ብዙም ያልታወቁት ከወር አበባ ጋር የሚከሰቱ የባህሪ ለውጦችና አደገኛ ውጤታቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
'ፒኤምዲዲ' ይባላል፤ ብዙዎች እንዳለባቸው እንኳን አያውቁትም። ለወር አበባ ከደረሱ ሴቶች መካከል 8 በመቶዎቹን የሚያጠቃ ሲሆን ቁጡ መሆንና እረፍት አልባነት ይስዋልባቸዋል። ነገር ግን ስለዚህ የጤና እክል ብዙ ሰዎች በተለይም ሴቶች ግንዛቤ የላቸውም።
ካሮላይን ሄናጋን የ30 ዓመት ሴት ነች። በሥራዋ በጣም የተወጠረች ስትሆን ለእንግሊዙ የአገር ውስጥ ጉዳይ መስሪያ ቤት ነው የምትሰራው። በተደጋጋሚ የሚያጋጥማት ጭንቀትና ያልተለመዱ ባህሪያት ምናልባት ከሥራ ጫና ጋር የተያያዙ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነበር የምትገምተው።
''ማቆሚያ የሌለው አስጨናቂ ጉዞ'' ብላ ነው የምትገልጸው የሚሰማትን ስሜት።
አስጨናቂው ስሜት ምናልባት የሚለቀን ከሆነ ብላ አጠር ያለ እረፍትም እስከ መውሰድ ደርሳ ነበር። ነገር ግን ምንም የተለወጠ ነገር እንዳልነበረ ታስታውሳለች ካሮላይን።
በእያንዳንዱ ጠዋት ከመጥፎ ስሜት ጋር ከመናሳት ባለፈ ከሰዎች ጋር ያላትን ማኅበራዊ ህይወትንም ጭምር አስቸጋሪ አድርጎታል።
የሆድ በከፍተኛ ሁኔታ መነፋት፣ ከባድ ድካም፣ ጭንቀት፣ ከሰዎች ጋር በትንሽ በትልቁ መጣላት፣ ከአልጋ አለመውረድ፣ ሥራ አካባቢ ግድ የለሽ መሆን ካሮላይን ካጋጠሟት መካከል ዋናዎቹ ናቸው።
በመጨረሻ ግን እነዚህ ነገሮች በሙሉ ከወር አበባዋ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ደረሰችበት።
የሄደችባቸው ዶክተሮች (ሁሉም ወንዶች ነበሩ) ከወር አበባ በፊትና በወር አበባ ወቅት የሚከሰተው 'ፕሪማኑስትሪያል ሲንድረም ወይም 'ፒኤምኤስ' የሚባለው ተፈጥሮአዊ ሂደት እንደሆነ ቢነግሯትም "ለምን እኔ ላይ እንደዚህ በረታ?" የሚል ጥያቄ ፈጠረባት።
በግሏ ሌሎች ባለሙያዎችን በማማከርና በይነ መረብ ላይ ያሉ መረጃዎችን በመጠቀም ችግሯ ላይ ደረሰችበት። 'ፕሪማኑስትሪያል ዲስፎሪክ ዲስኦርደር' ወይንም በአጭሩ 'ፒኤምዲዲ' ይባላል።
በዚህ ችግር የሚጠቁ ሴቶች የማይቋረጥ የድካም ስሜት፣ ከባድ የራስ ምታት፣ የባህሪ ቶሎ ቶሎ መለዋወጥ የሚያጋጥማቸው ሲሆን ሲብስ ደግሞ እራሳቸውን እስከማጥፋት ሊያደርሳቸው ይችላል።
በቅርቡ በተሰራ አንድ ጥናት መሰረት 'ፒኤምዲዲ' ካለባቸው ሴቶች 15 በመቶ የሚሆኑት እራሳቸውን ለማጥፋት ሙከራ አድርገዋል። ካሮላይንም ከእነዚህ ሴቶች መካከል አንዷ ናት።
በመጨረሻ ግን ከብዙ ጊዜ በኋላ የዘርፉን ባለሙያ አግኝታ ህክምና መከታተል ችላለች። ነገር ግን ህክምናው ጊዜያዊ እንጂ ሙሉ መፍትሄ ሊያስገኝላት አልቻለም ነበር።
በዚህም ምክንያት ከዶክተሯ ጋር በመማከር እ.አ.አ. በ 2015 በ36 ዓመቷ ማህጸኗን በቀዶ ህክምና በማስወጣት አስባው የማታውቀውን ነገር በወጣትነቷ ለማድረግ መገደዷን ትናገራለች።
'ፕሪማኑስትሪያል ሲንድረም ወይም 'ፒኤምኤስ' የተለመደውና ከወር አበባ አንድ ወይም ሁለት ሳምንት በፊት የሚጀምር ሲሆን በርካታ ሴቶች የሚያጋጥማቸው አይነት ችግር ነው።
ነገር ግን 'ፕሪማኑስትሪያል ዲስፎሪክ ዲስኦርደር' ወይንም 'ፒኤምዲዲ' ያለባቸው ሴቶች በቀላሉ ሊገላገሉት የሚችሉት ነገር አይደለም። ልክ እንደ ማንኛውም አይነት በሽታ የህክምና ክትትል የሚያስፈልገው ነው።
''ይህ ችግር በቀላሉ ሊታይ የማይገባውና ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫና ሊያስከትል የሚችል ነው'' ይላሉ በኤሊኖይስ ዩኒቨርሲቲ የሴቶችን ሥነ ልቦናን የሚያጠኑት ቶሪ ኢሰንሎር።
አንዳንድ ባለሙያዎች ደግሞ ሴቶች በዚህ ችግር የሚጠቁ መሆኑ እስካልታወቀ ድረስ ባህሪያቸው በተቀያየረና ቁጡ በሆኑ ቁጥር በሥራ ቦታ፣ ከጓደኞቻቸው እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ከባድ አደጋ ላይ ይወድቃል ይላሉ።
ጥናቶች እንደሚጠቁት በመላው ዓለም ከሚገኙና ለአቅመ ሄዋን ከደረሱ ሴቶች መካከል ከ3 እስከ 8 በመቶ የሚሆኑት በዚሁ 'ፒኤምዲዲ' የሚጠቁ ሲሆን ይህም በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሴቶች የሚመለከት መሆኑን ያሳያል።
ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ በዘርፉ የተሰማሩ የህክምና ባለሙያዎች ዘንድ እንኳን ስለ 'ፒኤምዲዲ' ብዙም እውቀት አለመኖሩ ነው።
በችግሩ ከሚያጋጥማቸው ሴቶች ጋር በተያያዘ ከታዩ ክስተቶች መካከል በእንግሊዝ አንዲት ሴት የመጠጥ ቤት አስተናጋጅን በስለት ወግታ የገደለችበትና በአሜሪካ ደግሞ ከፍጥነት በላይ በማሽከርከሯ ያስቆማት ፖሊስ ላይ ጥቃት ያደረሰችው ሴት ጉዳይ የሚጠቀስ ነው።
በህክምና ባለሙያዎች እንደተረጋገጠው ሁለቱም ሴቶች በ'ፒኤምዲዲ' የሚሰቃዩ ነበሩ።
ካሮላይን ሄናጋን ሁሉም የህክምና ባለሙያዎች ስለችግሩ በቂ እውቀት ኖሯቸው በዚሁ ምክንያት ለሚሰቃዩ ሴቶች መፍትሄ እንደሚያገኙ ተስፋ ታደርጋለች። ''የትኛዋም ሴት በዚህ ምክንያት በፍርሀትና በጭንቀት መኖር የለባትም'' ትላለች።



















