ዲሞክራቶች ትራምፕን ለመክሰስ ተፍ ተፍ እያሉ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዲሞክራቶች ፕሬዝዳንት ትራምፕ የፖለቲካ ተቀናቃኛቸውን ለማጥፋት ከውጪ ኃይሎች ድጋፍ ጠይቀዋል በሚለው ውንጀላ የተነሳ እንዲጠየቁላቸው ማመልከቻ ለማስገባት እየተንቀሳቀሱ ነው።
የዲሞክራቶችን ቡድን እየመሩ ያሉት ናንሲ ፔሎሲ ፕሬዝዳንቱ " መጠየቅ አለባቸው" ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ውንጀላውን የካዱ ሲሆን " የሌለን ነገር ፍለጋና ርባና ቢስ" ሲሉ አጣጥለውታል።
ፕሬዝዳንቱን የመክሰሱ ሀሳብ ከዲሞክራቶች ጠንካራ ድጋፍ ያገኘ ቢሆንም፣ የመክሰሱ ሃሳብ ቢጸድቅ እንኳን በሪፐብሊካን ጠንካራ ቁጥጥር ስር ያለውን ሴኔት ማለፍ አይቻለውም እየተባለ ነው።
ውንጀላው የተሰማው ፕሬዝዳንቱ ከዩክሬኑ አቻቸው ጋር ያደረጉትን የስልክ ልውውጥ ተከትሎ በቀረበ መረጃ ላይ ነው።
መረጃውን ለዲሞክራቶች ሹክ ያለው ግለሰብ ማንነት ባይገለፅም፣ ትራምፕ ዩክሬን የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንና ልጃቸው ላይ የሙስና ምርመራ እንዲጀምሩ በወታደራዊ እርዳታ አስታከው አስፈራርተዋቸዋል ብለዋል ዲሞክራቶች።
ትራምፕ በዚህ የስልክ ምልልሳቸው ውስጥ ኮንግረስ ለዩክሬን ያፀደቀውን የ250 ሚሊየን ዶላር የወታደራዊ እርዳታ ሳያነሱ አልቀሩም ተብሏል። የትራምፕ አስተዳደር ይህንን እርዳታ እስከ መስከረም አጋማሽ በሚል አዘግይቶት ነበር።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከዩክሬኑ አቻቸው ጋር የጆ ባይደንን ስም አንስተው መወያየታቸውን አልካዱም። ነገር ግን አሉ ፕሬዝዳንቱ አውሮፓ ወታደራዊ እርዳታ ድጋፏን እንድታሻሽል ለመገፋፋት ብቻ ነው ወታደራዊ ድጋፋችንን ላይ እናስብበታለን ያልኩት ብለዋል።
ናንሲ ፒሎሲ ግን ፕሬዝዳንቱ " የሕግ ጥሰት" ፈፅመዋል ሲሉ በመክሰስ " ሕገመንግሥታዊ ግዴታዎቹን የተላለፈ ነው" ሲሉ አክለዋል።
"በዚህ ሳምንት ፕሬዝዳንት ትራምፕ የፖለቲካ ትርፍ የሚያገኙበትን እርምጃ እንዲወስዱ የዩክሬኑ አቻቸውን መጠየቃቸውን አምነዋል" ያሉት ናንሲ " ለዚህም ተጠያቂ መሆን አለባቸው" ሲሉ ተደምጠዋል።
ጆ ባይደን በበኩላቸው ምንም የሠሩት ስህተት እንደሌለ በመናገር ፕሬዝዳንት ትራምፕ በጉዳዩ ላይ ምርመራ እንዲደረግ የማይተባበሩ ከሆነ የይከሰሱልን ጥያቄውን እንደሚደግፉ ተናግረዋል።
ትራምፕን መክሰስ " አሳዛኝ ነው የሚሆነው" ያሉት ባይደን " ነገር ግን ሐዘኑን በራሱ ላይ ያመጣው ነው የሚሆነው" ብለዋል።
ጆ ባይደን በ2020 ምርጫ የትራምፕ ተፎካካሪ ሲሆኑ የዲሞክራቶቹን ጎራ ከፊት እየመሩት ይገኛሉ።
አፈ ጉባኤ ናንሲ ፒሎሲ ደግሞ አንጋፋ የዲሞክራት አባል ናቸው።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትዊተራቸው ላይ ዲሞክራቶች "ሆን ብለው" የተባበሩት መንግሥታት ጎዟቸው ላይ ጥላ ለማጥላት " ሰበር ዜና እና ተልካሻ ወሬ" በማምጣት ለማደናቀፍ እየሞከሩ እንደሆነ ፅፈዋል።
" የስልክ ምልልሱ ቃል በቃል ተጽፎ እንኳ አላዩትም" ያሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ጋር ያደረጉትን የስልክ ቃለምልልስ አንድ በአንድ ተፅፎ ይፋ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።












