ጃፓን ፡ ደብዛዎን ማጥፋት ፈልገዋል? ለምን ጃፓን አይሄዱም? የደብዛ ማጥፋት አገልግሎት ያገኛሉ

የማይታይ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Alamy

አንዳንድ ጊዜ "ጥፉ ጥፉ" አይላችሁም? በቃ መትነን አያምራችሁም? እንደ ጭስ።

ያን ጊዜ ነበር ጃፓን መሄድ።

በጃፓን ይህንን የሚያመቻቹ ሰዎች አሉ። ለዚያውም ሕጋዊ ፍቃድ ያላቸው። የመረራቸው ሰዎች እምጥ ይግቡ ስምጥ እንዳይታወቅ አድርገው፣ ዱካቸውን ሳይተዉ እንዲሰወሩ ያግዛሉ። ተግተው ይሰራል።

ማስታወቂያቸው ራሱ "ሰዎችን እንሰውራለን፣ ስንል እንሰውራለን፤ አንቀልድም" የሚል አይነት ነው።

የእነዚህ ሰዎች ስም ጆሐትሱ (jouhatsu) ይባላል። ይህ ቃል በጃፓን ቋንቋ ትነት (evaporation) ማለት መሆኑ ራሱ ስለ አገልግሎታቸው ብዙ የሚነግረን ነገር አለ።

በቃ፣ ሰዎችን ያስተንናሉ። እንደ ጭስ ተነው እንዲቀሩ ያግዝዎታል።

"ለመሆኑ ሥራ ከየት ያገኛሉ?" እንዳይሉ። ደንበኛ በሽ በሽ ነው። እንዲያውም ወረፋ አለው።

በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እልም ብለው መጥፋት ይፈልጋሉ።

አብዛኞቹ ትዳር ያቃጠላቸው ናቸው። ሌሎች ደግሞ ሥራ ያታከታቸው፣ የቤተሰብ ጫና ናላቸውን ያዞራቸው፣ በዕዳ የተነከሩ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በቃ ሕይወት ራሷ የሰለቸቻቸው፤ እነሱም የሰለቿት።

አንዳንዶች ደግሞ አገራቸው የሰለቻቸው። የገዛ አገርም ይሰለቻል አንዳንዴ። የገዛ ሕይወትም ይሰለቻል አንዳንዴ።

ደንበኞቻችን በብዛት ከአሜሪካ ከጀርመንና ከዩናይትድ ኪንግደም ናቸው ይላሉ፤ አትናኞቹ።

ደንበኞቻቸው መጥፋት ሲፈልጉ ታዲያ ቁርጥ ውሳኔ ላይ ደርሰው ነው። የማያወላዳ ውሳኔ።

እንደው ለጨዋታ እንዳይመስላችሁ እንጥፋ የሚሉት።

ምክንያቱም አንዳንዶቹ ወደ ሕይወታቸው የሚመለሱት የወለዷት ልጅ አግብታ ወልዳ ከብዳ ነው። አንዳንዶቹ ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው የሚመለሱት ከአስርታት በኋላ ነው።

ታዲያ ወዴት እንደሚሄዱ ለማንም ትንፍሽ አይሉም። ወደዚህ ሄጃለሁ አይባልም። አሊያማ ምኑን ደብዛቸው ጠፋ፤ ምኑን ተነኑት።

"ከሰው ጋማውጋት እጅ እጅ አለኝና ጠፋሁ"

"የሰው ልጅ ሁሉ ሰለቸኝ። እጅ እጅ አለኝ። አንድ ሳምሶናይት ብቻ ይዤ ወጣሁ፤ አልተመለስኩም" ይላሉ የ42 ዓመቱ ሱጊሞቶ። ሱጊሞቶ የእውነተኛ ስማቸው አይደለም።

"በቃ እጅ እጅ ከሚለው ሰው አመለጥኩ።"

ሱጊሞቶ ተወልደው ባደጉበት ሰፈር ሁሉም ሰው ያውቃቸዋል። ምክንያቱም ከትልቅ ቤተሰብ ነው የተገኙት። ይህ በራሱ መፈናፈኛ አሳጣቸው። በቃ ከዕለታት አንድ ቀን እዚህ ሄጃለሁ ሳይሉ ጠፉ፣ ጠፉ።

