የኦብነግ ክንፍን ጨምሮ ሦስት ድርጅቶች "የሶማሊ ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ መወሰን" የተባለ ጥምረት መሠረቱ

የጥምረቱ አመራሮች

የፎቶው ባለመብት, ONLF

የምስሉ መግለጫ, ጥምረቱን የመሠረቱት በአብዱራህማ ማህዲ የሚመራው የኦብነግ ክንፍ እንዲሁም 'ኮንግረስ ፎር ሶማሊ ኮዝ' እና 'ሶማሊ ሪጅናል ዴሞክራቲክ አሊያንስ' የተባሉ ሶማሌ ክልል ላይ ያተኮሩ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ናቸው

በአብዱራህማ ማህዲ የሚመራው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ክንፍ እና በሶማሌ ክልል ላይ ትኩረት ያደረጉ ሌሎች ሁለት ፖለቲካዊ ንቅናቄዎች "የሶማሊ ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥምረት" የተባለ ስብስብ መመሥረታቸውን አስታወቁ።

ጥምረቱን የመሠረቱት የኦብነግ ክንፍ፣ 'ኮንግረስ ፎር ሶማሊ ኮዝ' እና 'ሶማሊ ሪጅናል ዴሞክራቲክ አሊያንስ' ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ "የከንቱ ድርድር ዘመን አብቅቷል" ብለዋል።

ሦስቱ አካላት ጥምረቱን መመሥረታቸውን ያስታወቁት ትናንት ማክሰኞ ጥር 12/2018 ዓ.ም. በኦብነግ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ ባወጡት መግለጫ ነው። አዲሱ ጥምረት፤ የሶማሊ ሕዝብን "ፖለቲካዊ ውክልና" (political agency) ለማጠናከር ያለመ "የተቀናጀ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ሲቪክ መድረክ" እንደሆነ ገልጸዋል።

"የሶማሌ ሕዝብን የጋራ መብቶች፣ ክብር እና ፖለቲካዊ መጻኢ ዕድል" ማሳደግም ሌላኛው የጥምረቱ መቋቋም ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የአሁኑ እና ያለፉት የኢትዮጵያ መንግሥታት በሶማሊ ሕዝብ ላይ የተከተሉት አገዛዝ ሥርዓት "በፖለቲካዊ ማግለል፣ በአሃዳዊ አገዛዝ፣ በሕዝብ ስብጥር ለውጥ፣ በመዋቅራዊ መድልዎ እና በመሠረታዊ መብቶች ላይ በሚፈጸሙ ተከታታይ ጥሰቶች" የታጀበ እንደነበር መግለጫቸው ላይ አስፍረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ ከኦብነግ ጋር የተፈረመው ስምምነትን ጨምሮ "ለእርቅ እና ለፍትሕ ሊሆኑ የሚችሉ መንገዶችን ሁሉ ሞክረን ጨርሰናል" ብለዋል።

መንግሥት "በውይይት ፈንታ አገዛዙ ጭቆናን አባብሷል፣ ብዝበዛን ተቋማዊ አድርጓል፣ እና በሕዝባችን ላይ የኅልውና አደጋ የሚደቅኑ ፖሊሲዎችን ዘርግቷል" በማለት ወንጅለዋል።

"እኛን ለማጥፋት የታለመ የተቀነባበረ ዘመቻ" ተከፍቶብናል ያሉት ሦስቱ የጥምረቱ አባላት፤ ከአሁን በኋላ ጉዳዩን "በዝምታ" ማለፍ እንደማይችሉ አስታውቀዋል። "ያ የትዕግስት ምዕራፍ አሁን ለዘለቄታው አብቅቷል" ሲሉም አክለዋል።

መንግሥት "የሰላም በሮችን ዘግቷል" በማለት የከሰሰው የጥምረቱ መግለጫ፤ "የከንቱ ድርድር ዘመን አብቅቷል" ሲልም የሦስቱን አካላት አቋም ይፋ አድርጓል።

የሶማሊ ሕዝብ "መብታችንን መልሰን ለማግኘት፣ ክብራችንን ለመመለስ እና መጻኢ ዕድላችንን ለማረጋገጥ" ይደረጋል ላሉት "ትግል" አንዲነሳ ጥሪ አቅርበዋል። "ጭቆናን እና አገዛዝን ከሚቃወሙ ሁሉ ጋር በመርኅ ላይ የተመሠረተ አጋርነት" እንደሚመሠርቱም አስታውቀዋል።