ሰባት ተጨማሪ አገራት የትራምፕን 'የሰላም ቦርድ' እንደሚቀላቀሉ አስታወቁ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሳዑዲ አረቢያ፣ ቱርክ እና ግብፅን ጨምሮ ሰባት ተጨማሪ አገራት የትራምፕን 'የሰላም ቦርድ' እንደሚቀላቀሉ አስታወቁ።
አገራቱ በጋራ ባወጡት መግለጫ ቦርዱን ለመቀላቀል መወሰናቸውን ገልጸዋል። እስራኤልም ቦርዱን እንደምትቀላቀል አስታውቃለች።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዳሉት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቱን ቦርዱን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በሌላ በኩል በቦርዱ ውስጥ አንድም ፍልስጤማዊ አለመኖሩ እና ቋሚ የቦርዱ አባል ለመሆን 1 ቢሊዮን ዶላር መክፈል ያስፈልጋል መባሉ ጥያቄ አጭሯል። በቦርዱ ውስጥ የመንግሥታቱ ድርጅት ያለው ሚናም አነጋጋሪ ሆኗል።
ሳዑዲ አረቢያ እንዳለችው ቱርክ፣ ግብፅ፣ ዮርዳኖስ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ፓኪስታን እና ኳታር የተካተቱበት እና አብላጫው አባላቱ ሙስሊም አገራት የሆኑበት ቡድን በጋዛ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንዲጸና እንዲሁም ጋዛን መልሶ ለመገንባት ቦርዱ እንደሚረዳም ገልጻለች።
የዓለም የምጣኔ ሃብት ፎረም ስዊትዘርላንድ ሲካሄድ፤ ትራምፕ እንደተናገሩት ፑቲን ቦርዱን እንዲቀላቀሉ የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለዋል። ፑቲን ግን ገና ጥሪውን እያጤኑት እንደሆነ ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ምን ያህል አገራት ቦርዱን እንደተቀላቁ ይፋ አልተደረገም። ካናዳ እና ዩናይትድ ኪንግደም ምላሻቸውን አላሳወቁም፥
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ባሕሬን፣ አልቤንያ፣ አርሜንያ፣ አዘርባጃን፣ ቤላሩስ፣ ሃንጋሪ፣ ካዛኪስታን፣ ሞሮኮ እና ቬትናም ቦርዱን ተቀላቅለዋል።
'የሰላም ቦርድ' ዋና ሥራ አስፈጻሚ አባላት ሆነው ከተካተቱ መካከል የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ይገኙበታል።
የአሜሪካ ባለሥልጣን ለቢቢሲ አጋር ሲቢኤስ እንደተናገሩት፤ ቦርዱን ለመቀላቀል የተቀመጠ ምንም ቅድመ ሁኔታ የለም።
ሆኖም ከሦስት ዓመት በላይ ለሚዘልቅ ጊዜ የጋዛ ሰላም ቦርድ ቋሚ አባል መሆን የሚፈልጉ አካላት 1 ቢሊዮን ዶላር መክፈል አለባቸው።
ገንዘቡ ጋዛን መልሶ ለመገንባት እንደሚውል ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።
የቦርዱ የዕድሜ ዘመን መሪ ትራምፕ ይሆናሉ። ከፕሬዝዳንትነት ቢለቁም ቦርዱን መምራት ይቀጥላሉ።
ቦርዱ ከጋዛ ባሻገር በሌሎችም አካባቢዎች ያሉ ግጭቶችን ለመፍታት እንደሚሠራ ሮይተርስ የዜና ወኪል የተመለከተው የቦርዱ ረቂቅ ሰነድ ይጠቁማል።
የቫቲካን ጳጳስ ሊዮ የቦርዱ አባል እንዲሆኑ ተጠይቀዋል።
የስሎቬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦርዱ ከዓለም አቀፍ አሠራር ጋር ይጣረሳል በሚል የቀረበላቸውን ጥሪ ውድቅ አድርገዋል።
ከሰላም ቦርዱ በተጨማሪ ሁለት ከፍተኛ ቦርዶችም ይፋ ተደርገዋል። አንደኛው 'ፋውንዲንግ ኤክስኪውቲቭ ቦርድ' የሚባል ሲሆን፤ ኢንቨስትመንት እና ዲፕሎማሲ ላይ ያተኩራል።
ሁለተኛው ደግሞ 'ጋዛ ኤክስኪውቲቭ ቦርድ' ይባላል። ጋዛን የማስተዳደር ሁኔታን የሚተካተል ሲሆን በሽግግር አስተዳደር ሥር በጋዛ መልሶ ግንባታ ላይ የሚሳተፍ ነው።
ዋይት ሐውስ እንዳለው፤ በዚህ ቦርድ ውስጥ እንዲሠሩ የተመረጡ አባላት "ለጋዛ ሕዝብ ሰላም፣ መረጋጋት እና ብልፅግና ለማስፈን ውጤታማ አስተዳደር እና አገልግሎት የማቅረብ" ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።
'ፋውንዲንግ ኤክስኪውቲቭ ቦርድ' በትራምፕ ይመራል። በጋዛ መልሶ ግንባታ ዋነኛ ተሳትፎ የሚኖረው ሲሆን፤ ዋይት ሐውስ እንዳለው አባላቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ማርኮ ሩቢዮ፣ የአሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የትራምፕ ልጅ ባል ጄራርድ ኩሽነር ናቸው።















