ቀደምት አሜሪካውያን በተነጠቀ መሬታቸው ላይ የተሰራውን ሃውልት ትራምፕ እንዳይጎበኙ ተቃውሞ እያሰሙ ነው

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የነፃነት ቀንን በማስመልከት ወደ ረሽሞር ተራራ ሊያደርጉ የነበረው ጉዞ በቀደምት አሜሪካውያን ዘንድ ተቃውሞ ገጥሞታል። ቀደምት አሜሪካውያኑ ለተቃውሞ ሰልፎችም እየተዘጋጁ ነው።
ከዚህ ቀደምም አሜሪካውያኑ የተቀደሱ ስፈራዎችና የተሰረቁ ቦታዎች ከሚሏቸው ቦታዎች ጋር ተያይዞ ከአሜሪካ መሪዎች ጋር ውዝግብም ተፈጥሮ ነበር።
ከነዚህም መካከል የሲዎክስ ህዝቦች የተቀደሰ ስፍራ በሚሉት የተገነባው የሳውዝ ዳኮታ ሃውልቶች ይገኝበታል።
ትራምፕ ተዋጊ አውሮፕላኖቻቸውን ይዘው ወደ ተራራው ለመውጣት ከሳምንት በኋላም እቅድ ይዘዋል።
ይሄ አወዛጋቢ ጉዞም በአገሪቷ ውስጥ ያለውን የዘር ውጥረት ቤንዚን አርከፍክፎበታል።
የረሽሞር ተራራ 18.2 ሜትር እርዝማኔ ያለው ሲሆን የጆርጅ ዋሺንግተን፣ ቶማስ ጄፈርሰን፣ ቲዎዶር ሩዝቬልትና የአብርሃም ሊንከን ምስልም ተቀርፆበታል።
በድንጋዩ ላይ የተቀረፀው የአራቱ ፕሬዚዳንት የፊት ምስል በጎርጎሳውያኑ 1927-1941 ድረስ ባለው ነው።
ነገር ግን ሃውልቱ የተቀረፀበት የሳውዝ ዳኮታው ብላክ ሂልስ የተሰኘው ኮረብታማ ቦታ ከቀደምት ህዝቦች ላኮታ ሲዎክስ በሃይል የተነጠቀ ነው። የአሜሪካ መንግሥት ቦታውን ከህዝቡ የነጠቀውም በጎርጎሳውያኑ 1800 ነው።
ቅርፆቹ በተጨማሪ የነጭ የበላይነትን የሚያንፀባርቁና ጥቁርአሜሪካውያንና ቀደምት አሜሪካውያን በመጨፍጨፍ ከሚታወቀው የኩ ክሉክስ ክላን ቡድን ጋር ቁርኝት አለው ተብሏል።
አንዳንድ የቀደምት አሜሪካውያን የመብት ተሟጋቾች ቦታው ለሲዎክስ ህዝቦች መመለስ አለበት ሃውልቶቹም መፍረስ አለባቸው እያሉ ነው። አንዳንዶቹ ደግሞ ከአካባቢው ከሚገኘው የቱሪዝም ገንዘብም ሊሰጣቸው ይገባልም ብለውም የሚከራከሩ አሉ።
የኦጋላ ሲዎክስ ፕሬዚዳንት ጁሊያን ቢር ራነር እንደተናገሩት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ስለ ጉበኝታቸው የቀደምት ህዝቦችን አላማከሩም ማለታቸውን አርጉስ ሊደር የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል።
ሌላኛው የቀደምት ህዝቦች የመብት ታጋይ ኒክ ቲልሰን ለአሶሺየትድ ፕሬስ እንደተናገረው ሃውልቱ የነጮች የበላይነት የሚንፀባረቅበትና በሃገሪቱ ውስጥ የተንሰራፋው መዋቅራዊ ዘረኝነትም በአሁኑ ሰዓት መቀጠሉ ማሳያ ነው ብሏል።
"የቀደምት ህዝቦችን መሬት ነጥቆና ሰርቆ፣ የነጮችና ቅኝ ገዥዎች ምስል በድንጋዩ ላይ መቅረፅ ኢ-ፍትሐዊነት ነው። እነዚህ መሪዎች መሬታችንን ብቻ ሳይሆን የነጠቁት ጨፍጭፈውናል" ብሏል።
በነጭ ፖሊስ ተደፍቆ የተገደለውን ጆርጅ ፍሎይድን ሞት ተከትሎ የባርያ ፈንጋዮች፣ የቅኝ ገዥዎችና የዘረኞች ሃውልቶች እየተገረሰሱ ነው።
በቅርቡም ፕሬዚዳንቱ ሃውልቶችን ከመገርሰስ የሚከላከል ትዕዛዝ ይፈርማሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ይህ ትእዛዝም ከተላለፈ ሃውልቶችን የሚያበላሸ ሰው እስር ይጠብቀዋል። ትራምፕ ከሰሞኑም ሃውልቶቹን የሚገረስሱ ተቃዋሚዎችን "ሽብርተኛ" ሲሉ ጠርተዋቸዋል።
ባርያ ፈንጋይ የነበሩት ጆርጅ ዋሽንግተንና ቶማስ ጄፈርሰን ሃውልቶች ከሰሞኑ ተገርስሷል።













