ኮሮናቫይረስ፡ "ኮንቴጀን" በኮሮና ምክንያት ቀን የወጣለት ፊልም

የፎቶው ባለመብት, PA, Getty Images, AP
በሆሊውድ ሲኒማ ታሪክ እንደዚህ ወቅት በሽታና ወረርሽኝ ላይ ያተኮሩ ፊልሞች ተፈላጊ ሆነው አያውቁም። በተለይ በዚህ ረገድ አንድ ፊልም ከ10 ዓመት በኋላ ቀን ወጥቶለታል፤ ኮንቴጀን።
ስለ ኮንቴጀን ከማውራታችን በፊት ሌሎች በኮሮና ምክንያት ገበያው የደራላቸው ፊልሞችን እንቃኝ፡፡
በነባራዊ ሁኔታ ላይ መሠረት ያደረጉ ተከታታይ የቴሌቪዥን ዘጋቢ ፊልሞች (Docuseries) እጅግ ተፈላጊ ሆነዋል፤ በተለይም ጭብጣቸው ወረርሽኝ ላይ የሆኑቱ። ለምሳሌ 'How to Prevent an Outbreak' እጅግ የብዙ ተመልካችን ልብ ገዝቷል፤ ኔትፍሊክስ በዚህ ፊልም ተመልካቾች ቁጥር ተጨናንቋል።
93 Days (2016)፣ Outbreak (1995)፣ Warld War Z (2013)፣ I am Legend (2007)፣ Old Boy (2003)፣ The Light House (2019)፤ ሌሎቹ ተቀራራቢ ጭብጥ የያዙና በስፋት ተመልካች ያገኙ ፊልሞች ሆነዋል። ወደ በኋላ በአጭር በአጭሩ ጭብጦቻቸውን እንዳስሳለን።
ኮንቴጀን በድንገት ቀን የወጣለት ፊልም
ኮንቴጀን በፈረንጆች 2011 የወጣ ፊልም ነው። ጥቁር ስክሪኑ ሲገለጥ ከባድ ደረቅ ሳል ይሰማል። ፊልሙ ስለከፋ ወረርኝ እንደሆነ የምንገምተውም ያኔ ነው።
ያ ከባድ፣ አስጨናቂ ደረቅ ሳል ከተዋናይት ጉዌት ፓትሮው የሚወጣ ነው። በፊልሙ ቤቲ ኢምሆፍን ሆና ነው የምትጫወተው ጉዌት። ከሆንግ ኮንግ ወደ ሚኒያፑሊስ (ሜኔሶታ) ስትጓዝ ነው በሽታውን ይዛው የምትመጣው።
ሞት ከዚህ ይጀምራል። መጀመርያ ወንድ ልጇ ይሞታል። ወዲያውኑ እሷ ትከተለዋለች፤ የ'ርሷ ባል ሆኖ የሚሰራው ማት ዴመን በቤተሰቡ ሞት ያዝናል። እርሱ ግን ለቫይረሱ ተጠቂ አይሆንም። ሆኖም የፓትሮው ከሆንግ ኮንግ ወደ ሚኒሶታ የመመለስ ጉዞ ሲጠና በድብቅ ቺካጎ ጎራ ብላ እንደነበር ይደረስበታል።
የኮንቴጀን ጭብጡ ከሆንግኮንግ በሚነሳ ወረርሽኝ ላይ ያተኮረ ሲሆን ብዙዎቹ የፊልሙ የታሪክ መዋቅሮች አሁን ካለው ኮሮና ጋር ተቀራራቢ ትርክት አላቸው። ወረርሽኙ ከእሲያ መነሳቱ አንድ አስገራሚ ግጥምጥሞሽ ሆኖ ተመዝግቧል።
ኮንቴጀን ሌሎች ከኮሮና የሚያቀራርቡት በርካታ የሲኒማ ገቢሮችም አሉት። ለዚህም ነው ፊልሙ ንግርት ነው እስከመባል የደረሰው።
በፊልሙ ላይ ስመጥር ተዋንያን ይገኙበታል። ፈርጦቹ እንስት ተዋንያን ጉዌት ፓትሮው እና ኬት ዊንስሌት እንዲሁም እውቆቹ ማት ዴመንና ሎውረንስ ፊሽበርን እና ጁድ ሎው ድንቅ ብቃታቸውን አሳይተውበታል።
