ለሁለት ዓመታት የአስራ ሁለት ዓመት ልጁን በጓደኞቹ ያስደፈረው አባት ህንድን አስቆጣ

የታዳጊዋ መኝታ ክፍል ግድግዳ

የፎቶው ባለመብት, NEBULA MP

ቅዳሜና እሁድ ለሁለት ዓመታት ያህል የአስራ ሁለት ዓመቷ ህንዳዊቷ ታዳጊ በአባቷ ጓደኞች እንዲሁም አባቷ ባመጣቸው ሰዎች ተደፍራለች።

[ማስጠንቀቂያ፦ ፅሁፉ የሚሰቀጥጡና የሚረብሹ መረጃዎች ስላሉት ሲያነቡ ይህንን ከግምት ውስጥ እንዲያስገቡ]

ይሄ ሁሉ የተጀመረው በአንዲት ዕለት ነው፤ የታዳጊዋ አባት ጓደኞቹን ለመጠጥ ጋብዟቸው ነበር። በመጠጥ ኃይል የተገፋፉት ግለሰቦች ቤተሰቦቿ ፊት ይጎነታትሏት ጀመር። አንዳንዶቹም እናቷን ይዘዋት አንደኛው መኝታ ክፍል ውስጥ በተደጋጋሚ ይገቡ፣ ይወጡ ነበር።

በዚህ የተጀመረው መጎነታተል እዚያ ላይ አላቆመም። አንድ ዕለትም አባቷ ከአንደኛው ጓደኛው ጋር እንድትሆን አድርጎ የአንደኛውን መኝታ ቤት በር ከውጭ ቆለፈባት፤ ሰውየውም ደፈራት።

የልጅነት ዓለሟም በዚህ ተቀጨ፤ ስቃይዋም አንድ ተብሎ ተጀመረ። አባቷ ጓደኞቹም የሆኑም ያልሆኑም ወንዶች ጋር በመደወል ቀጠሮ በመያዝ ገንዘብ እየተቀበል፤ ልጁን ማስደፈር ተያያዘው።

ባለሙያዎች እንደሚያምኑት ህፃኗ ቢያንስ በሰላሳ የተለያዩ ወንዶች ተደፍራለች።

ከጥቂት ወራት በፊት ከመምህራን በደረሰ ጥቆማ በህፃናት ደህንነት ላይ የሚሰሩ ኃላፊዎች ታዳጊዋን ከትምህርት ቤቷ ወስደው በመጠለያ ቤት ውስጥ አስቀምጠዋታል። በተደረገላትም የህክምና ምርመራ በተደጋጋሚ እንደተደፈረች ማረጋገጥ ተችሏል።

አባቷን ጨምሮ አራት ወንዶችም በቁጥጥር ስር ውለዋል። እነሱም በመድፈር፣ ህፃናትን በወሲብ ንግድ በማሰማራትና በጥቃት ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን ዋስም ተከልክለዋል።

ከነዚህ ግለሰቦች በተጨማሪ ፖሊስ አባቷ ያውቃቸዋል ያላቸውና የመድፈርና አካላዊ ጥቃት አድርሰውባታል የተባሉ አምስት ግለሰቦችንም እየፈለገ ነው።

መርማሪዎች ልጅቷን በመድፈር የተጠረጠሩ ሃያ አምስት ወንዶች ስምና ፎቶዎችን ይዘዋል።

"ፊታቸውን አላስታውስም፤ ብዙው ነገር ብዥ ብሎ ነው የሚታየኝ" ብላለች ታዳጊዋ ጥቃቱን ስለፈጸሙባት ሰዎች ስትጠየቅ።

ቤተሰቦቿ በደቡባዊ ህንድ በምትገኝ ጥሩ አቅም ያላቸው ሰዎች በሚኖሩባት ከተማ ቢኖሩም፤ እነሱ ግን ኑሯቸው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በመስከረም ወር ላይ የታዳጊዋ ጎረቤቶች የሆኑ መምህራን ለትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች ልጅቷ ችግር ሊኖርባት እንደሚችል አሳውቀው ነበር።

"ቤተሰቦቿ አንድ የሆነ ችግር ያለባቸው ይመስለናል፤ ቤቷም ውስጥ ምን እንደሆነ ባናውቅም የሆነ ግራ ግብት የሚል ጉዳይ እየተከናወነ ነው፤ እስቲ ህፃኗን አናግሯት" ብለው ተናገሩ።

