ዶናልድ ትራምፕ፡ቲክ ቶክ በአሜሪካ አገልግሎቱን እንዲቀጥል ለማስቻል የቀረበው ስምምነት ምን ይላል?

የፎቶው ባለመብት, EPA
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለቤትነቱ የቻይና የሆነው የተንቀሳቃሽ ምስል መጋሪያ መተግበሪያ [አፕሊኬሽን] በአሜሪካ አገልግሎቱን መስጠት እንዲቀጥል የሚፈቅደውን ስምምነት ማፅደቃቸውን አስታወቁ።
ትራምፕ የቻይናው ቲክ ቶክና የአሜሪካ ድርጅቶች ኦራክልና ወልማርት በጋራ ለመስራት እንዲስማሙ መፍቀዳቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ፕሬዚደንቱ መተግበሪያው የብሔራዊ ደህንነት አደጋ ላይ ይጥላል በማለት ከአሜሪካ እንዲታገድ ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር።
የአሜሪካ የደህንነት ባለሥልጣናትም የቲክ ቶክ ባለቤት በመተግበሪያው አማካኝነት ከተጠቃሚዎች የሰበሰበው መረጃ ለቻይና መንግሥት ተሰጥቶ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።
የቻይና የቴክኖሎጂ ኩባንያውና የቲክ ቶክ ባለቤት ብቴዳንስ ግን፤ በቻይና ገዥው የኮሚኒስት ፓርቲ ቁጥጥር ሥር ነው ያለው ወይም መረጃዎችን አሳልፎ ይሰጣል በሚል የቀበረበበትን ክስ ተቃውሟል።
ቅዳሜ እለት ትራምፕ አዲሱ ስምምነት የ100 ሚሊዮን አሜሪካዊያንን መረጃ ደህንነቱ መጠበቁን ያረጋግጣል ሲሉ ተናግረዋል። ደህንነቱም መቶ በመቶ አስተማማኝ ይሆናል ብለዋል ትራምፕ።
በሰሜን ካሮላይና የምርጫ ሰልፍ ቀደም ብሎ ዋይት ሃውስን ለቀው ሲወጡ "ስምምነቱን ባርኬዋለሁ" ካሉ በኋላ ስምምነቱን ያፀደቁት በሃሳብ ደረጃ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ቢቴዳንስ ግን አዲስ በቀረበውና ከቻይና መንግሥት ተጨማሪ ይሁንታ በሚያስፈልገው የቲክ ቶክ ስምምነት ላይ ያለው ነገር የለም ።
ፕሬዚደንት ትራምፕ በጋራ የመስራቱን ሃሳብ የደገፉት አስተዳደራቸው በአገሪቷ ያሉ ሕዝቦች ቲክ ቶክን ከየትኛውም 'አፕስቶር' እንዳያወርዱ ከእሁድ ጀምሮ ሊያግድ እንደሚችል ካሳወቀ ከቀናት በኋላ ነው።
ሆኖም የአሜሪካው የንግድ መሥሪያ ቤት "በቅርቡ አዎንታዊ ሂደቶች በመታየታቸው" ትዕዛዙን ለማስፈፀም አርብ ዕለት ሰጥቶት የነበረውን የ48 ሰዓታት የጊዜ ገደብ በአንድ ሳምንት ማራዘሙን አስታውቋል።
በቲክ ቶክ ላይ የተፈጠረው አለመግባባት የተከሰተው በትራምፕ አስተዳደርና በቻይና መንግሥት መካከል በንግድ፣ በሆንግ ኮንግ ተቃውሞ እና ቤጂንግ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን የተቆጣጠረችበትን መንገድ ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ሳቢያ ከፍተኛ ውጥረት ከተከሰተ በኋላ ነው።
የቀረበው ረቂቅ ስምምነት ምንድን ነው?
የቀረበው ስምምነት 'ዳብድ ቲክ ቶክ ግሎባል' የተባለ አዲስ ኩባንያ እንዲቋቋም እንደሚያመላክት ሮይተርስ የዜና ወኪል ሐሙስ ዕለት በዘገበው አስታውቋል።
ይህ ኩባንያ በአብዛኛው አሜሪካዊያን ዳሬክተሮች ይኖሩታልም ተብሏል። ፕሬዚደንቱና የደህንነት ባለሙያም የቦርድ አባል ይሆናሉ ይላል።
የአሜሪካ ኩባንያዎቹ ኦራክልና ወልማርትም በኩባንያው ውስጥ ወሳኝ ድርሻ እንደሚኖራቸው የሚጠበቅ ሲሆን የቻይና ኩባንያው ቢቴዳንስም የአሜሪካ ተጠቃሚዎችን መረጃን ለመጠበቅ ተስማምቷል።
የቲክ ቶክ መረጃዎችም በኦራክል ቋት የሚከማቹ ሲሆን ይህም የመረጃ ምንጭ ኮዱን የመመርመር መብት ይኖረዋል ተብሏል።
ፕሬዚደንት ትራምፕ አዲሱን የቲክ ቶክ ኩባንያ ኦራክልና ወልማርት ሙሉ በሙሉ እንደሚቆጣጠሩት ተናግረዋል።
አዲሱ ስምምነት በአገሪቷ ተጨማሪ የሥራ እድል እንደሚፈጥርና ገቢ እንደሚያስገኝም ፕሬዚደንቱ አክለዋል።












