ስለጀርባ ሕመም መከላከያ እና ማስታገሻ ሊያውቋቸው የሚገቡ 5 ነጥቦች

የጀርባ አጥንት የሚያሳዩ ፎቶዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images and BBC

በርካታ ሰዎች በሕይወታቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ የጀርባ ሕመም ያጋጥማቸዋል።

እርግጥ ነው ሕመሙ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ሊጠፋ ይችላል። ነገር ግን ተመልሶ ሲመጣ ስቃይ ደርቦ ነው። ይህ ደግሞ የዕለተ ዕለት ኑሯችንን ያከብድብናል።

የጀርባ አጥንታችን ከጎናችን እና ከዳሌ አጥንታችን ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም። ከተለያዩ ስሮች፣ ከመገጣጠሚያዎች እና ስስ ሥጋዎች ጋር የተገናኘ በመሆኑ ከእነዚህ ክፍሎች አንዱ ሲጎዳ ጀርባችንን ሊያመን ይችላል።

በተለያዩ ምክንያቶች በዓለም ዙሪያ ከልጅ እስከ አዋቂ እያሰቃየ ያለውን የጀርባ ሕመም ለመከላከል እና ለማስታገስ ልናውቃቸው የሚገቡ አምስት መንገዶች እነሆ፡

የጀርባ አጥንት ከጭቅንላታችን ጀምሮ እስከ መቀመጫችን የሚወርድ ነው
የምስሉ መግለጫ, የጀርባ አጥንት ከጭቅንላታችን ጀምሮ እስከ መቀመጫችን የሚወርድ ነው

የታችኛው ወይስ የላይኛው?

ግሎባል በርደን ኦፍ ዲዚዝ የተሰኘው ተቋም ያሠራው ጥናት እንደሚያሳየው በታችኛው የወገብ ሕመም የሚሰቃዩ ሰዎች ቁጥር እስከ አውሮፓውያኑ 2050 ባለው ጊዜ ሦስት እጥፍ ይጨምራል።

ይህ የአሜሪካው ዋሺንግተን ዩኒቨርሲቲ እና ኢንስቲትዩት ፎር ሄልዝ ሜትሪክስ ኤንድ ኢቫሉዌሽን የተባለው ተቋም በጋራ የሠሩት ጥናት ነው።

ማለትም በ2050 ከ10 ሰዎች አንዱ የታችኛው ጀርባ ሕመም ተጠቂ ይሆናሉ ማለት ነው።

በጥናቱ መሠረት ከስትሮክ፣ ከልብ ሕመም፣ ከስኳር ሕመም እና ጨቅላዎችን ከሚያጠቁ በሽታዎች ቀጥሎ የጀርባ ሕመም ዓለም አቀፋዊ ጤና ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው።

የታችኛው ጀርባ ሕመም ከፍተኛ ስቃይ የሚያስከትለው አብዛኛውን የሰውነታችንን ክፍል ስለሚሸከም ነው።

ነገር ግን የላኛው ጀርባ ሕመም የሚባለውና አንገት እና ትከሻን የሚያጠቃው ሕመምም ስቃዩ ቀላል አይደለም።

ሕፃናት ሲጫወቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሕፃናት የጀርባ አጥንታቸው ከሌሎች አጥንቶች ፈጥኖ የሚያድግ ከሆነ ሊያማቸው ይችላል

ከመታከም በፊት መመርመር

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከመታከም በፊት መመርመር የሚለው የሕክምና ሐሳብ በተለይ ለጀርባ ሕመም ወሳኝ ነው። ምክንያቱም የጀርባ ሕመም ምክንያቶች የተለያዩ ስለሆኑ የምርመራ ውጤታቸውም ያላሰብነው ሊሆን ይችላል።

ዶክተሮች ብዙውን ጊዜ የጀርባ ሕመም እንደ ኩላሊት አሊያም ካንሰር ለሕይወት የሚያሰጋ አይደለም ይላሉ። ምርመራው ደግሞ አካላዊ ሁኔታ እና የታካሚውን የሕክምና ታሪክ የሚያጠና ነው።

