልም እንደገና ቢመለስም ከፍተኛ የሆነ እይታም ሆነ ተወዳዳሪነት እንዳለው ሳይታለም የተፈታ ነው።

ፊልሙ 25ኛ ዓመት ክብረ በዓልም እየተከበረ ባለበት ወቅት ኔትፍሊክስ ፊልሙን እያሳየ መሆኑ አዳዲስ ተመልካቾችን ማምጣት ችሏል።

ቀልዶቹም በአዲሶቹ ተመልካቾች ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘት መቻላቸው፤ የተለያዩ ትውልዶችን ማገናኘት የቻለ ተብሎለታል።

በተለይም ከኔትፍሊክስ ጋር በብዙ ሚሊዮን ፓውንዶች ስምምነት መድረስ መቻሉ ያለው ተፈላጊነትን ማሳያ እንደሆነ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያሉ ሰዎች ይናገራሉ።

ፊልሙን የሰራው ዋርነር ብራዘርስ ቲቪ ስቱዲዮ ሰዎች ለሬዲዮ 1 ኒውስ ቢት እንደተናገሩት "ይህ ማለት ፊልሙ እንደገና ይመለሳል ማለት አይደለም፤ ለዓመታትም ሳይቋረጥ ታይቷል" ማለታቸው ተሰምቷል።

የተመልካቾች ቁጥር አዘጋጆቹ ላይ ተፅዕኖ ማሳረፍ ካልቻለ፤ ምናልባት በፊልሙ ስም የሚመረቱ አልባሳትና ቁሶች እንደገና ሊያመጡት ይችሉ ይሆን?

በእንግሊዝ ውስጥ ከፊልሙ የተወሰዱ ሃረጎች ለምሳሌ ጆዊ የተባለው ገፀባህርይ በተደጋጋሚ የሚላቸውን "ሃው ዩ ዱይን" ፅሁፍ የሰፈረባቸው ሹራቦች እንዲሁም ቲሸርቶች በከፍተኛ ደረጃ ተፈላጊነት አላቸው።

ታላላቅ ዓለም አቀፍ የአልባሳት ኩባንያዎችም በዚህ ዘርፍ ተሳታፊ ሲሆኑ ከነዚህም ውስጥ ዘርፉን ዘግይቶ የተቀላቀለው ኤችኤንድ ኤም ነው። ኤች ኤንድ ኤም ለቢቢሲ እንደገለፀው ከፍተኛ ሽያጭም አላቸው።

ችሎ ኮሊንስ ዓለም አቀፉን የአልባሳት ሽያጮችን መረጃ ተንታኝ ናት፤ በተለያዩ አልባሳት ሱቆች ውስጥ ዘርፉን እየመሩ ያሉት የትኞቹ ናቸው ብላም በምትመለከትበት ወቅት በፍሬንድስ ፊልም ዙሪያ የተሰሩ አልባሳት ገበያውን ቀዳሚ እንደሆነ ትናገራለች።

ከእነዚህም ውስጥ ታዋቂዎቹ የአልበሳት ምርት ምልክቶች ኤችኤንድኤም፣ ቶፕሾፕ ኤስኦኤስ ይገኙበታል።

"አሁንም ቢሆን ሰዎች በየቀኑ የሚያዩት ፊልም ነው፤ አያረጅም፤ ጊዜም አያልፍበትም" ትላለች።

የፍሬንድስ ተዋናዮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ያልተጠበቀ መሰባሰብ

የተመልካች ቁጥር ወይም ፍላጎት ሳይሆን ዋናው ጥያቄ ተዋናዮቹ እንደገና ተሰባስበው መስራት ይፈልጉ ይሆን ወይ የሚለው ነው።

ኮርትኒ ኮክስ (ሞኒካ) ቤት በተሰባሰቡበት ወቅት እንደገና አንድ ላይ ሊሰባሰቡ ይችላሉ የሚለው ተስፋ አንሰራርቶ ነበር።

ከፍሬንድስ ተዋናዮች ጄኔፈር አኒስተን (ሬቸል)፣ ማት ለብላንክ (ጆዊ) ጋር አብረው የተነሱትንም ፎቶ "ያልተለመደ ምሽት፤ በጣም ነው የወደድኩት'' በማለት ሞኒካ በኢንስታግራም ገጿ አጋርታለች።

በተለይም ጄኔፈር አኒስተን በተገናኙበት በነገታው ከአሜሪካው ሬድዮ ጋር ባደረገችው ቃለ መጠይቅ ስድስቱም መገናኘታቸውን ይፋ ማድረጓን ተከትሎ ብዙዎችም ደስታቸውን ገልፀው ነበር።

አሁን ባሉበት እድሜ ተሰባስበው እንደገና የመስራት እቅድ አላችሁ ወይ ተብሎ ለቀረበላት ጥያቄ የሚያቅማማ የሚል ምላሽ ሰጥታለች።

"እንደገና ተሰባስበን ብንሰራ እንደቀድሞው ጥሩ አይሆንም፤ ያበላሸዋል" ብላለች።

ምንም እንኳን በጭራሽ አይሆንም የሚል መልስ ባትሰጥም የቴሌቪዥን ፊልሞች ላይ ሂስ በመስጠት የሚታወቀው ስኮት ብርያን ሊሰባሰቡ እንደማይችሉ ይናገራል "ዋናው ጉዳይ ተዋናዮቹ ናቸው" ይላል።

ፊልሙን እንደገና መስራትም አደጋ እንዳለውም አልደበቀም።

"ፊልሙ ከተመለሰ በትዝታ ብቻ መሄድ አይችልም፤ እሱ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይጠፋል። አሁን ያለንበትን ጊዜ ሊያንፀባርቅ የሚችል ታሪክና ገፀባህርያት ያስፈልጋሉ" ይላል።

ሆነም ቀረም ፊልሙን እንደገና የመስራት ውሳኔ የአዘጋጆቹና የፀሃፊዎቹ ቢሆንም የተዋናዮቹም እንደገና መገናኘታቸው ብዙ ያነሳሳቸው አይመስልም።