ኢንዶኔዢያውያን ከትዳር በፊት ወሲብ የሚከለክለውን ህግ ተቃወሙ

ተቃዋሚዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ትናንት ማምሻውን የኢንዶኔዢያ ፓርላማ አካባቢ ዜጎች ከትዳር በፊት ወሲብ የሚከለክለውን ህግ በመቃወም ሰልፍ አድርገው ከፖሊስ ጋር ተጋጩ።

ፖሊስ ሰልፈኞቹን ለመቆጣጠር አስለቃሽ ጭስ እና የውሃ ፓምፖችን ተጠቅሟል። በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎችም ረቂቅ ህጉን በመቃወም ዜጎች ቁጣቸውን ሲገልጹ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪ ረቂቅ ህጉ የጽንስ ማቋረጥና ፕሬዝዳንቱን መሳደብን ህግወጥ እንደሆነ አስቀምጧል።

ምንም እንኳን ረቂቅ ህጉ እስካሁን ሙሉ በሙሉ ባይጸድቅም ዜጎች ፓርላማው በሙሉ ድምጽ እንዳይቀበለው ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

ለፓርላማው የቀረበው ረቂቅ ህግ የሚከተሉትን ዋና ዋና ሃሳቦች ይዟል፡

  • ከትዳር በፊት የወሲብ ግንኙነት መፈጸም ወንጀል ሲሆን እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ እስርም ያሰቀጣል
  • ከትዳር በፊት ከፍቅር አጋር ጋር አብሮ መኖር እስከ ስድስት ወር በሚደርስ እስር ያስቀጣል
  • ፕሬዝዳንቱን፣ ምክትል ፕሬዝዳንቱን፣ ሃይማኖት፣ የመንግሥት ድርጅቶችን መሳደብ እና እንደ ባንዲራ ያሉ ሃገራዊ ምልክቶችን ማንቋሸሽ ክልክል ነው
  • ጽንስ ማቋረጥ እስከ አራት ዓመት በሚደርስ እስር የሚያስቀጣ ሲሆን በአስገድዶ መደፈር ወይም ሌላ የህክምና አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ ህጉ ተግባራዊ ይሆናል።

ረቂቅ ህጉ ዛሬ ለፓርላማው ቀርቦ ውሳኔ እንደሚያገኝ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም ፕሬዝዳንት ጆኮ ዊዶዶ ሂደቱ ማካተት ያለበት አንዳንድ ነገሮች አሉ በማለት ወደ አርብ እንዲዘዋወር ማድረጋቸው ታውቋል።

ፖሊስና ተቃዋሚዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ተቃዋሚዎች ከዚህ ባለፈ ረቂቅ ህጉ በሃገሪቱ ተንሰራፍቶ የነበረውን ሙስና ከምንጩ ለማድረቅ ሲሰራ የነበረውን የሙስና አስወጋጅ ኮሚሽን ያዳክመዋል ሲሉ ስጋታቸውን ሲያሰሙ ነበር።

አብዛኛዎቹ ተማሪዎች የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢንዶኔዢያውያን በመላው ኢንዶኔዢያ ዋና ዋና መንገዶች ላይ በመውጣት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

ተቃዋሚዎች ከፖሊስ ጋር የተጋጩት ግን በዋና ከተማዋ ጃካርታ ሲሆን የፓርላማው አፈ ጉባኤ የሆኑት ባምባንግ ሶሳትዮ መጥተው እንዲያነግሩን እንፈልጋለን የሚል መልእክትም አሰምተዋል።

በመቀጠል ሰልፈኞቹ ፖሊስ ላይ ድንጋይ መወርወር መጀመራቸውን ተከትሎ አድማ በታኝ ቡድኖች አስለቃሽ ጭስና ውሃ ፓምፖችን በመጠቀም ተቃዋሚዎቹን ለመበተን ጥረት አድርገዋል።