የደም ምርመራ ውጤቶች ካንሰር አሊያም እብጠት ሊገኝባቸው ይችላል። እኒዚህ ስስ የሆነውን የሥጋ ክፍል (ካርቲሌጅ) የሚጎዱና አርትራይተስ (የመገጣጠሚያ በሽታ) የሚያስከትሉ ናቸው።

እንደ ራጅኤ፣ ሲቲ ስካን፣ አልትራሳውንድ እና ኤምአርአይ ያሉ ምርመራዎች ደግሞ መገጣጠሚያዎችን፣ አጥንቶችን፣ ወሳኝ የሰውነት ክፍሎችን እና ሕብረ ህዋሳት የሚባሉት ክፍሎችን ይዳስሳሉ።

ጡንቻችን ላይ አደጋ ሲከሰት ከባድ የሆነ የጀርባ ሕመም ሊያስከትል እና መቀመጫችን እና እግሮቻችን አካባቢ ከፍተኛ ስቃይ ሊያመጣ ይችላል። ይህ ምናልባትም የነርቭ ችግር እንዳለ ሊጠቁመን ይችላል።

በጡንቻችን ላይ ያለውን ኤሌክትሪካዊ እንቅስቃሴ የሚመረምረው ኤሌክትሮዳያግኖሲስ የጡንቻ ወይስ የነርቭ ችግር የሚለውን መለየት ያስችላል።

ይህ ምርመራ ለአዋቂዎችም ሆነ ለሕፃናት የሚሠራ ነው።

ዶ/ር አሪማ ዲሱዛ የጀርባ አጥንት ቀዶ ሕክማና አማካሪ ናቸው። በሕንድ እና በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የሕፃናት ሐኪም ሆነው ሠርተዋል። አሁን ደግሞ በጀርመን እያገለገሉ ይገኛሉ።

ወላጆች ልጆቻቸውን ይዘው ሲመጡ "ልጆች ሁሌም እንደቦረቁ ነው። ስሊዚህ ሲጫወቱ ተጎድተው ይሆን? የተደበቀ የአጥንት ችግር ይኖር ይሆን? ወላጆቻቸውስ የጀርባ ሕመም ችግር አለባቸው? የሚመገቡት ምግብ የተመጣጠነ ነው? የሚለውን እመለከታለሁ" ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

"ሕፃናት ላይ የጀርባ ሕመም የሚከሰተው የጀርባ አጥንታቸው ከሌሎች የሰውነታቸው አጥንት በተለየ በፍጥነት ስለሚያድግ ነው" ይላሉ።

ጤናማ አእምሮ፤ ጤናማ ሰውነት

ባለሙያዎች እንደሚሉት አንዳንድ ሰዎች የጀርባ ሕመማቸው ቶሎ የማይድነው ተመልሶ ይመጣል የሚል ፍራቻ ስላለባቸው ነው።

"ድጋሚ እንታመማለን በሚል ስጋት ምንም የጀርባ አጥንት እና የጡንቻ ሕመም ሳይኖርባቸው ጀርባቸውን ማሠራት ያቆማሉ" የሚሉት በዩኬ የሚገኘው ዳውን2ዩ የጤና ተቋም ኃላፊ የሆኑት አዳም ሱ ናቸው።

"ፍራቻው እንቅስቃሴ እንዲቀንሱ ያደርጋቸዋል። አንዳንዶች ዘና የሚሉባቸውን እንቅስቃሴዎች ሁላ ማድረግ ያቆማሉ።"

በአውስትራሊያው ማኳሪ ዩኒቨርሲቲ የፊዚዮቴራፒ ፕሮፌሰር የሆኑት ማርክ ሀንኮክ "አንዳንድ ሰዎች ጀርባቸውን እንዳይጎዱት በማሰብ ከማኅበራዊ ሕይወት ራሳቸውን ያገላሉ" ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

በዚህ ምክንያት አሁን ዓለም ላይ ያለው መመሪያ "አካላዊ፣ ሥነ-ልቡናዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮችን" ከግምት ያስገባ እንደሆነ ይናገራሉ።

የፊት አጥንት

የፎቶው ባለመብት, Adam Siu

እረፍት ወይስ እንቅስቃሴ?