የትምህርት ቤቱ አስተዳደርም ከሴቶች ድጋፍ ቡድን አማካሪ በማምጣት ህፃኗን እንዲያናግሯት አደረጉ።

የታዳጊዋ ደብተር

የፎቶው ባለመብት, NEBULA MP

በመምህራኑና ሰራተኞች ክፍል ውስጥም "እስቲ ስለ ራስሽና ስለ ቤተሰቦችሽ ትንሽ ንገሪን" አለቻት አማካሪዋ።

ለሰዓታትም ከታዳጊዋ ባወሩበት ወቅት፤ አባቷ ሥራ ስሌለው ሁኔታዎች ፈታኝ እንደሆኑ ተናገረች። የቤት ኪራይም ስላልከፈሉ ከቤት ሊያስወጧቸውም እንደሚችሉ እያለቀሰች በልጅነት አንደበቷ አወራች።

ትንሽ ቆይታም በዝምታ ተዋጠች። አማካሪዋ በክፍል ውስጥ ስለሚማሩት የሥርዓተ ፆታ ክፍለ ጊዜና ምን ያህል ህፃናትስ ጥቃት እንደሚደርስባቸው ጠየቀቻት።

"እኛም ቤት ጥቃቶች ይደርሳሉ፤ አባቴ እናቴ ላይ ጥቃት ይፈፅማል" ብላ ምላሽ ሰጠች።

አማካሪዋም "እስቲ ዘርዘር አድርገሽ ንገሪኝ" ብላ ጠየቀቻት። አንድ ቀን እናቷን ሊያይ የመጣ ግለሰብ ጥቃት እንዳደረሰባት ተናገረች። እናቷም በአፀፋው ግለሰቡን አስጠንቅቃዋለች አለች። ነገር ግን እሷ በሌለችበት ወቅት እናቷን ሊያዩ የሚመጡ ብዙ ወንዶች መኖራቸውንም አስረዳች።

በተለይም ምሽት ላይ ጠጥተው የሚመጡና እናቷም ላይ ወሲባዊ ጥቃት የሚያደርሱ ወንዶች ቁጥር ብዙ ናቸው አለች።

አማካሪዋም ስለ እርግዝና መከላከያ መድሃኒት ታውቅ እንደሆነ በጠየቀቻት ጊዜ "አይ እኛ ኮንዶም ነው የምንጠቀመው" የሚል ምላሽ ሰጠች ታዳጊዋ።

ይሄ እንግዲህ በንግግራቸው መካከል ታዳጊዋ ወሲብ ፈፅማ እንደምታውቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር የጠቆመችው።

በህንድ ያለው የህፃናት ወሲባዊ ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, AFP

ከዚህ በኋላ ነበር ስለተሰረቀው ልጅነቷ መናገር የጀመረችው።

"ወንዶች እየመጡ እናቴን ወደ አንዱ መኝታ ክፍል ይወስዷታል። እኔ ይሄንን ያየሁት እንደተለመደ ነገር ነው። አንድ ቀን አባቴ እኔንም አንደኛው መኝታ ክፍል ውስጥ ገፍቶ አስገባኝና ከማላውቀው ሰው ጋር ቆለፈብኝ" ብላለች።

አንዳንድ ጊዜም አባቷ አስገድዶ እርቃኗን ፎቶ ያነሳትና ለደፈሯት ወንዶች ፎቶ ይልክላቸዋል።

የሆነ ወቅት ላይም ታዳጊዋ ለሦስት ወራት ያህል የወር አበባዋ በመዘግቱ ቤተሰቦቿን አስደንግጦ የነበረ ሲሆን፤ ህክምናም ወስደዋት መድኃኒት ታዞላት ነበር።

በዚህ ወቅት አማካሪዋ በተደጋጋሚ የመደፈር ጥቃት እንደደረሰባት መረዳት ቻለች። አማካሪዋም በአፀፋው የህፃናት ደህንነት ኃላፊዎች ጋር ደወለችና ወደ መጠለያ እንደሚወስዷት ለታዳጊዋ ነገረቻት።

ይህ ሁኔታ ታዳጊዋን ብዙ አልረበሻትም። እናቷ በተመሳሳይ ሰዓት ከመምህራን ጋር ውይይት እያደረገች የነበረ ሲሆን ስትወጣም ልጇ ወደ አንድ መኪና ስትገባ አይታ ጩኸቷን አቀለጠችው።

