ትራምፕ በግሪንላንድ ጉዳይ "ወደፊት ስምምነት" እንደሚደረስ አስታውቀው አውሮፓውያን ላይ የጣሉትን ታሪፍ አነሱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በግሪንላንድ ጉዳይ ስምምነት በሚደረስበት ጉዳይ ላይ ከኔቶ አባላት ጋር ማውራታቸውን እና የአውሮፓ ሀገራት ላይ የጣሉትን ታሪፍ ማንሳታቸውን አስታወቁ።
ትራምፕ በማኅበራዊ ሚድያ ገፃቸው እሳቸው እና ኔቶ "በጣም ገንቢ" ያሉት ውይይት ማድረጋቸውን ቢያስታውቁም ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ላለፉት ጥቂት ሳምንት የኔቶ ጥምረት ላይ ትችት ሲያሰሙ የቆዩት ትራምፕ ውይይቱ ወደፊት ስምምነት የሚደረስበት "ማዕቀፍ" ላይ እንዳደረሳቸው ገልፀዋል።
የአሜሪካው መሪ በዓለም ምጣኔ ሀብት ፎረም ላይ ባሰሙት ንግግር ግሪንላንድን "መቆጣጠር" አማራጭ የሌለው ነገር መሆኑን ጠቁመው ወታደራዊ ኃይል እንደማይጠቀሙ ቃል ገብተው ነበር።
የአውሮፓ ሀገራት የደረሱት ስምምነት ግሪንላንድን የአሜሪካ ንብረት በማድረግ ጉዳይ ላይ በምን እንደተስማማ የሚታወቅ ነገር የለም።
በትሩዝ ሶሻል ገፃቸው ረቡዕ መልዕክታቸውን ያሰፈሩት ትራምፕ "በግሪንላንድ እና በአርክቲክ ቀጣና ጉዳይ ወደፊት ከስምምነት የምንደርስበትን ማዕቀፍ አዘጋጅተናል" ብለዋል።
"ይህ ስምምነት ተፈፃሚ ከሆነ ለዩናይትድ ስቴትስ እና ለኔቶ ሀገራት ታላቅ ነገር ይሆናል።"
በዩኤስ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ከምንጮቹ እንደሰማው አሜሪካ የዴንማርክ ክፍል የሆነችውን ራስ ገዝ ደሴት ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠሯ ጉዳይ ከስምምነት አልተደረሰም።
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና ልዩ መልዕክተኛው ስቲቭ ዊትኮፍ "ለኔ ቀጥታ ሪፖርት" ያደርጋሉ ሲሉ ፕሬዝደንቱ ድርድሩ እንደቀጠለ ጠቁመዋል።
የዴንማርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላርስ ሎክ ራስመሰን በለቀቁት መግለጫ "አሁን ረጋ ብለን በአርክቲክ የአሜሪካን ስጋት እንዴት መቀነስ እንደምንችል እናውራ። ነገር ግን የዴንማርክ አገዛዝን ቀይ መስመር ማክበር አለብን" ብለዋል።
በስዊዝ አልፓይን ሪዞርት ከኔቶ ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩተ ጋር የመከሩት ትራምፕ ወደፊት የሚደረሰው ስምምነት የማዕድን መብትን ሊያካትት እንደሚችል ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ግሪንላንድ ስትራቴጂካዊ ስፍራ ከመሆኗም ባለፈ የአሜሪካው ፕሬዝደንት በተደጋጋሚ የደሴቷን ያልተነኩ ማዕድናት ጉዳይ ሲያነሱ ይሰማል። ግሪንላንድ ያሏት ብርቅየ የሚባሉ ማዕድናት ተንቀሳቃሽ ስልክን ጨምሮ ሌሎች የኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች ለመሥራት ይጠቅማል።
የኔቶ ዋና ፀሐፊ ዴንማርክ በግሪንላንድ ላይ ስላላት ሉዓላዊነት ከትራምፕ ጋር አለመወያየታቸውን ለአሜሪካው ፎክስ ኒውስ ተናግረዋል።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ኃይል ወደፊት ግሪንላንድ ውስጥ አንድ ወታደራዊ ጣቢያ ሊገነባ ይችላል ሲሉ ዘግበዋል።
ትራምፕ፤ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ዴንማርክ እና ፈረንሳይን ጨምሮ 7 የአውሮፓ ሀገራት ላይ ከአውሮፓውያኑ የካቲት 1 ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የ25 በመቶ ታሪፍ ጥለው ነበር።
ነገር ግን ትራምፕ ከኔቶ ፕሬዝደንት ጋር ከመከሩ በኋላ የንግድ ጦርነቱን ለማስቆም ወስነዋል።
"በተደረሰው መግባባት መሠረት ከየካቲት 1 ጀምሮ ተፈፃሚ ይሆናል ያልኩትን ታሪፍ ለማንሳት ወስኛለሁ" ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ገፃቸው ለጥፈዋል።















