የ40 ሺህ ብር ጉቦ አልቀበልም ያለው ዋና ሳጅን ሲራጅ ምን ይላል?

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister
ዋና ሳጅን ሲራጅ አብደላ በአፋር ክልል ዞን አንድ፤ ኤሊዳአር ወረዳ ማንዳ ቀበሌ በፖሊስነት ሙያ ላይ ተሰማርቶ ይሰራል። ሳጅን ሲራጅ በፖሊስነት መሥራት ከጀመረ ገና አንድ ዓመት ተኩል አካባቢ እንደሆነው ይናገራል።
አካባቢው ድንበር በመሆኑ ሕገወጥ የመሣሪያ ዝውውሮችና ኮንትሮባንዶች የሚበዙበት አካባቢ እንደሆነ በቆይታው ተገንዝቧል።
ታዲያ ባለፈው ሐሙስ መስከረም 8 ቀን 2012 ዓ.ም ከምሽቱ አምስት ሰዓት ገደማ አንድ ተሽከርካሪ ባዶውን ለማለፍ ሲሞክር ይመለከታል። በወቅቱ በሥራ ላይ እሱን ጨምሮ አራት የፖሊስ አባላት የነበሩ ቢሆንም በወቅቱ ወደ መንገዱ ያመራው ግን እርሱ ብቻ ነበር።
መንገድ በመዝጋት ተሽከርካሪው እንዲቆም ትዕዛዝ ሰጠ። ትዕዛዝ በተሰጠው መሠረት አሽከርካሪው መኪናውን አቆመ። ምንም የጫነው ነገር አልነበረም። ጋቢና ውስጥ ግን ሹፌሩ፣ ረዳቱና ሌላ ባለቤት እንደሆኑ የተነገረው አንድ ሰው ነበሩ።
በዚህ ሌሊት ምንም ጭነት ሳይዝ ምን ያስጉዛቸዋል? ሲል ሲራጅ ጥርጣሬ ያድርበታል።
"ቦታው ግንባር በመሆኑ ከመከላከያ መኪና በስተቀር ሌሎች መኪናዎች እምብዛም አያልፉም" ሲል በዋናነት ወደ ጥርጣሬ የከተተውን ምክንያት ይናገራል። ከዚህም ባሻገር ቀደም ብሎ ከሕብረተሰቡ ጥቆማ ደርሶት እንደነበርም ያክላል።
ከዚያም ተሽከርካሪውን የእጅ ባትሪ አብርቶ መፈተሽ ይጀምራል። ጥርጣሬው እውነት ሆኖም ከተሽከርካሪው ጎማ በላይ የታሰረ ጆንያ ያያል።
"ይህ ምንድን ነው?" ብሎ ይጠይቃል። ግለሰቦቹ "እኛ የምናውቀው ነገር የለም" የሚል መልስ ቢሰጡትም በፍተሻው 29 ክላሽንኮቭ የጦር መሣሪያ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲያመሩ ትዕዛዝ ይሰጣል።
እነርሱ ግን አንድ መሣሪያና አርባ ሺህ ብር በመስጠት መደራደር ጀመሩ።
ከዚያም አርባ ሺህ ብሩን በመያዝ ከእነመሣሪያቸው በቁጥጥር ሥር ሊያውላቸው ችሏል።
"አርባ ሺህ ብር እና አንድ መሳሪያ ከአገር ደህንነት አይበልጥም" ይላል ምክንያቱንም ሲያስረዳ። ሳጅን ሲራጅ ከዚህ ቀደም በነበረው አጭር የሥራ ልምድ እንዲህ ዓይነት ጉዳይ አጋጥሞት እንደማያውቅ ይናገራል።
ይህ ዜና ከተሰማ በኋላ ግን ዝናው ናኘ። ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድም ይህንን የፖሊስ አባል ጽህፈት ቤታቸው ድረስ ጠርተው የምስጋና የምስክር ወረቀት አበርክትውለታል።
እንኳንስ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ከማንም ሽልማት ይበረከትልኛል ብሎ ያላሰበው ዋና ሳጅን ሲራጅ፤ ሽልማቱ ደስታንና መበረታታትን እንደፈጠረለት ይናገራል።
"ወደፊትም እንደዚህ ዓይነት ሕገ ወጥ ተግባር ብናይ ማለፍ እንደሌለብን በሥልጠናችን ወቅት አስቀድመን ቃል የገባንበት ጉዳይ ነው" ሲል የሙያ ግዴታው እና ኃላፊነቱ የሕዝብንና የአገር ደህንነትን ማስጠበቅ እንደሆነ ያስረዳል።