ብዙዎቹን ፍቅር አልባ ትዳር ያስጠፋቸዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ የዕዳ ክምር። ሌሎች ደግ ልክ እንደ ሱጊሞቶ ሳይቸግራቸው፣ በመታወቅ ውስጥ ለሕይወት ጣዕም ማጣት ያስጠፋቸዋል።

እነዚህ ኩባንያዎችን "የሕይወት ኮንትሮባንዲስቶች" ብለው የሚጠሯቸው አሉ። በሌሊት ነው ደንበኞቻቸውን ይዘው የሚሾልኩት፤ ወደ ሆነ ደሴት ሊሆን ይችላል። አዲስ ማንነት ሰጥተው። አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ከፍተው።

ሾ ሐቶሪ በዚህ የሥራ ዘርፍ ጥርሱን ነቅሎበታል። ኩባንያውን የከፈተው ድሮ በ1990ዎቹ ነው። እሱ ራሱ በፊት ይመስለው የነበረው ሰዎች በኢኮኖሚ ሲፈተኑ ብቻ ነበር የሚጠፉ የሚመስለው። ነገሩ የተገላቢጦሽ መሆኑ በኋላ ነው የገባው።

"ሰዎች ገንዘብ ብቻ አይደለም የሚያስጠፋቸው፤ የገንዘብ መብዛት፣ መታወቅ፣ ብቸኝነት፣ የህሊና ሰላም ማጣት፣ ዝርዝሩ ብዙ ነው።"

"በአጭሩ የእኛ ሥራ ለደንበኞቻችን ሁለተኛ ሕይወት መስጠት ነው፤ ምዕራፍ ሁለት ሕይወት" ይላል ሾ ሆቶሪ።

"ትዳሬ ጎመዘዘ፤ ጥፊ ጥፊ አለኝ"

የማኅበረሰብ ሳይንስ ባለሙያው ኂሮኪ ናካሞሪ ስለነዚህ ጆሐትሱዎች ብዙ ጥናትና ምርምር አሳትመዋል።

በጥናታቸው እንደደረሱበት ከሆነ ጆሐትሱ መጀመርያ ቃሉ አገልግሎት ላይ የዋለው በ60ዎቹ ነበር። በ60ዎቹ ሰዎች በፖለቲካ ምክንያት ድንገት ይሰወሩ ነበር። ያን ጊዜ እከሌ የት ሄደ ሲባል 'ተነነ' ይባል ነበር።

በኋላ ላይ ደግሞ በትዳራቸው ደስተኛ ያልሆኑ ሰዎች ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ጀመሩ።

በጃፓን የፍቺ አሐዝ በጣም ዝቅተኛ ነው። ምክንያቱ ግን ሰዎች በትዳራቸው ደስተኛ ሆነው አይደለም፤ ፍቺ ከባድ ሂደት ስለሚጠይቅ እንጂ። ስለዚህ ቀላሉ መንገድ እዚህ ነኝ ሳይሉ ወጥቶ መቅረት ሆነ። ለዚህ ደግሞ ጆሐትሱዎች አሉ።

በጃፓን ፖሊስ እከሌ ጠፋብኝ ስለተባለ ብቻ ፍለጋ አይወጣም። ፍለጋ ለመጀመር አንዳች ወንጀል ወይም አንድ አደጋ ስለመኖሩ ከቤተሰብ ማረጋገጫ ማግኘት አለበት፤ አደን ዝምብሎ አይጀመርም። ስለዚህ ለሚሰወረው ሰው ሁለተኛ ሕይወቱን ቀላል ያደርግለታል። ምክንያቱም ፖሊስ እያደነው እንዳልሆነ ያውቃልና።

"የተሰወረ አባል ያለው ቤተሰብ ማድረግ የሚችለው ከፍተኛ ገንዘብ ከፍሎ የግል መርማሪ መቅጠር ብቻ ነው። ሌላው አማራጭ መጠበቅ ብቻ ነው" ይላሉ ሶሲዮሎጂስቱ ኂሮኪ ናካሞሪ።

"ትዳሬ ጎመዘዘ፣ እንደወጣሁ ቀረሁ" የሚሉት የበዙትም ለዚሁ ነው።

"ክው ብዬ ቀረሁ"