በነገራችሁ ላይ ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የሥነ ጤና ትምህርት ክፍል እነዚህን ስመጥር ተዋያን ከ10 ዓመት በኋላ በድጋሚ በቪዲዮ ስልክ እንዲገናኙ በማድረግ ለኅብረተሰቡ ስለ ወረርሽኙ ትምህርት እንዲሰጡ አድርጎ ውጤታማ ሥራ ሠርቷል።

የፎቶው ባለመብት, Twitter/Columbia Public Health
ስለ ኮሮና መልዕክቱ በ'ነርሱ አንደበት እንዲተላለፍ የሆነው ኮንቴጀን ፊልም በመላው ዓለም በከፍተኛ ቁጥር እየታየ በመሆኑ የተዋንያኑን ተሰሚነት ለመጠቀም ታስቦ ነው።
ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ገና ድሮ ከመነሻውም (በ2011) ማለት ነው፤ በፊልሙ ላይ ስለ ቫይረስ ወረርሽኝ ጠቃሚ ሳይንሳዊ ግብአት በመስጠት ተሳትፎ ነበረው። ለዚህም ይሆናል ከሳይንስ ብዙም ያልራቀው።
ፊልሙ እንደብዙዎቹ የሆሊውድ "የጥፋት ሲኒማዎች" በሰው ልጆች ላይ መዓት ሲመጣ የሚያሳይበት መንገድ የተጋነነ አለመሆኑ ልዩ ያደርገዋል።
እነዚህ ሰዎች ኮሮና እንደሚመጣ ገና ድሮ ታይቷቸው ነበር እንዴ የሚያሰኙ የታሪኩ ገቢሮችም በፊልሙ ላይ እዚህም እዚያም ይገኛሉ።
ለምሳሌ በአማካይ የሰው ልጅ ፊቱን በደቂቃ አምስት ጊዜ እንደሚነካካና ይህም ቫይረሱን እንደሚያሰራጨው፤ ቫይረሱ የተነሳበት እሲያ መሆኑና ቫይረሱ ወደተቀረው ዓለም እንዴት እንደተሰራጨ በፊልሙ የሚተርክበት መንገድ ከኮሮና እጅግ ተቀራራቢ ሆኗል።
‹‹በቅጽበት 200 ሰው እንደቅጠል ሲረግፍ በፊልሜ እያሳየሁ ተራ ግነት መፍጠር አልፈለኩም›› ብሎ ነበር የኮንቴጀን ፊልም ዳይሬክተር ስቲቨን ሶደርበርግ፤ ገና ያኔ ፊልሙ የተለቀቀ ሰሞን።
ስቲቨን ለምን ከተለመደው የሆሊውድ ግነት ገሸሽ እንዳለ ሲጠየቅ ‹‹አንድን ፊልም ይበልጥ ግነት በጨመርክበት ቁጥር ተመልካችህን ከእውኑ ዓለም እንዲርቅና የፈጠራ ሲኒማ እያየ እንደሆነ እንዲሰማው ታደርገዋለህ። ይህ እንዲሆን ስላልፈለኩ ነው›› ብሏል፡፡
የዚህ ፊልም አንዱና ዋንኛው ስኬት በቫይረስ ወረርሽኝ ዙርያ የቅርብ ሳይንቲስቶችን ምክር መሠረት አድርጎ መሠራቱ ነው የሚሉም አልጠፉም።
ኮንቴጀን ፊልም ከዛሬው እውነታ ጋር በማጠጋጋት እጅግ ስኬታማ ሆኗል ብንልም በርካታ ተመሳሳይ በዚህ ዘውግ የሚገኙ የሲኒማ ውጤቶች መሠረታቸው የሰዎች በወረርሽኝ የመያዝ ፍርሃት ላይ የቆሙ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, PA
ለምሳሌ የዞምቢ ፊልሞችን ማንሳት ይቻላል።
