የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ቀረጥ መነሳት የዩኬ የመብት ተሟጋቾችን አስደስቷል

ላውራ ኮይተን

የፎቶው ባለመብት, LAURA CORYTON

በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ከጥር 1 ጀምሮ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ላይ ተጥሎ የነበረው 5 በመቶ ቀረጥ ይነሳል።

የአውሮፓ ሕብረት ሕግ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን እጅግ አስፈላጊ በሆኑ ቁሳቁሶች ዝርዝር ስላላካተተ አባል አገራቱ ቀረጥ መክፈል ይጠበቅባቸዋል።

ቻንስለር ሪሺ ሱናክ ይህ ሕግ እንዲሻር ያደረጉ ባለሥልጣን ሲሆኑ፤ የመብት ተሟጋቾች "ጾተኛ ቀረጥ" ያሉት ክፍያ በመነሳቱ ደስታቸውን ገልጸዋል።

የመብት ተሟጋቿ ላውራ ኮይተን "ውሳኔው ከጾተኝነት ጋር የሚደረገው ትግል አካል ነው" ብለዋል።

ዩኬ ቀረጡን ማንሳት የቻለችው የአውሮፓ ሕብረት የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ሕጎችን ከዚህ በኋላ መከተል ግዴታዋ ስላልሆነ ነው።

የአውሮፓ ሕብረትም ቀረጡን ለማንሳት ሂደት ጀምሯል።

እአአ 2018 ላይ የአውሮፓ ኮሚሽን የተጨማሪ እሴት ታክስ ሕግጋትን ለመቀየር ሐሳብ አቅርቦ ነበር።

ሕጉ ከተሻሻለ አገራት ከወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ላይ ቀረጥ ማንሳት ይችላሉ። ሁሉም አባል አገራት በማሻሻያው አልተስማሙም።

በሌላ በኩል አየርላንድ ቀረጡን ሙሉ በሙሉ ያነሳችው የአውሮፓ ሕብረት 5 በመቶ ቀረጥ የመጣል ሕግን ከማውጣቱ በፊት ነው።

የ27 ዓመቷ የመብት ተሟጋች ላውራ ከወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ላይ ቀረጥ እንዲነሳ ንቅናቄ የጀመረችው በ21 ዓመቷ ነበር።

ቀረጡ ማኅበረሰቡ ስለ ሴቶች የተዛባ አመለካከት እንዲያዳብር ያደርጋል ትላለች።

ጥቅምት ላይ ስኮትላንድ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያን በነጻ በማቅረብ ከዓለም ቀዳሚዋ አገር ሆናለች።

ፋውካት ሶሳይቲ በተባለ የመብት ተቆርቋር ተቋም ዋና ኃላፊ ፌሊሺያ ዊሎ "የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያን እንደ ቅንጦት እቃ ይቆጥር የነበረው ሕግ ታሪክ ሆኗል። እዚ ለመድረስ ብዙ ተጉዘናል" ብላለች።

ቀረጡ መነሳቱ እያንዳንዷ ሴት በመላው ሕይወቷ 40 ፓውንድ እንድታተርፍ እንደሚያደርግ የወጣው መረጃ ይጠቁማል።

ዓመታት የወሰደው ትግል

ታክሱ እንዲነሳ ዓመታት የዘለቀ ንቅናቄ ነው የተደረገው።

2016 ላይ ወግ አጥባቂው የዩኬ መንግሥት ከወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች የሚሰበሰበው ቀረጥ በሴቶች ዙርያ ለሚሠሩ የተራድኦ ድርጅቶች እንዲሰጥ ወስኖ ነበር።

"ቀረጡ ሲነሳ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ዋጋ ይቀንሳል። በተለይም በወረርሽኙ ሳቢያ ኑሮ ለከበዳቸው አቅመ ደካሞች ትልቅ ዜና ነው" ትላለች ላውራ።

ፍሪ ፔሬድስ የተባለው ንቅናቄ አባል የሆነችው ጠበቃ ጀማ አቦት 2019 ላይ በእንግሊዝ ትምህርት ቤቶች የወር አበባ የንጽህና መጠበቂያ በነጻ እንዲከፋፈል አስችላለች።

ቀረጥ መነሳቱ ትልቅ እርምጃ እንደሆነ ትናገራለች።

"እጅግ አስፈላጊ ያልሆኑ ምርቶች ዝርዝር ውስጥ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ መካተቱ አግባብ አይደለም። የጾታ እኩልነት የሰፈነበት ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ወደኋላ ይጎትታል" ስትልም አስተያየቷን ሰጥታለች።

ላውራ ከእህቷ ጁልያ ጋር በመሆን 'ሴክስ ኤድ ማተርስ' የተባለ ተቋም መስርታለች። መምህራን ለተማሪዎች ስለ ወሲብ ትምህርት እንዲሰጡ ያግዛል።

ተቋሙ 150 መምህራንን ጠይቆ በሠራው የዳሰሳ ጥናት መሠረት፤ ዩኬ ውስጥ አሁንም ስለ ወር አበባ የተዛባ አመለካከት ይስተዋላል።

ላውራ "ስለ ወር አበባ የተዛባ አመለካከት ስላለ ሴቶች የወር አበባቸው ሲመጣ የንጽህና መጠበቂያ ለመጠየቅ አይደፍሩም" ትላለች።

ይህንን ለመቀየር የላውራ እና የጀማ አይነት እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።