"ልጄን የት ነው የምትወስዷት?" እያለች ነበር።

አማካሪዋም ለእናቲቱ "አንዳንድ የባህርይ ችግሮች ስለተከሰቱባት የምክር አገልግሎት ስለሚያስፈልጋት ነው" የሚል ምላሽ ሰጠች።

"ያለእኔ ፈቃድ ለልጄ የምክር አገልግሎት የምትሰጡት እነማን ናችሁ?" ነበር የእናቲቱ ጥያቄ።

እናቷ እንደዚህ ብትልም ታዳጊዋ ወደ መጠለያ ተወሰደች። ላለፉት ሁለት ያህል ወራትም ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ታዳጊዎች ጋር እየኖረች ነው።

በህንድ በሚያሳፍር መልኩ ቁጥራቸው ትንሽ የማይባሉ ታዳጊ ህፃናት ወሲባዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል። አብዛኛዎቹ ጥቃቶች የሚደርሱት ደግሞ ታዳጊዎቹ በሚያውቋቸው ሰዎች [በዘመዶች፣ በጎረቤቶች፣ በቤተሰብ] እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

ከሁለት ዓመት በፊት የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው ከ10 ሺህ በላይ ህፃናት እንደተደፈሩ ነው። በቅርብ ዓመታትም በህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸውን ነው።

አማካሪዎቹ እንደሚሉት እንደእነዚህ አይነት አሰቃቂ ታሪኮችን መስማት አዲስ ነገር እንዳልሆነ ነው። መጠለያው ውስጥ ካሉ ታዳጊዎች መካከል በአስራ ሁለት እና በአስራ ስድስት ዓመት መካከል ያሉ ሦስት ታዳጊዎች ያሉ ሲሆን ሁሉም የተደፈሩት በአባቶቻቸው ነው።

አንዷ አማካሪ እንደገለፀችውም በአባቷ የተደፈረች ነፍሰጡር የ15 ዓመት ታዳጊን ፈተና እንድትፈተን ወደ አዳራሹ እንዳደረሰቻት ነው።

"ታዳጊዋን ከወለደች በኋላ ልጁን ስጭን ስንላት፤ ለምንድን ነው ልጄን የምሰጣችሁ? የአባቴ ልጅ እኮ ነው። ራሴ አሳድጋለሁ" ማለቷን አማካሪዋ ተናግራለች።

የታዳጊዋ በር

የፎቶው ባለመብት, NEBULA MP

የአስራ ሁለት ዓመቷ ታዳጊ መጠለያ በተወሰደችበት የመጀመሪያ ቀናቶች ውስጥ ሰላማዊ የሆነ እንቅልፍ ሊወስዳት ችሏል። ነገር ግን ከትንሽ ቀናት በኋላ እናቴ ናፈቀችኝ እያለች ግድግዳው ላይ መፃፍ ጀመረች።

እናቷ በበኩሏ የልጇ ታሪክ የውሸት ነው "ከእኛ ጋር በተደጋጋሚ እየተጣላች ስለነበር እኛን ለማስተማር ስትል የፈጠረችው ታሪክ ነው" ብላለች።

እናቷ እንደተናገረችው ባሏ ሥራውን ከማጣቱ በፊት በአንድ ወቅት ጥሩ ይከፈለው እንደነበር ነው።

በአሁኑ ወቅት ባሏ እስር ቤት ሆኖ የፍርድ ሁኔታውን እየተጠባበቀ ሲሆን፤ ልጇም መጠለያ ውስጥ በመገኘቷ ቤቱ ውስጥ ብቻዋን ቀርታለች።

"ለልጄ የማስብ እናት ነኝ፤ እናም ትፈልገኛለች" በማለት የታዳጊዋ እናት ለቢቢሲ ገልፃለች። . ......

በግድድዳው ላይ ትሞነጫችራቸው የነበሩ ስዕሎች በትዝታ እንድኖር አድርጎኛል የምትለው እናት "ሁሌም መሳል፣ መሞነጫጨር ነበር ሥራዋ፤ ያንን ብቻ ነበር የምታደርገው" በማለት እናቷ ትናገራለች።

መኝታ ክፍሏ ውስጥም እናቷን እንደምትወዳት "ይቅርታ እማማ" የሚሉና ሌሎችም ስዕሎች አሉ ተብሏል።