ትራምፕ ኤርትራን ጨምሮ በአፍሪካውያን ተጓዦች ላይ አዲስ ገደብ ጣሉ

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ

የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የ15 አፍሪካ አገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ ከመጓዛቸው በፊት ተመላሽ የሚሆን እስከ 15ሺህ ዶላር በቦንድ መልክ ማስያዝ አለባቸው የሚል አዲስ ጊዜያዊ ሕግ አውጥቷል።

ይህ ሕግ ተፈጻሚ መሆን የሚጀምረው ከአንድ ወር በኋላ ሲሆን ለስድስት ተከታታይ ወራት ከዘለቀ በኋላ ውጤታማ ሆኖ የሚገኝ ከሆነ ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል።

ይህ ሕግ ተፈጻሚ የሚሆንባቸው አገራት፤ አንጎላ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ቻድ፣ ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኦፍ ኮንጎ፣ ጂቡቲ፣ ኤርትራ፣ጋምቢያ፣ ጊኒ-ቢሳው፣ ላይቤሪያ፣ ሊቢያ፣ ሞሪታኒያ፣ ሱዳን፣ ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ፣ ኬፕ ቨርዴ እና ቡሩንዲ ናቸው።

አገራቱ የተለዩት ወደ አሜሪካ ካቀኑ ዜጎቻቸው 10 በመቶ እና ከዛ በላይ የሚሆኑት ዜጎቻቸው በተሰጣቸው ቪዛ መሠረት ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ በአሜሪካ በመቆየታቸው ነው ተብሏል።

የእነዚህ አገራት ዜጎች እንደየ ሁኔታው ለጉብኝትም ይሁን በሥራ ጉዳይ ወደ አሜሪካ ከመጓዛቸው በፊት 5ሺህ፣ 10ሺህ ወይም 15ሺህ ዶላር ማስያዝ ይኖርባቸዋል።

ተሰናባቹ ፕሬዝደንት ትራምፕ በዋይት ሃውስ በነበራቸው የአራት ዓመት ቆይታ የኢሚግሬሽን ጉዳዮችን አስተዳደራቸው በትኩረት ሲያስፈጽመው የቆየ ጉዳይ ነው። ተመራጩ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የሪፓብሊካኑን ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በርካታ የኢሚግሬሽን ፖሊሲዎች እንደሚቀይሩ ቃል ገብተዋል።