እናት ናቸው። የ22 ዓመት ልጃቸው ከዕለታት አንድ ቀን ጠፋ። ቢጠብቁ የለም።

ለፖሊስ "አቤት!" አሉ። ፖሊስ ግን ሊረዳቸው አልቻለም። ልጃቸው ሁለት ጊዜ ከሥራ ተባሮ ነበር። "ምናልባት ያ መጥፎ ስሜት ፈጥሮበት ይሆናል" ይላሉ እናት።

"ይኖርበት ወደ ነበረበት ቤት አካባቢ እየሄድኩ ተደብቄ መኪና ውስጥ ቁጭ ብዬ ከደጅ እጠብቃለሁ። ድንገት ብቅ ካለ በሚል። ይኸው ስንት ዓመቴ።"

እናት ከፖሊስ እርዳታ አለማግኘታቸው አብግኗቸዋል።

"ይገባኛል፣ የልጄ መረጃ ለሌላ ዓላማ ሊውል ይችላል። ነገር ግን እኔ ወንጀለኛ ወይም ሰው አሳዳጅ አይደለሁም፤ እናት ነኝ። እናት እንዴት ስለልጇ መረጃ ትነፈጋለች? ይሄ ተገቢ አይደለም።"

የጃፓን ሕግ የሰዎችን ገለል የማለት ምርጫ እጅጉኑ ያከብራል። እናት አንዲህ አሉ፣ በመጨረሻ፡- "ሕጉ እስኪለወጥ ደረስ ያለኝ አማራጭ የወጣት ሬሳ ባየሁ ቁጥር ልጄ እንዳልሆነ ማረጋገጥ ብቻ ነው።"

"የጠፋሁት ባሌ አንገብግቦ ሊገድለኝ ሲል ነው"

ጆሐትሱዎች ራሳቸው ብዙዎቹ ከቤተሰባቸው የጠፉ ሰዎች ናቸው። ሌላውም እንዲጠፋ የሚያግዙት ወደው አይደለም። አንድም ቢዝነሳቸው ነው፤ አንድም ሕይወታቸው።

ድሮ የጠፋው ሱጊሞቶ ለቢቢሲ ሲናገር፣ "ሁልጊዜ ሕሊናዬን ይቆረቁረኛል፣ ለምን መሰለሽ፤ ልጄን ካየኋት ስንትና ስንት ዓመት ሆነኝ መሰለሽ። መጣሁ ብያት ጠፋሁባት፤ ፀፀት ይቦረቡረኛል።"

ሲጊሞቶ ከቶኪዮ ወጣ ብላ በምትገኝ ደበቅ ያለች ሰፈር ውስጥ ነው የሚኖረው። በዚህ ታሪክ ስሙን ስለቀየረ ቤተሰቦቹ ይህን አንብበው ሊደርሱበት አይችሉም።

የሚኖርበት ቤት ያከራየችው ሴትዮ ሳይታ ትባላለች። እሷም ስሟን ቀይራለች። እሷ ራሱ ድሮ ጠፍታ ነው ወደዚህ የመጣችው።

አሁን እሷ ራሱ ጆሐትሱ ሆናለች። ቤቷን ይህንን ሥራ ለሚሰሩ ምስጢራዊ ኩባንያዎች ታከራያለች።

"ባሌ ይደበድበኝ ነበር። የሆነ ቀን መረረኝ። እዚህ ነኝ ሳልል ከቤት ወጣሁ። ይኸው እንደቀልድ 17 ዓመት አለፈኝ።"

ሳይታ ሰው ላይ መፍረድ አትወድም። ያለ ምክንያት አይደለም።

"አሁን ብዙ ደንበኞች አሉኝ። ለመጥፋት ያበቃቸው ነገር ይለያያል። ታሪካቸውን ሲያጫውቱኝ 'ምን ካቸው? አሁን ይሄ ምክንያት ይሆናል?' አልልም። ተራ ጉዳይ ነው ያስጠፋችሁ አልላቸውም። ለምን መሰለሽ? ምክንያቱም ከታማሚው በላይ ህመሙን የሚያውቅ ሰው ቡዳ ነው።"