ጁሊያን አሳንጅ ለአሜሪካ ተላልፎ እንዳይሰጥ ፍርድ ቤት ወሰነ

ጁሊያን አሳንጅ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ጁሊያን አሳንጅ

የመንግሥታትን ምስጢር ሲያጋልጥ የነበረው የዊኪሊክስ መስራች ጁሊያን አሳንጅ ለአሜሪካ ተላልፎ እንዳይሰጥ አንድ የለንደን ፍርድ ቤት ውሳኔ አሳለፈ።

የፍርድ ቤቱ ዳኛ አሳንጅ በጥብቅ ለምትፈልገው አሜሪካ ተላልፎ መሰጠቱን የከለከሉት በግለሰቡ የአእምሮ ጤና ላይ ባላቸው ስጋት የተነሳ መሆኑ ተገልጿል።

የ49 ዓመቱ ጁሊያን አሳንጅ በወንጀለኝነት እየተፈለገ ለመሳደድ የበቃው ከአስር ዓመት በፊት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የመንግሥታትን ጥብቅ የምስጢር ሰነዶች በድረ ገጹ ላይ በማተሙ ነው።

አሜሪካ በአሳንጅ ላይ ባቀረበችው ክስ ግለሰቡ ይፋ ያደረጋቸው ምስጢራዊ ሰነዶች ሕግን የሚጣሱ እንዲሁም የሰዎችን ሕይወት ለአደጋ የሚያጋልጡ በመሆናቸው ነው ብላለች።

የምስጢራዊ መረጃዎች አሹላኪ የሆነው 'ዊኪሊክስ' መስራች ጁሊያን አሳንጅ የቀረቡበትን ክሶች ፖለቲካዊ አላማ ያላቸው ናቸው በማለት ተላልፎ እንዳይሰጥ ተከራክሯል።

አሳንጅ ተላልፎ እንዳይሰጥ የወሰኑት ዳኛ ቫኔሳ ባሬይስትር በውሳኔያቸው ላይ እንዳመለከቱት ግለሰቡ እራስን ለማጥፋት የማሰብና እራሱ ላይ ጉዳት ማድረስን የሚያመለክቱ ማስረጃዎችን ጠቅሰዋል።

"አጠቃላይ ግምገማው የሚያመለክተው መደበትና አንዳንድ ጊዜም ተስፋ መቁረጥ የሚታይበት የወደፊት ሕይወቱ የሚያሰጋው ሰው ነው" ሲሉ ስላለበት ሁኔታ ተናግረዋል።

የአሜሪካ ባለስልጣናት ግን ውድቅ የተደረገባቸው ውሳኔን ለማስቀልበስ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ገልጸዋል።

ጁሊያን አሳንጅ በአሜሪካ ፍርድ ቤት ቀርቦ ጥፋተኛ ከተባለ አስከ 175 ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት ሊበየንበት እንደሚችል ጠበቆቹ የተናገሩ ቢሆንም የአሜሪካ መንግሥት ግን ቅጣቱ ከአራት አስከ ስድስት ዓመት እንደሚሆን አመልክቷል።

አሳንጅ በዊኪሊክስ ድረ ገጽ ላይ የታተሙ ከአፍጋኒስታንና ከኢራቅ ጦርነቶች ጋር የተያያዙ ምስጢራዊ መረጃዎችን ወታደራዊ የመረጃ ቋት ሰብሮ በመግባት ለመውሰድ ከማሴር ጋር በተያያዘ በአሜሪካ መንግሥት በርካታ ክሶች ቀርበውበታል።

አሳንጅ እንደሚለው ይፋ የወጡት መረጃዎች በአሜሪካ ሠራዊት የተፈጸሙ ግፎችን የሚያጋልጡ ናቸው በማለት ይከራከራል።

ነገር ግን የአሜሪካ ዐቃቤ ሕግ ይፋ የወጡት ምስጢራዊ ሰነዶች የሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ በመሆናቸው በአሁኑ ጊዜ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ቤልማርሽ በሚባል እስር ቤት የሚገኘው አሳንጅ ተላልፎ እንዲሰጣት ትፈልጋለች።

አሳንጅ ለእስር የተዳረገው በዋስት ከእስር ውጪ እንዲቆይ የተሰጠውን ዕድል በመተላለፍ ለንደን ውስጥ በሚገኘው ኢኳዶር ኤምባሲ ውስጥ ተደብቆ በመቆየቱ ነው።

አሳንጅ ከ2012 (እአአ) አንስቶ ወደ ኤምባሲው በመግባት ጥገኝነት ጠይቆ ለሰባት ዓመታት የቆ ሲሆን፤ ከኤምባሲው በ2019 ሲወጣ ነው በፖሊስ የተያዘው።

ወደ ኢኳዶር ኤምባሲ ገብቶ ከለላ በጠየቀበት ጊዜ ወሲባዊ ጥቃት ፈጽሟል በሚል ክስ ስዊዲን ግለሰቡ ተላልፎ እንዲሰጣት ጠይቃ ነበር። አሳንጅ ክሱን ያስተባበለ ሲሆን በኋላ ላይ ደግሞ ክሱ ውድቅ ተደርጓል።