በኒጀር ሁለት መንደሮች ላይ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት በርካቶች ተገደሉ

የኒጀር ወታደር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኒጀር ወታደር

የእስላማዊ ቡድን አባላት ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉ ታጣቂዎች በኒጀር ሁለት መንደሮች ላይ በፈጸሙት ጥቃት ቁጥራቸው በርከት ያሉ ሰዎችን መግደላቸው ተነገረ።

በጥቃቱ ቾምባንጉ በተባለች መንደር 49 ሰዎች ሲገደሉ 17 የሚሆኑት ደግሞ ክፉኛ መቁሰላቸው ታውቋል። ዛሩምዳርየ በተባለችና በምዕራብ ኒጀር ከማሊ ጋር በምትዋሰነው ሌላኛዋ መንደር ደግሞ 30 ሰዎች መገደላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

በታጠቁ ኃይሎች የሚፈጸሙ መሰል ጥቃቶች በአፍሪካ ሳህል አካባቢ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ ይገኛሉ።

ፈረንሳይ ቅዳሜ ዕለት በማሊ ሁለት ወታደሮቿ መገደላቸውን አስታውቃለች። ከሰዓታት በፊት ደግሞ ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት ያለው እስላማዊ ቡድን፣ በማሊ ሰኞ ዕለት በተለያዩ ቦታዎች ሦስት የፈረንሳይ ወታደሮችን ገድያለሁ ብሎ ነበር።

ፈረንሳይ የምዕራብ አፍሪካንና የአውሮፓን ጥምረት ኃይልን በመምራት ባሳህል አካባቢ እስላማዊ ታጣቂ ቡድኖችን እየተዋጋች ትገኛለች።

ቢሆንም ግን አካባቢው የጎሳ ግጭት፣ ዝርፊያ፣ የሰው እና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር የተስፋፋበት ቀጠና መሆኑን ቀጥሏል። የትናንቱን ጥቃት ተከትሎ የአገር ውስጥ ሚንስትሩ አልካቼ አልሃዳ ወደ ስፍራው ወታደር መንቀሳቀሱን ገልጸዋል። ይሁንና ጥቃቱ እንዴት እንደተፈጸመ ያብራሩት ነገር የለም።

የአካባቢው ባለስልጣናት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ሲገልጹ፣ አንድ የዚያው አካባቢ ጋዜጠኛ ደግሞ የሟቾች ቁጥር 50 መድረሱን ዘግቧል።

ኒጀርን ከማሊና ቡርኪናፋሶ ጋር የሚያዋስነው ቲላበሪ ግዛት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የጂሃዲስት ኃይሎች በስፋት ጥቃት የሚፈጽሙበት አካባቢ ሆኗል።

ከተሽከርካሪ ላይ በመሆን አክራሪ ኃይሎች የሚፈጽሙትን ጥቃት ለመከላከል ሲባል በሞተር ሳይክል መሽከርከር ከተከለከለ ከአንድ ዓመት በላይ አስቆጥሯል።

ኒጀር በሌላ በኩል ከናይጀሪያ በሚነሳው የቦኮሃራም ቡድንም ጥቃት ይደርስባታል። ባለፈው ወር በኒጀር ደቡብ ምሥራቅ ዲፋ አካባቢ ይሄው የቦኮሃራም ቡድን በፈጸመው ጥቃት ቢያንስ 27 ዜጎቿ ተገድለዋል።

በቅርቡ ቲላቤሪ አካባቢ የደረሰው ጥቃት ብሔራዊ ምርጫ በሚካሄድበት ወቅትና አገሪቱን ለሁለት አምስት ዓመታት በፕሬዝዳንትነት የመሩት መሐማዱ ኢሱፉ በተሸነፉበት ዕለት ነበር።

የአገሪቱ የምርጫ ባለስልጣናት ጊዜያዊ የምርጫ ውጤቱን ቅዳሜ ያሳወቁ ሲሆን የቀድሞው ሚንስትርና የገዥው ፓርቲ አባል ሞሐመድ ባዙም እየመሩ መሆኑ ታውቋል።

የአገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት የዚህኛውን ምርጫ ሐቀኝነት ካረጋገጠ በኋላ በሚቀጥለው የካቲት ወር በአገሪቱ ሁለተኛው ዙር ምርጫ ይካሄዳል ተብሏል።