ሰሜን ኮርያ፡ ፕሬዝዳንት ኪም የአገራቸው ምጣኔ ሀብት እቅድ አለመሳካቱን ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሰሜን ኮርያ ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን የአገራቸው የአምስት ዓመት የምጣኔ ሀብት እቅድ "በሁሉም ዘርፎች ሊባል በሚችለ ሁኔታ" የተቀመጠለትን ግብ አለማሳካቱን ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን የያሉት በፓርቲያቸው ጉባኤ መክፈቻ ላይ ነው።
የሰሜን ኮርያ የሠራተኞች ፓርቲ ስብሰባ ሲያደርግ ይህ ስምንተኛው ብቻ ነው ተብሏል።
ሰሜን ኮርያ ካለፈው ዓመት ታኅሣስ ወር ጀምሮ ምንም እንኳ አንድም በቫይረሱ የተያዘ ሰው የለም ብትልም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በሚል ድንበሯን ዘግታለች።
ይህም ከጎረቤቷና አጋሯ ቻይና ጋር ተቆራርጣ እንድትቀር አድርጓታል።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ 80 በመቶ መውደቁ ተገልጿል።
በሰሜን ኮርያ አውሎ ንፋስ እና ጎርፍ ቤቶችን ያወደመ ሲሆን በኒውክለር ፕሮግራሟ የተነሳም ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥብቅ የሆነ ማዕቀብ ተጥሎባታል።
ፕሬዝዳንት ኪም የሚሰሯቸውን ስህተቶች ሲያምኑ የመጀመሪያቸው አይደለም።
በቴሌቪዥን በተላለፈው የፓርቲው ጉባኤ ላይ አዳራሹ በተሰብሳቢዎች ሞልቶ የታየ ሲሆን አንዳቸውም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አላደረጉም።
ፕሬዝዳንቱ ወደ ስብሰባ አዳራሽ ሲገቡ ሁሉም ከመቀመጫቸው ተነስተው በጭብጨባ ተቀብለዋቸዋል።
ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው በ2016 ያስተዋወቁት የአምስት ዓመት የምጣኔ ሀብት ስትራቴጂ "በሁሉም ዘርፍ ሊባል በሚችል ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ ዝቅተኛ አፈጻጸም አስመዝግቧል "ስህተቶችን ደግሞ በይፋ መቀበል ያስፈልጋል" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ የፓርቲያቸው አባላትን የኮሮናቫይረስን በመከላከል ረገድ ላሳዩት ቁርጠኝነት አመስግነዋል።
ሰሜን ኮርያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በኮሮናቫይረስ መጠርጠራቸውን ለዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ሪፖርት ብታደርግም አንድም ሰው በቫይረሱ ተይዟል ብላ ሪፖርት አላደረገችም።
ፕሬዝዳንት ኪም ለምክር ቤቱ አባላት አዲስ የአምስት ዓመት የምጣኔ ሀብት እቅድ ያስተዋውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።












