ስኮትላንድ ለዜጎቿ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን በነጻ ልታቀርብ ነው

የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች

ስኮትላንድ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን ለዜጎች በነጻ በማቅረብ የመጀመሪያዋ አገር ልትሆን ነው።

የአገሪቱ የሕዝብ እንደራሴዎች ትናንት ማክሰኞ ዕለት ዜጎች የወር አበባ ንጽህና በነጻ እንዲያገኙ የቀረበውን ሀሳብ ሙሉ በሙሉ ማጽደቃቸው ተገልጿል።

በአዲሱ ሕግ መሠረትም የየአካባቢው ባለስልጣናት ማንኛውም ምርቶችን የሚፈልግ ሰው መነጻ እንዲያገኛቸው የማመቻቸት ግዴታ አለባቸው ተብሏል።

ይህንን ሀሳብ ያቀረቡት የሌበር ፓርቲ ተወካዩዋ ሞኒካ ሌነን ናቸው። የሕዝብ እንደራሴ ሞኒካ ከፈረንጆቹ 2016 ጀምሮ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች እጥረት ላይ ሲሰሩ ቆይተዋል።

''ይህን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ ምንም የሚያግደን ነገር የለም። በተለይ ደግሞ በዚህ የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን እንዲህ በሚያስጨንቅበት ወቅት'' ብለዋል የሕዝብ እንደራሴዋ።

አክለውም '' የወር አበባ በወረርሽኝ ጊዜ የሚቆም ነገር አይደለም። ለወር አበባ የሚሆኑ ምርቶች በቀላሉ ለሰዎች ማቅረብና በድጋሚ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ጥሬ እቃዎችን መጠቀም በጣም ወሳኝ ነው'' ብለዋል።

በስኮትላንድ በተሰራ አንድ ኢመደበኛ ጥናት መሰረት ከ2000 በላይ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችና የኮሌጅ ተማሪዎች በቀረበላቸው ጥያቄ ከአራት ሴቶች መካከል አንዷ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂ ምርቶችን በበቂ ሁኔታ መግዛት አትችልም።

ይህ በንዲህ እንዳለ በዩናይትድ ኪንግደም ከሚገኙ ሴቶች መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት የወር አበባ መገልገያዎችን መግዛት የማይችሉ ሲሆን 15 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በበቂ ሁኔታ መግዛት አይችሉም።

በተጨማሪም 19 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በዋጋው ውድነት ምክንያት ጥራት የሌላቸውን እና ለመጠቀም የማይመቹ መገልገያዎችን ለመግዛት ተገድዋል።

በጥናቱ መሰረት እድሜያቸው ከ14 እስከ 21 ከሆኑ ሴቶች መካከል 71 በመቶ የሚሆኑት የወር አበባ መገልገያዎችን ከመድሀኒት ቤቶችና ሌሎች ቦታዎች ሄደው ለመግዛት ያፍራሉ።

የስኮትላንድ መንግሥት ይህንን ሀሳብ ለመደገፍ 5.2 ሚሊየን ዩሮ የመደበ ሲሆን ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 'ፌርሼር' የተባለው በጎ አድራጎት ድርጅት ደግሞ ለዝቅተኛ ገቢ ቤተሰቦች የወር አበባ መገልገያዎችን በነጻ እንዲያቀርብ ግማሽ ሚሊየን ዩሮ ያገኛል ተብሏል።