የጀርባ ሕመማቸው እንዳይገረሽባቸው የሚሰጉ ሰዎች እረፍት ማድረግ ጠቃሚ ነው ብለው ያስባሉ።

ነገር ግን እንደ ብሪታኒያው የጀርባ አጥንት ቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ከሆነ እንቅስቃሴ ማድረግ ለጀርባ ሕመም ማስታገሻ ነው። ባለፉት 10 ዓመታት የተሠሩ ጥናቶችም እረፍት ማድረግ ሕመሙ ቶሎ እንዳይሻለን ሊያደርግ እንደሚችል ይጠቁማሉ።

". . . የጀርባ አጥንት መስመሮች የሰውነትን ክብደት እና እንቅስቃሴ የመሸከም አቅም አላቸው። ይህን ተፈጥሯዊ ይዘት ላለማወክ ለረዥም ጊዜ መቀመጥ፣ ማጎንበስ አሊያም መቆም አይመከረም" ይላሉ ሱ።

ቢሆንም የዘመናዊው ዓለም ዘይቤዎች ማለትም የቢሮ ሥራ፣ ጌም መጫወት፣ ማንበብ እና ስልክ መነካካት የሰውነታችንን እንቅስቃሴ እየገደቡት ነው።

የቢሮ ሥራ ያላቸው በየመሐሉ እንቀስቃሴ እንዲያደርጉ ለምሳሌ ደረጃ እንዲወጡ እንዲወርዱ ይመከራል።

"የጭነት መኪና አሽከርካሪ ከሆኑ የትራፊክ መጨናነቅ ሲኖር ሰውነትዎን ማፍታታት አለብዎ" ይላሉ።

"የግንባታ ሥራ የሚሠሩ ሰዎች ከባድ ዕቃ መሸከም ስለሚኖርባቸው አደጋን ለመከላከል መመሪያውን መከተል እና የፊዚዮቴራፒ ባለሙያ ማማከር ይጠበቅባቸዋል።"

እርጉዝ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እርጉዝ ሴቶች ለጀርባ ሕመም የተጋለጡ ናቸው

እርግዝና በተለይ ደግሞ በመጀመሪያዎቹ ወራት የጀርባ ሕመም ከሚያስከትሉ ጉዳዮች አንዱ ነው።

ይህ የሚሆነው እርጉዝ ሴቶች ሰውነታቸው ለወሊድ ራሱን ሲያመቻች ራሱን ስለሚያፍታት ነው። በዚህ ምክንያት የጀርባ አጥንት እና ሌሎች ኅብረ ህዋሳት ሊፍታተቱ ይችላሉ።

እርጉዞች በሚዞሩበት ጊዜ እግራቸውን እንዲያንቀሳቅሱ ይመከራል። ይህን ማድረግ የጀርባ አጥንት እንዳይጣመም ያግዛል።

አልፎም የሰውነትን ክብደት መሸከም የሚችል ጫማ መጫማት እና ለእርጉዝ ሴቶች የተዘጋጁ ትራሶች እና ፍራሾች መጠቀም ያስፈልጋል።

ማስታገሻ መድኃኒት መውሰድ

ሱ "የጀርባ ሕመም ሲጀማምር እብጠትን የሚከላከሉ በየትኛውም ፋርማሲ ሊገኙ የሚችሉ ማስታገሻዎችን መውሰድ ችግር የለውም" ይላሉ።

"ነገር ግን ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ሁኔታዎች የማይሻሻሉ ከሆነ ችግሩን እያባሱት ነው የሚሄዱት። በሚያሳዝን ሁኔታ ለዓመታት ማስታገሻ የወሰዱ ታካሚዎች አጋጥመውኝ ያውቃሉ።"

አንዳንዶች ማስታገሻ መውሰድ የጀርባ ሕመም በምን ምክንያት እንደተከሰተ እንዳናውቅ ያደርገናል ቢሉም የብሪታኒያው ማኅበር በዚህ አይስማማም።

"ሰውነታችን በጣም ኃይለኛ የሚባል መከላከያ አለው። ማስታገሻ መድኃኒቶች ይህን ማስወገድ አይችሉም። ዋናው ነገር ስለምንወስደው መድኃኒት ሐኪሞችን ማማከር ነው።"