ትራምፕ ስምንት የቻይና መተግበሪያዎች ላይ እገዳ ጣሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከስምንት የቻይና መተግበሪያዎች [አፕ] ጋር ግብይት እንዳይካሄድ የሚያግድ ትዕዛዝ ፈረሙ።
ከመተግበሪያዎቹ መካከል ታዋቂ የክፍያ ዘዴዎች የሆኑት አሊፔይ፣ ኪውኪው ዋሌት እና ዊቻት ፔይን ይገኙበታል።
በ45 ቀናት ውስጥ ተግባራዊ የሚሆነው ውሳኔ መተግበሪያዎቹ ለአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ስጋት በመሆናቸው ታግደዋል ተብሏል።
መተግበሪያዎቹ የአሜሪካ ፌዴራል ሠራተኞች መረጃን ለመከታተል እያገለገሉ ሳይሆን አይቀርም የሚል ፍንጭ ሰጥቷል።
ውሳኔው ቴንሴንት፣ ኪውኪው፣ ካምስካነር፣ ሼርኢት፣ ቨሜት እና ደብሊውፒኤስን የሚያካትት ሲሆን ትራምፕ ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ የሚተገበር ነው ተብሏል።
የፕሬዝዳንቱ እርምጃ "ከቻይና ጋር ግንኙነት ያላቸውን የሶፍትዌር መተግበሪያዎች በሚያዘጋጁ ወይም በሚቆጣጠሩት ላይ አሜሪካ እርምጃ መውሰድ አለባት" ይላል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በዚህ ውሳኔያቸው ላይ "ከቻይና ጋር የተገናኙ የሶፍትዌር መተግበሪያዎች እንደ ስማርት ስልኮች፣ ታብሌቶች እና ኮምፒውተሮች ያሉ የግል የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን በማግኘት ግላዊ የሆኑትን ጨምሮ ሰፋ ያሉ መረጃዎችን ከተጠቃሚዎች ማግኘት እና መያዝ ይችላሉ" ብለዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ከመጨረሻዎቹ የስልጣን ወራቶቹ ጀምሮ የብሔራዊ ደኅንነት አደጋ ናቸው የሚሏቸውን ጨምሮ በቻይና ኩባንያዎች ላይ ጫናዎችን እያደረጉ ነው።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለቻይና መንግሥት መረጃዎችን ያጋራሉ በሚል በበርካታ የቻይና ኩባንያዎች ላይ እገዳዎችን ጥለዋል።
የዋሽንግተን ቅጣት ከደረሰባቸው መካከል የቻይና ማኅበራዊ ሚዲያ መተግበሪያው ቲክቶክ እና ግዙፉ የቴሌኮም ተቋም ሁዋዌ ተጠቃሽ ናቸው።
ቻይና እነዚህ ድርጅቶች መረጃዎቻቸውን ለቻይና መንግሥት ያካፍላሉ የሚሉ ቅሬታዎችን በተከታታይ ውድቅ ስታደርግ የቆች ሲሆን፤ የወታደራዊ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ውጭ መላክ የሚገድቡ የራሷን ሕጎች በማውጣት ምላሽ ሰጥታለች።












