በሕንድ የወር አበባ ላይ ያሉ ሴቶች ለምን ማዕድቤት እንዳይገቡ ይከለከላሉ?

የፎቶው ባለመብት, Niraj Gera
በሕንድ የወር አበባ እያየች ያለች ሴት ሁሉን አቀፍ መገለል ይደርስባታል። እንደጎደፈች ትቆጠራለች። ከማኅበራዊና መንፈሳዊ ሕይወት ትገለላለች። ቤተ መቅደስ አትገባም፤ እንኳን ቤተ መቅደስ ማዕድቤት ምግብ ለማብሰልም እንዳትገባ ትደረጋለች። ይህ በዚያች አገር አሁንም ድረስ ያለና በስፋት የሚታይ ሀቅ ነው።
የዓለም የወር አበባ ቀንን አስመልክቶ ዝነኛው የፎቶግራፍ ጥበበኛ ኒራጅ ጌራ የወር አበባ ውብ ተፈጥሮ እንጂ ነውር እንዳልሆነ ለማሳየት ሞክሯል። እነዚህ የፎቶግራፍ ሥራዎቹ ቀጥተኛና ሀቁን የሚያፍረጠርጡ በመሆናቸው ማንኛውም ተመልካች እንዲሁ አንደዋዛ አይቶ የሚያልፋቸው አይደሉም።
በሕንድ በወር አበባ ጉዳይ ላይ ግልጽ ውይይት ስለማይበረታታ 71 ከመቶ የሚሆኑ ልጃገረዶች የመጀመርያውን የወር አበባ የሚያዩት "ፔሬድ" ምን እንደሆነ ጨርሶዉኑ ሳይረዱ ነው።
በጉዳዩ ላይ ለውጥ ለማምጣት የሚሠሩ ትጉሃን እንደሚናገሩት ከሆነ በሕንድ ወላጆች ለልጆቻቸው ስለ ወር አበባ ለማስረዳት ስለሚያፍሩ ወይም ስለማይደፍሩ ወይም ተገቢ ነው ብለው ስለማያስቡ ሴት ልጆቸውን ለመሸማቀቅ፣ ለድንጋጤና ለፍርሃት ይዳርጓቸዋል።
የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ እንደልብ ማግኘት በሕንድ ሌላ ትልቅ ራስ ምታት ነው።
ከሁለት ዓመት በፊት የመብት ተሟጋቾች ለወራት የዘለቀ እልህ አስጨራሽ ዘመቻ በማድረግ መንግሥት በወር አበባ የንጽህና መጠበቂያ ላይ ጥሎት የነበረውን የ12 ከመቶ ግብር እንዲያነሳ ማስገደድ ችለዋል።
የመብት ተሟጋቾች በወቅቱ ያነሱት አንኳር ነጥቦች ሁለት ናቸው። አንዱ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ እንደ ቅንጦት ዕቃ ተደርጎ መታሰብ እንደሌለበት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የወር አበባ ሴቷ ተፈጥሮ የሰጣት ጸጋ እንጂ ሲሻት እንዳይመጣ የምታደርገው ነገር አለመሆኑን ነው።
ያም ሆኖ የመብት ተሟጋቾቹ ያስገኙት የ12 ከመቶ የግብር ቅነሳ ገና የመጀመሪያው ሂደት እንጂ የመጨረሻው ግብ አይሆንም። በአገሪቱ ሁሉም ሴቶች የንጽሕና መጠበቂያ የማግኘት ሙሉ መብትን ሊጎናጸፉ ይገባል።
ይህን ለመገንዘብ አንዳንድ የቁጥር መረጃዎችን ማጤን ያሻል።

