ኮሮናቫይረስ ፡ ታዋቂው የቴሌቪዥን አቅራቢ ላሪ ኪንግ በኮቪድ-19 ተይዞ ሆስፒታል ገባ

ላሪ ኪንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ላሪ ኪንግ

ታዋቂው የቴሌቪዥን አቅራቢ ላሪ ኪንግ ኮሮናቫይረስ እንዳለበት በመረጋገጡ ሎስአንጀለስ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ህክምና እየተደረገለት መሆኑን የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።

ለላሪ ኪንግ ቤተሰብ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለኤቢሲ ኒውስና ቀድሞ ይሰራበት ለነበረው ሲኤንኤን ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ላሪ ሆስፒታል ከገባ ከሳምንት በላይ ሆኖታል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የልብ ህመምን ጨምሮ በርካታ የጤና እክሎች ሲያጋጥሙት የነበረው ላሪ፤ ከ60 ዓመት በላይ በዘለቀው የቴሌቪዥን አቅራቢነት ሙያው በርካታ ሽልማቶችናና እውቅናዎችን አግኝቷል።

የ87 ዓመቱ ላሪ ተወካዮች እስካሁን በይፋ ወጥተው ሆስፒታል ስለመግባቱና አሁን ስላለበት ሁኔታ ምንም አይነት መግለጫ ስላልሰጡ ዝርዝር መረጃ የለም።

ላሪ ኪንግ መጀመሪያ ላይ እውቅናን ያገኘው በ1970ዎቹ በሬዲዮ ያቀርበው በነበረ ዝግጅቱ ነበር። ከዚያም ከ1985 እስከ 2010 (እአአ) በሲኤንኤን ቴሌቪዥን ላይ በተለያዩ መስኮች የዓለማችን ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑ ታዋቂ ግለሰቦች ጋር በሚያደርገው ቃለ ምልልስ እውቅናን አትርፏል።

ላሪ ኪንግ ከሬዲዮና ከቴሌቪዥን ሙያው በተጨማሪ በአሜሪካ ታዋቂ ለሆነው 'ዩኤስኤ ቲዴይ' ለተባለው ጋዜጣ ለ20 ዓመታት አምደኛ ሆኖ ጽሁፎችን ሲያርብ ቆይቷል።

በቅርቡም በሩሲያ መንግሥት በሚተዳደረው የስርጭት ተቋም ስር ለሚቀርቡት 'ሁሉ' እና 'አርቲ' ለተባሉት ቴሌቪዥኖች 'ላሪ ኪንግ ናው' የተሰኘ ዝግጅትን ያቀርብ ነበር።

ታዋቂው ቃለ መጠይቅ አድራጊ ላሪ ኪንግ ሙያውን እያከናወነ ባለበት ዘመን ውስጥ የስኳር፣ የልብ ህመምና የሳምባ ካንሰርን ጨምሮ በርካታ ከባድ የጤና ችግሮች ገጥመውት ነበር።

በተጨማሪም ካሉት አምስት ልጆች ውስጥ ሁለቱ በልብ ህመምና በሳንባ ካንሰር በሳምንት ልዩነት ውስጥ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ሞተውበታል።

ላሪ ኪንግ ከ30 ዓመት በፊት የልብ ህሙማን ሆነው የገንዘብ አቅምም ሆነ የጤና መድን የሌላቸውን ሰዎች የሚረዳ የበጎ አድራጎት ድርጅት በስሙ በማቋቋም ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።