ባለፈው አንድ ዓመት ከ1200 ሰዎች በላይ መገደላቸውን ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Attoreny General
ባለፈው 2011 ዓ.ም በመላ የአገሪቱ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች 1229 ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በፌስቡክ ገፁ አስታውቋል።
በግጭቶቹ ተሳትፈዋል የተባሉ 1323 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመስርቶ 645 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየታየ መሆኑንና 667 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች ደግሞ እንዳልተያዙ ፤ የ10 ተጠርጣሪዎች ክስም በምህረት መነሳቱን በኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተደራጁ ድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ፍቃዱ ፀጋ ገለጹ፡፡
አቶ ፍቃዱ እንደገለፁት በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በግጭቶች 1,393 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ሲደርስ በ19 ሰዎች ላይም የግድያ ሙከራ ተደርጓል።
በሌላ በኩል ደግሞ 2,290,490,159.(ሁለት ቢሊየን ሁለት መቶ ዘጠና ሚሊየን አራት መቶ ዘጠና ሺ አንድ መቶ ሃምሳ ዘጠኝ ብር ገደማ) የሚገመት የዜጎች ንብረት የወደመ ሲሆን፤1,200437(አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺ አራት መቶ ሰላሳ ሰባት) ዜጎች ከመኖሪያ ቤታቸውና ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸውን ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።