የፎቶው ባለመብት, Niraj Gera
በሕንድ የወር አበባ ከሚያዩ 355 ሚሊዮን ሴቶች ውስጥ 36 ከመቶ ብቻ ናቸው መሠረታዊ የንጽህና መጠበቂያን የሚያገኙት። የተቀሩት ግን እንደ አፈር፣ ጭቃ፣ ብጣሽ ጨርቅ፣ ገለባ፣ ቅጠላ ቅጠልና ሌሎች ለጤና ጠንቅ የሆኑ ነገሮችን ነው የሚጠቀሙት።
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ደግሞ በተለይ አሁን በኮሮናቫይረስ ምክንያት የንጽህና መጠበቂያ ምርትና አቅርቦት እንደልብ ባለመኖሩ በርካታ የሕንድ ሴቶች ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን ነው።
ድህነት ለዚህ ችግር ሌላው ምክንያት ነው።
የፕላን ኢንተርናሽናል ዩኬ ጥናት እንደሚያስረዳው ከሆነ በሕንድ ከ10 ሴቶች አንዷ ከ21 ዓመት በታች ያለች ሴት መሰረታዊ የንጽህና መጠበቂያ ማግኘት ስለማትችል ጋዜጣ ወይም የሽንት ቤት ሶፍት አልያም ካልሲን በምትኩ ለመጠቀም ትገደዳለች።
በሕንድ ሴቶች ገና በወጣትነታቸው ከእንደዚህ ዓይነት መሳቀቅና ህመም ጋር መኖርን ተላምደውታል፤ ወይም ለማላመድ ተገደዋል።
ከዚህ ችግር ለመውጣትና ለመወያየት ሲጥሩ እምብዛምም አይታዩም። አሁን አሁን ግን ከማኅበራዊ ሚዲያው መስፋፋት ጋር ተያይዞ ሴቶች ከወር አበባ ጋር የተያያዘ ታሪካቸውን በድፍርት ማጋራት ጀምረዋል።
የሚገርመው ሴቶች ታሪካቸውን በማጋራታቸው ብቻ የሞራል ፖሊስ ነን ባዮች ያንጓጥጧቸዋል፤ ስሜታቸውን የሚጎዱ ቃላትን ጭምር እየተናገሩ ሊያሳፍሯቸው ይሞክራሉ። ሺህዎች የበይነ መረብ ጥቃትና ዛቻን ያደርሱባቸዋል።
በሕንድ አሁንም ድረስ ሚሊዮኖች የንጽሕና መጠበቂያ አያገኙም።

የፎቶው ባለመብት, Niraj Gera
ከዚህ በላይ በሚታየው ምሥል ላይ በቀን ሠራተኝነት የሚተዳደር ቤተሰብ ልጅ የንጽህና መጠበቂያ አስፈልጓት ነገር ግን ቤተሰቧን መጠየቅ ጥፋተኝነት ስሜት ተሰምቷት ስትጨነቅ ይታያል።
ለቤተሰቧ ምርጫው ከባድ ነው፤ የእርሷን የንጽህና መጠበቂያ ፍላጎት ማሟላት ይሻላል ወይስ የሚላስ የሚቀመስ ማቅረብ? ይህ የብዙ ቤተሰቦች ሕይወት ነው።
ይህ የፎቶግራፍ ጥበበኛ በመሠረተው ሂዩማኒቲ ፋውንዴሽን አማካኝነት ሁሉም ከድህነት ወለል በታች ለሚኖሩ የሕንድ ሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ማግኘት መብት እንዲሆን እየታገለ ይገኛል።
በሕንድ በየዓመቱ 23 ሚሊዮን የሚሆኑ ሴቶች የወር አበባ ካዩ በኋላ ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ።
ለዚህም አንዱ ምክንያት በቂ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ አለመኖር ነው።

የፎቶው ባለመብት, Niraj Gera
ልጃገረዶች የወር አበባ መጠበቂያ ማግኘት ስለማይችሉ ልብሳቸው ላይ ደም ሲታይ በጓደኞቻቸው መንጓጠጥ ስለሚደርስባቸው ያን በመፍራት ከትምህር ቤት ይቀራሉ።
ሌላ ጥናት እንዳስረዳው ወንዶች ብቻ ሳይሆን በርካታ ሴቶች የወር አበባ ማለት መጉደፍ ወይም አለመንጻት መሆኑን አምነው እንዲቀበሉ ሆነዋል።
በወር አበባ ጊዜ ከማኅበራዊ ሕይወት መገለላቸውንም ተገቢና ትክክለኛ አደርገው ያዩታል።
ሆኖም ይህ ጉዳይ የሕንድ ችግር ብቻ አይደለም። "የወር አበባም ተፈጥሯዊና ጤናማ ነገር አድርገን መመልከት ይኖርብናል። በወር አበባ ዙርያ ያሉ አሉታዊ አመለካከቶች ቀስ በቀስ ሊጠፉ ይገባል" ይህ የሚሆነው ደግሞ ተፈጥሮን ስንቀበል ነው" ይላል የፎቶግራፍ ጠቢቡ ጌራ።
ጌራ የመጨረሻ መልእክት አለው። "ስለ ወር አበባ በግልጽ መነጋገር የመፍትሄዎች ሁሉ ቁልፍ ነው።"