የክልሉ መንግሥትም ለፖሊስ አባሉ የ50 ሺህ ብር ሽልማት አበርክቶለታል። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንም የዋና ሳጅንነት ማዕረግ እንደሰጠው የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አሊ ቢኒ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
" '40 ሺህ ብር ሊሰጡት ነበር 'እምቢ' ብሎ ነው' ብለን ለክልሉ ፕሬዚደንት ስንነግራቸው፤ ከእነርሱ የበለጠ ነው የምንሸልመው ብለው ነው 50 ሺህ ብር የሸለሙት" ሲሉ የክልሉ ፕሬዚዳንት በወቅቱ የተሰማቸውን ኮሚሽነሩ አስታውሰዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት መሣሪያው በቁጥጥር ሥር የዋለበት ቡሬ ግንባር፤ ድንበር በመሆኑ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የኮንትሮባንድ ንግድና ሕገ ወጥ የመሣሪያ ዝውውር ያጋጥማል።
በዚህም ምክንያት የፖሊስ አባላቶቻቸው ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርጉ ግንዛቤ መስጠት ዝንፍ የማይሉበት ተግባራቸው ነው። በመሆኑም ሲራጅ ከሕብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሠረት በገንዘብ ሳይደለል ሕገወጥ የመሣሪያ አዘዋዋሪዎቹን በቁጥጥር ሥር ማዋል ችሏል ይላሉ።
ለዚህም ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የፖሊስ አባሉ ለሕግ የበላይነት ላበረከተው አስተዋፅኦ የእውቅና የምስክር ወረቀት እና ሜዳሊያ አበርክተውለታል።
የፌደራል ፖሊስም የምስክር ወረቀትና ሞባይል ስልክ ሸልሞታል።
ኮሚሽነሩ አክለውም ዋና ሳጅን ሲራጅ ሲሠራበት የነበረበት ቦታ ላይ ዳግም ድል እንደሚያስመዘግብ ተስፋ እንዳላቸው ነግረውናል።
"የተሽከርካሪውን ሹፌር ባነጋገርኩበት ወቅት፤ 'መኪናው ባዶ በመሆኑ ጠለቅ ያለ ፍተሻ አይደረግብንም' በማለት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሲሰጣቸው እንደቆሙ ነግሮኛል" ሲሉ የማምለጥ ሙከራ እንዳላደረጉ ኮሚሽነሩ ገልፀውልናል። ወዲያው ጥበቃ ላይ የነበሩ ሌሎች ፖሊሶችና የአካባቢው ማኅበረሰብ ትብብር እንዳደረጉለት በመጥቀስ።
ሕገወጥ መሣሪያ በማዘዋወር የተጠረጠሩት ግለሰቦች እና ተሽከርካሪው በአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በእስር ላይ ሆነው ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝም ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።
ከአንድ ወር በፊት፤ አንድ ተሽከርካሪ በዚያው ክልል 'ሰርዶ' የተባለ ኬላ ጥሶ በማለፍ ሎግያ መግቢያ ላይ የጦር መሣሪያና በርካታ ጥይቶችን እንደጫነ መያዙን አስታውሰዋል።
ምንም እንኳን እስካሁን ጉቦ በመቀበል ተጠርጥረው የተያዙ የፖሊስ አባላት ባይኖሩም፤ ሕገ ወጦች የፀጥታ አባላትን በተለያየ መንገድ በማማለል የማይሰሩት ሥራ ስለሌለ ሙስና ይኖራል ብለው ያስባሉ- ኮሚሽነሩ።
ይሁን እንጅ በክልሉ ጉቦ ሲቀበሉ በቁጥጥር ሥር የዋሉ የፖሊስ አባላት አለመኖራቸውን ገልፀውልናል።