28 days Later (2002)፡ በዳኒ ቦየል ዳይሬክተርነት የተሰራ ሲሆን ማጠንጠኛው በእንግሊዝ የሚፈጠር ምስጢራዊ ወረርሽኝ ነው። የሚደንቀው በፊልሙ አንድ ክፍል ዋና ተዋናዩ በሎንዶን ከተማ ጭርታ መሀል ዌስትምኒስትር አቅራቢያ በሚገኝ ድልድይ ብቻውን ግራ ተጋብቶ ሲዋልል ያሳያል። ነዋሪዎች ቤታቸው ተከተው በሲኒማው መታየቱ ከአሁን የሎንዶን እውነታ ጋር እጅግ ተቀራራቢ ያደርገዋል።
93 days፡በዳይሬክተር ስቲቭ ጉከስ የተሰራ ፊልም ሲሆን በናይጄሪያ በኢቦላ ተይዞ ሌጎስ የገባን ሰው መሰረት አድርጎ፣ የጤና ባለሞያዎች ኢቦላን ለመቆጣጠር የሞት ሽረት ትግል ሲያደርጉ ያሳያል። ፊልሙ በያዘው ጭብጥ ለዚህ የኮሮና ዘመን ተስማሚ በመሆኑ ተመራጭ ሆኗል።
outbreak (1995)፡ በዎልጋንግ ፒተርሰን ዳይሬክት የተደረገ ፊልም ሲሆን ከአፍሪካ ወደ ካሊፎርኒያ በመጣ አንድ ዝንጀሮ አማካኝነት የሚከሰት የቫይረስ ወረርሽኝን መሠረት ያደረገ ታሪክ ነው፡፡ በፊልሙ ስመጥሮቹ ደስቲን ሆፍማን ሬኔ ሩሶና ሞርጋን ፍሪማን ይተውኑበታል።
Warld War Z ፡ ብራድ ፒት በዋናነት የሚተውንበት ሲኒማ ሲሆን አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞ ባልደረባ ምንነቱ ያልታወቀ ወረርሽኝ ለማቆም በመላው ዓለም ሲሯሯጥ የሚደርስበትን ውጣ ውረድ የሚተርክ ፊልም ነው፤ ዳይሬክተሩ ማይክ ፎስተር ነው።
I am Legend: የሳይንሳዊ ልቦለድ ዘውግ ያለው የፍራንሲስ ሎውረን ፊልም ነው። በዚህ ፊልም ኒውዮርክ ከተማ መዓት ከደረሰባት በኋላ ዊል ስሚዝ ብቻውን ሲንከራተት ይታያል። አሁን በኒውዮርክ ካለው እውነታና ሁኔታ አንጻር I am Legend እጅግ ተቀራራቢ በመሆኑ ይህ ፊልም በጭብጡ ምክንያት ተፈላጊ እንዲሆን ሳያደርገው አልቀረም።
Old Boy፡ ዋናው ገጸ ባሕሪ ከተጠለፈ በኋላ ለ15 ዓመታት ከአጋቹ በቀር ከሰው ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ሳይኖረው የሚኖረውን ሕይወት የሚቃኝ ፊልም ነው። አሁን በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ቤታቸውን ቆልፈው እንዲቀመጡ በመገደዳቸው ይህ ታሪክ ከዚህ እውነታ መቀራረቡ ተፈላጊ ሳያደርገው አልቀረም።
The Light House (2019): ከአስጨናቂ (ሆረር) ዘውግ የሚመደበውን ይህንን ሲኒማ ሮበርት ኤገርስ ዳይሬክት አድርጎታል። በአንዲት ደሴት (ኒው ኢንግላንድ አይላንድ) ላይ ለብቻቸው ተነጥለው በሚኖሩ ሁለት ሰዎች የአእምሮ ጤንነታቸውን ለማቆየት ሲጥሩ የሚያሳይ ሲኒማ ነው።



















